ዘፀአት 14:1-31

  • እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ደረሱ (1-4)

  • ፈርዖን እስራኤላውያንን አሳደዳቸው (5-14)

  • እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተሻገሩ (15-25)

  • ግብፃውያን ባሕሩ ውስጥ ሰመጡ (26-28)

  • እስራኤላውያን በይሖዋ አመኑ (29-31)

14  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “ወደ ኋላ ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በበዓልጸፎን ትይዩ በሚገኘው በፊሃሂሮት ፊት ለፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው።+ በበዓልጸፎን ፊት ለፊት በባሕሩ አጠገብ ስፈሩ።  ፈርዖንም ስለ እስራኤላውያን ‘ግራ ተጋብተው በምድሪቱ ላይ እየተንከራተቱ ነው። ምድረ በዳው ጋሬጣ ሆኖባቸዋል’ ማለቱ አይቀርም።  እኔም የፈርዖን ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ እሱም ያሳድዳቸዋል፤ እኔም ፈርዖንንና ሠራዊቱን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን እጎናጸፋለሁ፤+ ግብፃውያንም እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”+ እነሱም ልክ እንዲሁ አደረጉ።  በኋላም ለግብፁ ንጉሥ ሕዝቡ እንደኮበለለ ተነገረው። ፈርዖንና አገልጋዮቹም ስለ ሕዝቡ የነበራቸውን ሐሳብ ወዲያው በመቀየር+ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን ባሪያ ሆነው እንዳያገለግሉን የለቀቅናቸው ምን ነክቶን ነው?” አሉ።  በመሆኑም ፈርዖን የጦር ሠረገሎቹ እንዲዘጋጁለት አደረገ፤ ሠራዊቱንም ከጎኑ አሰለፈ።+  ከዚያም 600 የተመረጡ ሠረገሎችንና ሌሎች የግብፅ ሠረገሎችን ሁሉ ይዞ ተነሳ፤ በእያንዳንዱም ሠረገላ ላይ ተዋጊዎች ነበሩ።  በዚህ መንገድ ይሖዋ የግብፁ ንጉሥ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ እስራኤላውያን ወጥተው በልበ ሙሉነት* እየሄዱ ሳሉ ፈርዖን እነሱን ማሳደዱን ተያያዘው።+  ግብፃውያኑ ተከታተሏቸው፤+ እስራኤላውያን በበዓልጸፎን ፊት ለፊት በባሕሩ አጠገብ ባለው በፊሃሂሮት ሰፍረው ሳሉም የፈርዖን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞቹና ሠራዊቱ በሙሉ ደረሱባቸው። 10  ፈርዖን ወደ እነሱ ሲቀርብ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ ግብፃውያኑ እነሱን እየተከታተሏቸው ነበር። እስራኤላውያንም ተሸበሩ፤ ወደ ይሖዋም ይጮኹ ጀመር።+ 11  እነሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እዚህ ምድረ በዳ ውስጥ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ የመቃብር ቦታ ጠፍቶ ነው?+ ከግብፅ መርተህ በማውጣት ምን ያደረግክልን ነገር አለ? 12  በግብፅ ሳለን ‘እባክህ ተወን፤ አርፈን ግብፃውያንን እናገልግል’ ብለንህ አልነበረም? እዚህ ምድረ በዳ ውስጥ ከመሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻለን ነበር።”+ 13  በዚህ ጊዜ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ።+ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በዛሬው ዕለት ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚፈጽመውን የእሱን ማዳን እዩ።+ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም፤ በጭራሽ አታዩአቸውም።+ 14  ይሖዋ ራሱ ስለ እናንተ ይዋጋል፤+ ብቻ እናንተ ዝም በሉ።” 15  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ወደ እኔ ትጮኻለህ? እስራኤላውያን ድንኳናቸውን ነቅለው እንዲጓዙ ንገራቸው። 16  አንተም እስራኤላውያን በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት እንዲሻገሩ በትርህን አንሳና እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር፤ ባሕሩንም ክፈለው። 17  እኔ ደግሞ የግብፃውያን ልብ እንዲደነድን ስለምፈቅድ እስራኤላውያንን ተከትለው ይገባሉ፤ እኔም ፈርዖንን፣ ሠራዊቱን ሁሉ፣ የጦር ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን እጎናጸፋለሁ።+ 18  ፈርዖንን፣ የጦር ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን በምጎናጸፍበት ጊዜ ግብፃውያን እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”+ 19  ከዚያም ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ፊት ይሄድ የነበረው የእውነተኛው አምላክ መልአክ+ ከዚያ ተነስቶ ወደ ኋላቸው ሄደ፤ ከፊታቸው የነበረውም የደመና ዓምድ ወደ ኋላቸው ሄዶ በስተ ጀርባቸው ቆመ።+ 20  በመሆኑም የደመናው ዓምድ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ሆነ።+ ዓምዱ በአንደኛው በኩል ጭልም ያለ ደመና ነበር። በሌላኛው በኩል ደግሞ ለሌሊቱ ብርሃን ይሰጥ ነበር።+ ስለሆነም ሌሊቱን ሙሉ አንደኛው ወገን ወደ ሌላኛው ወገን መቅረብ አልቻለም። 21  ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤+ ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ፤ የባሕሩንም ወለል ወደ ደረቅ መሬት ለወጠው፤+ ውኃውም ተከፈለ።+ 22  በመሆኑም እስራኤላውያን ውኃው በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ+ በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገሩ።+ 23  ግብፃውያኑም እነሱን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ የጦር ሠረገሎችና ፈረሰኞች ሁሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ መሃል ገቡ።+ 24  በማለዳውም ክፍለ ሌሊት* ይሖዋ በእሳትና በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤+ የግብፃውያንም ሠራዊት ግራ እንዲጋባ አደረገ። 25  ሠረገሎቻቸውን መንዳት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው የሠረገሎቻቸውን መንኮራኩሮች* አወላለቀባቸው፤ ግብፃውያኑም “ይሖዋ እስራኤላውያንን በመደገፍ ግብፃውያንን እየተዋጋላቸው ስለሆነ ከእስራኤላውያን ፊት እንሽሽ” አሉ።+ 26  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ውኃው በግብፃውያን፣ በጦር ሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ተመልሶ እንዲመጣባቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር” አለው። 27  ሙሴም ወዲያውኑ እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤ ሊነጋጋ ሲልም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ። ግብፃውያንም ውኃው እንዳይደርስባቸው ለመሸሽ ሲሞክሩ ይሖዋ ግብፃውያኑን ባሕሩ መሃል ጣላቸው።+ 28  ውኃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው የገቡትን የጦር ሠረገሎችና ፈረሰኞች እንዲሁም የፈርዖንን ሠራዊት በሙሉ አለበሳቸው።+ ከእነሱም መካከል አንድም የተረፈ የለም።+ 29  እስራኤላውያን ግን ውኃው በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ+ በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተጓዙ።+ 30  በዚህ መንገድ ይሖዋ በዚያ ቀን እስራኤላውያንን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤+ እስራኤላውያንም የግብፃውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ላይ ወድቆ ተመለከቱ። 31  በተጨማሪም እስራኤላውያን ይሖዋ ግብፃውያንን የመታበትን ኃያል ክንድ ተመለከቱ፤ ሕዝቡም ይሖዋን መፍራት ጀመረ፤ በይሖዋና በአገልጋዩ በሙሴም አመነ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወደ ላይ በተዘረጋ እጅ።”
ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ገደማ ያለውን ጊዜ ያመለክታል።
ተሽከርካሪ እግር።