ዘዳግም 20:1-20

  • ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ ሊከተሉት የሚገባው ሕግ (1-20)

    • ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ መሆን (5-9)

20  “ከጠላቶችህ ጋር ጦርነት ለመግጠም ብትሄድና ፈረሶቻቸው፣ ሠረገሎቻቸውና ሠራዊታቸው ከአንተ ይልቅ እጅግ ብዙ መሆናቸውን ብታይ አትፍራቸው፤ ምክንያቱም ከግብፅ ምድር ያወጣህ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው።+  ወደ ውጊያው ለመግባት በምትቀርቡበትም ጊዜ ካህኑ መጥቶ ሕዝቡን ማነጋገር አለበት።+  እንዲህም ይበላቸው፦ ‘እስራኤላውያን ሆይ፣ ስሙ፤ እንግዲህ ዛሬ ከጠላቶቻችሁ ጋር ጦርነት ልትገጥሙ ነው። ልባችሁ አይራድ። በእነሱ ምክንያት አትፍሩ፣ አትሸበሩ ወይም አትንቀጥቀጡ፤  ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ ጠላቶቻችሁን ሊዋጋላችሁና ሊያድናችሁ አብሯችሁ ይወጣል።’+  “አለቆቹም ሕዝቡን እንዲህ ይበሉ፦ ‘ከመካከላችሁ አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለ? ወደ ቤቱ ይመለስ። አለዚያ በጦርነቱ ላይ ሊሞትና ቤቱን ሌላ ሰው ሊያስመርቀው ይችላል።  ወይን ተክሎ ገና ከዚያ ያልበላ አለ? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። አለዚያ በጦርነቱ ላይ ሊሞትና ሌላ ሰው ሊበላው ይችላል።  አንዲት ሴት አጭቶ ገና ያላገባት ሰው አለ? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ።+ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ሊሞትና ሌላ ሰው ሊያገባት ይችላል።’  በተጨማሪም አለቆቹ ለሕዝቡ እንዲህ በማለት ይናገሩ፦ ‘ከመካከላችሁ የፈራና ልቡ የራደ አለ?+ ልክ እንደ ራሱ ልብ የወንድሞቹንም ልብ እንዳያቀልጥ+ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ።’  አለቆቹም ለሕዝቡ ተናግረው ሲጨርሱ ሕዝቡን እንዲመሩ የሠራዊቱን አለቆች ይሹሙ። 10  “አንዲትን ከተማ ለመውጋት ወደ እሷ ስትቀርብ ለከተማዋ የሰላም ጥሪ አስተላልፍ።+ 11  ከተማዋ የሰላም ጥሪህን ከተቀበለችና በሯን ከከፈተችልህ ነዋሪዎቿ ሁሉ የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሕዝቦች ይሆኑልሃል፤ አንተንም ያገለግሉሃል።+ 12  ይሁን እንጂ የሰላም ጥሪህን ካልተቀበለችና ከአንተ ጋር ውጊያ ለመግጠም ከተነሳች ከተማዋን ክበባት፤ 13  አምላክህ ይሖዋ ከተማዋን በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ አንተም በውስጧ የሚኖሩትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው። 14  ሆኖም ሴቶቹን፣ ትናንሽ ልጆቹን፣ እንስሳቱንና በከተማዋ ውስጥ የተገኘውን ነገር ሁሉ ማርከህ ለራስህ መውሰድ ትችላለህ፤+ አምላክህ ይሖዋ በእጅህ አሳልፎ የሰጠህን ከጠላቶችህ ያገኘኸውን ምርኮም ትበላለህ።+ 15  “በአቅራቢያህ በሚገኙ በእነዚህ ብሔራት ከተሞች ላይ ሳይሆን ከአንተ ርቀው በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ላይ የምታደርገው ይህንኑ ነው። 16  አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ እነዚህ ሕዝቦች በሚኖሩባቸው ከተሞች ውስጥ ግን እስትንፋስ ያለውን ማንኛውንም ነገር በሕይወት አታስቀር።+ 17  ከዚህ ይልቅ አምላክህ ይሖዋ ባዘዘህ መሠረት ሂታውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነአናውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ሙሉ በሙሉ አጥፋ፤+ 18  ይህን የምታደርጉት ለአማልክታቸው የሚያደርጓቸውን አስጸያፊ ነገሮች በሙሉ እንዳያስተምሯችሁና በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እንድትሠሩ እንዳያደርጓችሁ ነው።+ 19  “አንዲትን ከተማ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ብትከባትና ለብዙ ቀናት ብትወጋት ዛፎቿን በመጥረቢያ አትጨፍጭፍ። ፍሬያቸውን ልትበላ ትችላለህ፤ ሆኖም አትቁረጣቸው።+ ደግሞስ ሰው ይመስል የሜዳን ዛፍ ከበህ ማጥፋት አለብህ? 20  ለምግብነት እንደማይሆን የምታውቀውን ዛፍ ብቻ ማጥፋት ትችላለህ። ዛፉንም ቆርጠህ ከአንተ ጋር ውጊያ የገጠመችው ከተማ እስክትወድቅ ድረስ ዙሪያዋን ልታጥርበት ትችላለህ።

የግርጌ ማስታወሻዎች