ዘፀአት 38:1-31

  • የሚቃጠል መባ መሠዊያው (1-7)

  • የመዳብ ገንዳው (8)

  • የማደሪያ ድንኳኑ ግቢ (9-20)

  • የማደሪያ ድንኳኑ ዕቃዎች ተቆጥረው ተመዘገቡ (21-31)

38  እሱም የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ። ርዝመቱ አምስት ክንድ፣* ወርዱም አምስት ክንድ ሲሆን አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ፤ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር።+  ከዚያም በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ቀንዶቹን ሠራለት። ቀንዶቹም ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በመቀጠልም በመዳብ ለበጠው።+  ከዚህ በኋላ የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ይኸውም ባልዲዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ሳህኖቹን፣ ሹካዎቹንና መኮስተሪያዎቹን ሠራ። ዕቃዎቹን በሙሉ ከመዳብ ሠራቸው።  በተጨማሪም ለመሠዊያው ከጠርዙ ወደ ታች ወረድ ብሎ ወደ መሃል አካባቢ እንደ መረብ ያለ የመዳብ ፍርግርግ ሠራለት።  መሎጊያዎቹን ለመያዝ የሚያገለግሉትንም አራት ቀለበቶች ከመዳብ ፍርግርጉ አጠገብ በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ሠራ።  በኋላም መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በመዳብ ለበጣቸው።  ከዚያም መሠዊያውን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በመሠዊያው ጎኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስሎ ከሳንቃዎች ሠራው።  ከዚያም የመዳቡን ገንዳና+ ከመዳብ የተሠራውን ማስቀመጫውን ሠራ፤ ለዚህም በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በተደራጀ መልክ ያገለግሉ የነበሩትን ሴት አገልጋዮች መስተዋቶች* ተጠቀመ።  ከዚያም ግቢውን ሠራ።+ በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ርዝመታቸው 100 ክንድ የሆነ መጋረጃዎች ሠራ።+ 10  ከመዳብ የተሠሩ 20 ቋሚዎችና 20 መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ። 11  በተጨማሪም በስተ ሰሜን በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ርዝመታቸው 100 ክንድ ነበር። ሃያዎቹ ቋሚዎቻቸውና 20ዎቹ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ። 12  በስተ ምዕራብ በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ግን ርዝመታቸው 50 ክንድ ነበር። አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ነበሩ። 13  በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው ጎን ርዝመቱ 50 ክንድ ነበር። 14  በአንደኛው በኩል ያሉት የመግቢያው መጋረጃዎች ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው። 15  በሌላኛው በኩል ያሉት የግቢው መግቢያ መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው። 16  በግቢው ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ። 17  የቋሚዎቹ መሰኪያዎች ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸውም በብር የተለበጠ ነበር። የግቢው ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ ማያያዣዎች ነበሯቸው።+ 18  የግቢው መግቢያ መከለያ* ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር ተሸምኖ የተሠራ ነበር። ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ከፍታው ደግሞ ልክ እንደ ግቢው መጋረጃዎች 5 ክንድ ነበር።+ 19  አራቱ ቋሚዎቻቸውና አራቱ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። ማንጠልጠያዎቻቸውና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸው ደግሞ በብር የተለበጠ ነበር። 20  የማደሪያ ድንኳኑና በግቢው ዙሪያ የሚገኙት ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።+ 21  በሙሴ ትእዛዝ መሠረት ተቆጥረው የተመዘገቡት የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን+ ዕቃዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ይህን ያከናወኑት ሌዋውያኑ+ ሲሆኑ መሪያቸውም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታምር+ ነበር። 22  ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል+ ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23  ከእሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳማክ ልጅ ኤልያብ+ ነበር፤ እሱም የእጅ ባለሙያና የጥልፍ ባለሙያ እንዲሁም በሰማያዊ ክር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በጥሩ በፍታ የሚሸምን የሽመና ባለሙያ ነበር። 24  በአጠቃላይ በቅዱሱ ስፍራ ለተከናወነው ሥራ የዋለው ወርቅ በሙሉ መባ*+ ሆኖ ከቀረበው ወርቅ ጋር ተመጣጣኝ ነበር፤ ይህም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* 29 ታላንት* ከ730 ሰቅል* ነበር። 25  ከማኅበረሰቡ መካከል ከተመዘገቡት ሰዎች የተገኘው ብር ደግሞ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል 100 ታላንት ከ1,775 ሰቅል ነበር። 26  ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው ከተመዘገቡት 603,550+ ሰዎች መካከል የሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ የሰጠው ግማሽ ሰቅል፣ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* ግማሽ ሰቅል ነበር።+ 27  የቅዱሱን ስፍራ መሰኪያዎችና ለመጋረጃው ቋሚዎች የሚሆኑትን መሰኪያዎች ለመሥራት የዋለው 100 ታላንት ብር ነበር፤ 100 መሰኪያዎች 100 ታላንት ነበሩ፤ ይህም ለእያንዳንዱ መሰኪያ አንድ ታላንት ማለት ነው።+ 28  ለቋሚዎቹ ከ1,775 ሰቅል ብር ማንጠልጠያዎችን ሠራ፤ አናታቸውንም ከለበጠ በኋላ እርስ በርስ አያያዛቸው። 29  መባ* ሆኖ የቀረበው መዳብ ደግሞ 70 ታላንት ከ2,400 ሰቅል ነበር። 30  በዚህም የመገናኛ ድንኳኑን መግቢያ መሰኪያዎች፣ የመዳብ መሠዊያውንና የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ሠራ፤ 31  እንዲሁም በግቢው ዙሪያ ያሉትን መሰኪያዎች፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆኑትን መሰኪያዎች እንዲሁም የማደሪያ ድንኳኑን ካስማዎች በሙሉና በግቢው ዙሪያ ያሉትን የድንኳን ካስማዎች+ በሙሉ ሠራ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በደንብ የተወለወሉ የብረት መስተዋቶችን ያመለክታል።
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም “የሚወዘወዝ መባ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
ወይም “የሚወዘወዝ መባ።”