ዘኁልቁ 5:1-31

  • የረከሱ ሰዎች ተገልለው እንዲቆዩ ማድረግ (1-4)

  • ኃጢአትን መናዘዝና ካሳ መክፈል (5-10)

  • በዝሙት የተጠረጠረችን ሚስት እርግማን በሚያመጣው ውኃ መፈተን (11-31)

5  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “እስራኤላውያንን የሥጋ ደዌ ያለበትን፣+ ፈሳሽ የሚወጣውንና+ በሞተ ሰው* የረከሰን+ ማንኛውንም ሰው ከሰፈሩ እንዲያስወጡ እዘዛቸው።  ወንድም ሆነ ሴት አስወጧቸው። እኔ በመካከላቸው ስለምኖር*+ ሕዝቤ የሚኖርባቸውን ሰፈሮች እንዳይበክሉ+ ከሰፈሩ አስወጧቸው።”  በመሆኑም እስራኤላውያን እንደተባሉት አደረጉ፤ ሰዎቹንም ከሰፈሩ አስወጧቸው። እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ለሙሴ እንደነገረው አደረጉ።  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት የሰው ልጆች ከሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች ውስጥ የትኛውንም ቢሠሩና በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽሙ ይህን ያደረገው ሰው* በደለኛ ይሆናል።+  እሱም* የሠራውን ኃጢአት መናዘዝና+ ለፈጸመው በደል ካሳ አድርጎ ሙሉ ዋጋውን መመለስ አለበት፤ የዚህን አንድ አምስተኛም ይጨምርበት፤+ በደል ለፈጸመበትም ሰው ይስጠው።  ሆኖም በደል የተፈጸመበት ሰው ቢሞትና ካሳውን የሚቀበልለት የቅርብ ዘመድ ባይኖረው ካህኑ የግለሰቡን በደል ከሚያስተሰርይበት አውራ በግ በስተቀር ካሳው ለይሖዋ ይመለስ፤ የካህኑም ይሆናል።+  “‘እስራኤላውያን ለካህኑ የሚያቀርቧቸው ቅዱስ መዋጮዎች+ በሙሉ የእሱ ይሆናሉ።+ 10  እያንዳንዱ ሰው የሚያቀርባቸው ቅዱስ የሆኑ ነገሮች የእሱ ይሆናሉ። እያንዳንዱ ሰው ለካህኑ የሚሰጠው ማንኛውም ነገር የካህኑ ይሆናል።’” 11  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአንድ ሰው ሚስት ከትክክለኛው መንገድ ዞር በማለት ለባሏ ታማኝ ሳትሆን ብትቀርና 13  ሌላ ወንድ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም፣+ ባሏ ግን ይህን ነገር ባያውቅና ጉዳዩ ተሰውሮ ቢቀር፣ ይህች ሴት በዚህ መንገድ ራሷን ብታረክስም የሚመሠክርባት ሰው ባይገኝና እጅ ከፍንጅ ባትያዝ፣ 14  ባሏም ሚስቱ ራሷን አርክሳ ሳለ የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና የሚስቱን ታማኝነት ቢጠራጠር ወይም ደግሞ ራሷን ሳታረክስ የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና ታማኝነቷን ቢጠራጠር 15  ሰውየው ሚስቱን ለእሷ ከሚቀርበው መባ ይኸውም ከአንድ አሥረኛ ኢፍ* የገብስ ዱቄት ጋር ወደ ካህኑ ያምጣ። ይህ የቅናት የእህል መባ ይኸውም በደል እንዲታወስ የሚያደርግ የእህል መባ ስለሆነ በላዩ ላይ ዘይት አያፍስበት ወይም ነጭ ዕጣን አያድርግበት። 16  “‘ካህኑ ሴትየዋን አምጥቶ ይሖዋ ፊት እንድትቆም ያደርጋል።+ 17  ከዚያም ካህኑ የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ከማደሪያ ድንኳኑም ወለል ላይ ጥቂት አፈር ወስዶ ውኃው ውስጥ ይጨምረዋል። 18  ካህኑም ሴትየዋ በይሖዋ ፊት እንድትቆም ያደርጋል፤ ፀጉሯንም ይፈታል፤ ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል መባ ይኸውም የቅናት የእህል መባውን+ በእጆቿ ላይ ያደርጋል፤ ካህኑም እርግማን የሚያመጣውን መራራ ውኃ በእጁ ይይዛል።+ 19  “‘ካህኑም ሴትየዋን እንዲህ በማለት ያስምላታል፦ “በባልሽ ሥልጣን ሥር ሆነሽ ሳለ+ ሌላ ወንድ ከአንቺ ጋር የፆታ ግንኙነት ካልፈጸመ አንቺም ከትክክለኛው መንገድ ዞር ካላልሽና ካልረከስሽ እርግማን የሚያስከትለው ይህ ውኃ ምንም ጉዳት አያድርስብሽ። 20  ይሁንና በባልሽ ሥልጣን ሥር ሆነሽ ሳለ ራስሽን በማርከስ ከትክክለኛው መንገድ ዞር ብለሽ ከሆነና ከሌላ ወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመሽ+ ከሆነ . . . ” 21  ካህኑም ሴትየዋን እርግማን ያለበት መሐላ ያስምላታል፤ እንዲህም ይላታል፦ “ይሖዋ ጭንሽ* እንዲሰልና* ሆድሽ እንዲያብጥ በማድረግ፣ ይሖዋ በሕዝብሽ መካከል የእርግማንና የመሐላ ምሳሌ ያድርግሽ። 22  እርግማን የሚያመጣው ይህ ውኃ ወደ አንጀትሽ ገብቶ ሆድሽን ያሳብጠው፤ መሃንም ያድርግሽ።” በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “አሜን! አሜን!”* ትበል። 23  “‘ከዚያም ካህኑ እነዚህን እርግማኖች በመጽሐፍ ይጻፋቸው፤ በመራራውም ውኃ አጥቦ ያጥፋቸው። 24  እርግማን የሚያመጣውን መራራ ውኃም እንድትጠጣ ያድርግ፤ ውኃውም ወደ ሰውነቷ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያስከትልባት። 25  ካህኑም የቅናት የእህል መባውን+ ከሴትየዋ እጅ ላይ ወስዶ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዘው፤ ወደ መሠዊያውም ያምጣው። 26  ካህኑም ከእህል መባው ላይ አንድ እፍኝ በመውሰድ የመባው መታሰቢያ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጭሰው፤+ ከዚያ በኋላ ሴትየዋ ውኃውን እንድትጠጣ ያድርግ። 27  ውኃውን እንድትጠጣ በሚያደርግበትም ጊዜ ሴትየዋ ራሷን አርክሳና በባሏ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽማ ከሆነ እርግማን የሚያመጣው ውኃ ወደ ሰውነቷ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያስከትልባታል፤ ሆዷም ያብጣል፤ ጭኗም* ይሰልላል፤* እሷም በሕዝቧ መካከል የእርግማን ምሳሌ ትሆናለች። 28  ይሁንና ሴትየዋ ራሷን ካላረከሰችና ንጹሕ ከሆነች እንዲህ ካለው ቅጣት ነፃ ትሆናለች፤ እንዲሁም መጸነስና ልጆች ማፍራት ትችላለች። 29  “‘እንግዲህ ቅናትን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፤+ አንዲት ሴት በባሏ ሥልጣን ሥር ሆና ሳለ ከትክክለኛው መንገድ ዞር ብትልና ራሷን ብታረክስ 30  ወይም አንድ ሰው የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና የሚስቱን ታማኝነት ቢጠራጠር ሕጉ ይህ ነው፤ እሱም ሚስቱ በይሖዋ ፊት እንድትቆም ያድርግ፤ ካህኑም ይህ ሕግ በሙሉ በእሷ ላይ እንዲፈጸም ያድርግ። 31  ሰውየው ከበደል ነፃ ይሆናል፤ ሚስቱ ግን ስለ በደሏ ትጠየቃለች።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ስለማድር።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “እነሱም።”
አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የመራቢያ አካላትን የሚያመለክት ይመስላል።
ወይም “እንዲመነምንና።” ዘር የማፍራት ችሎታ ማጣትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ወይም “ይሁን! ይሁን!”
የመራቢያ አካላትን የሚያመለክት ይመስላል።
ወይም “ይመነምናል።” ዘር የማፍራት ችሎታ ማጣትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።