አንደኛ ሳሙኤል 22:1-23

  • ዳዊት ወደ አዱላም፣ በኋላም ወደ ምጽጳ ሄደ (1-5)

  • ሳኦል የኖብን ካህናት አስገደለ (6-19)

  • አብያታር አመለጠ (20-23)

22  ዳዊትም ከዚያ ተነስቶ+ ወደ አዱላም+ ዋሻ ሸሸ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤት ይህን ሲሰሙ እሱ ወዳለበት ወደዚያ ወረዱ።  ችግር ያጋጠማቸው፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ* ሰዎች ሁሉ ወደ እሱ ተሰበሰቡ፤ እሱም አለቃቸው ሆነ። ከእሱም ጋር 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ።  በኋላም ዳዊት ከዚያ ተነስቶ በሞዓብ ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞዓብንም+ ንጉሥ “አምላክ የሚያደርግልኝን ነገር እስካውቅ ድረስ እባክህ አባቴና እናቴ አንተ ጋ ይሁኑ” አለው።  በመሆኑም የሞዓብ ንጉሥ ጋ አስቀመጣቸው፤ እነሱም ዳዊት በተራራው ላይ ምሽግ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ እዚያ ተቀመጡ።+  ከጊዜ በኋላም ነቢዩ ጋድ+ ዳዊትን “እዚህ ምሽግ ውስጥ መቆየት የለብህም። ሄደህ ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው።+ በመሆኑም ዳዊት ሄዶ ወደ ሄሬት ጫካ ገባ።  ሳኦልም ዳዊትና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መገኘታቸውን ሰማ። በዚህ ጊዜ ሳኦል በጊብዓ+ በኮረብታው ላይ ባለው የታማሪስክ ዛፍ ሥር ጦሩን ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ አገልጋዮቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር።  ከዚያም ሳኦል በዙሪያው የቆሙትን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ቢንያማውያን፣ እስቲ ስሙኝ፤ ለመሆኑ የእሴይ+ ልጅ እንደ እኔ፣ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁም ይሰጣችኋል? ሁላችሁንስ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች አድርጎ ይሾማችኋል?+  እናንተ ሁላችሁ በእኔ ላይ ደባ ፈጽማችሁብኛል! የገዛ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲጋባ+ አንድም ሰው አልነገረኝም! ይኸው አሁን እንደምታዩት የገዛ ልጄ፣ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሳሳቱን አንዳችሁም ብትሆኑ ስለ እኔ ተቆርቁራችሁ አልነገራችሁኝም።”  ከዚያም በሳኦል አገልጋዮች ላይ ተሹሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦+ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወደሚገኘው ወደ አኪጡብ+ ልጅ ወደ አሂሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ። 10  አሂሜሌክም ይሖዋን ጠየቀለት፤ ስንቅም ሰጠው። ሌላው ቀርቶ የፍልስጤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።”+ 11  ንጉሡም ወዲያውኑ ሰዎች ልኮ የካህኑን የአኪጡብን ልጅ አሂሜሌክንና በኖብ በአባቱ ቤት የነበሩትን ካህናት በሙሉ አስጠራ። በመሆኑም ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ። 12  ሳኦልም “አንተ የአኪጡብ ልጅ፣ እስቲ ስማኝ!” አለው፤ እሱም መልሶ “እሺ ጌታዬ፣ እየሰማሁ ነው” አለ። 13  ከዚያም ሳኦል “ለእሴይ ልጅ ምግብና ሰይፍ በመስጠት እንዲሁም ስለ እሱ አምላክን በመጠየቅ አንተም ሆንክ እሱ ደባ የፈጸማችሁብኝ ለምንድን ነው? ይኸው አሁን እንደሚታየው እየተቃወመኝና እያደባብኝ ነው” አለው። 14  በዚህ ጊዜ አሂሜሌክ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እንደው ለመሆኑ ከአገልጋዮችህ ሁሉ መካከል እንደ ዳዊት ያለ እምነት የሚጣልበት* ማን አለ?+ እሱ የንጉሡ አማች፣+ የክብር ዘቦችህ አለቃና በቤትህ የተከበረ ሰው ነው።+ 15  ስለ እሱ አምላክን ስጠይቅ+ ዛሬ የመጀመሪያዬ ነው? የምትናገረው ነገር ፈጽሞ ያላሰብኩትን ነው! ንጉሡ አገልጋዩንም ሆነ የአባቴን ቤት በሙሉ ጥፋተኛ አያድርግ፤ ምክንያቱም አገልጋይህ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።”+ 16  ንጉሡ ግን “አሂሜሌክ፣ አንተም ሆንክ የአባትህ ቤት+ በሙሉ በእርግጥ ትሞታላችሁ”+ አለው። 17  ከዚያም ንጉሡ በዙሪያው ቆመው የነበሩትን ጠባቂዎች* “ከዳዊት ጋር ስላበሩ ዙሩና የይሖዋን ካህናት ግደሉ! ዳዊት መኮብለሉን እያወቁ አልነገሩኝም!” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን የይሖዋን ካህናት ለመግደል እጃቸውን ማንሳት አልፈለጉም። 18  ንጉሡም ዶይቅን+ “እንግዲያውስ አንተ ዙርና ካህናቱን ግደላቸው!” አለው። ኤዶማዊው+ ዶይቅም ወዲያውኑ ሄዶ ካህናቱን ገደላቸው። በዚያን ቀን፣ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ የለበሱ 85 ሰዎችን ገደለ።+ 19  እንዲሁም የካህናቱን ከተማ ኖብን+ በሰይፍ መታ፤ ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ጨቅላ ሕፃን፣ በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ አንድም ሳያስቀር ሁሉንም በሰይፍ ገደለ። 20  ሆኖም ከአኪጡብ ልጅ ከአሂሜሌክ ልጆች አንዱ የሆነው አብያታር+ አምልጦ ዳዊትን ለመከተል እሱ ወዳለበት እየሮጠ ሄደ። 21  አብያታር ለዳዊት “ሳኦል እኮ የይሖዋን ካህናት ገደላቸው” ሲል ነገረው። 22  በዚህ ጊዜ ዳዊት አብያታርን እንዲህ አለው፦ “ያን ቀን ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለነበር ይህን ለሳኦል እንደሚነግረው አውቄአለሁ።+ በአባትህ ቤት ላሉት ሰዎች* ሁሉ ሞት ተጠያቂው እኔ ራሴ ነኝ። 23  አሁን እኔ ጋ ቆይ። የአንተን ሕይወት* የሚፈልግ የእኔን ሕይወት* የሚፈልግ ስለሆነ አትፍራ፤ እኔ ከለላ እሆንሃለሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ።”
ወይም “ታማኝ።”
ቃል በቃል “ሯጮች።”
ወይም “ላለው ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”