ዘዳግም 34:1-12
34 ከዚያም ሙሴ ከሞዓብ በረሃማ ሜዳ ተነስቶ ወደ ነቦ ተራራ+ ይኸውም በኢያሪኮ+ ትይዩ ወደሚገኘው ወደ ጲስጋ አናት+ ወጣ። ይሖዋም ምድሪቱን በሙሉ አሳየው፤ ይኸውም ከጊልያድ እስከ ዳን፣+
2 ንፍታሌምን በሙሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ምድር፣ በስተ ምዕራብ በኩል እስካለው ባሕር* ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር በሙሉ፣+
3 ኔጌብን፣+ የዮርዳኖስን አውራጃ+ እንዲሁም የዘንባባ ዛፍ ከተማ በሆነችው በኢያሪኮ ካለው ሸለቋማ ሜዳ አንስቶ እስከ ዞአር+ ድረስ አሳየው።
4 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’+ በማለት የማልኩላቸው ምድር ይህች ናት። በዓይንህ እንድታያት አድርጌሃለሁ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትሻገርም።”+
5 የይሖዋ አገልጋይ ሙሴም ልክ ይሖዋ እንደተናገረው በዚያው በሞዓብ ምድር ሞተ።+
6 እሱም ከቤትጰኦር ትይዩ በሞዓብ ምድር በሚገኘው ሸለቆ ቀበረው፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩ የት እንደሚገኝ የሚያውቅ የለም።+
7 ሙሴ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 120 ዓመት ነበር።+ ዓይኖቹ አልፈዘዙም፤ ጉልበቱም አልደከመም ነበር።
8 እስራኤላውያንም በሞዓብ በረሃማ ሜዳ ለሙሴ 30 ቀን አለቀሱለት።+ በመጨረሻም ለሙሴ የሚለቀስበትና የሚታዘንበት ጊዜ አበቃ።
9 የነዌ ልጅ ኢያሱ ሙሴ እጁን ስለጫነበት+ የጥበብ መንፈስ ተሞልቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም እሱን ይሰሙት ጀመር፤ እንዲሁም ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።+
10 ሆኖም ይሖዋ ፊት ለፊት እንዳወቀው+ እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እስካሁን በእስራኤል ተነስቶ አያውቅም።+
11 ይሖዋ በግብፅ ምድር በፈርዖን፣ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ ሁሉ ፊት እንዲፈጽም የላከውን ምልክቶችና ተአምራት በሙሉ ፈጸመ፤+
12 ከዚህም በተጨማሪ ሙሴ በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት በኃያል ክንድ ታላቅና አስፈሪ ድርጊት ፈጸመ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ታላቁን ባሕር፣ ሜድትራንያንን ያመለክታል።