ዘኁልቁ 36:1-13

  • ውርስ የሚሰጣቸው ሴቶች የሚያገቡትን ሰው በተመለከተ የወጣ ሕግ (1-13)

36  ከዮሴፍ ልጆች ቤተሰቦች የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣+ የጊልያድ ተወላጆች የአባቶች ቤት መሪዎች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን የአባቶች ቤት መሪዎች ወደሆኑት አለቆች ቀርበው ተናገሩ፤  እንዲህም አሉ፦ “ይሖዋ ጌታዬን ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ርስት አድርጎ በዕጣ እንዲያከፋፍል አዞት ነበር፤+ ደግሞም የወንድማችንን የሰለጰአድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ እንዲሰጥ ይሖዋ ጌታዬን አዞት ነበር።+  እነዚህ ሴቶች ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባሎችን ቢያገቡ የእነሱ ውርስ ከአባቶቻችን ውርስ ላይ ተወስዶ በሚያገቡት ሰው ነገድ ውርስ ላይ ይጨመራል፤ በመሆኑም በዕጣ ከተሰጠን ውርስ ላይ ይቀነሳል።  የእስራኤል ሕዝብ የኢዮቤልዩ+ ዓመት በሚደርስበት ጊዜ የሴቶቹ ውርስ በሚያገቡት ሰው ነገድ ውርስ ላይ ለዘለቄታው ይጨመራል፤ በመሆኑም የእነሱ ውርስ ከአባቶቻችን ነገድ ውርስ ላይ ይቀነሳል።”  ከዚያም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “የዮሴፍ ልጆች ነገድ የተናገረው ነገር ትክክል ነው።  ይሖዋ የሰለጰአድን ሴቶች ልጆች በተመለከተ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘የፈለጉትን ሰው ማግባት ይችላሉ። ሆኖም ከአባታቸው ነገድ ቤተሰብ የሆነን ሰው ማግባት ይኖርባቸዋል።  የትኛውም የእስራኤላውያን ውርስ ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ መተላለፍ የለበትም፤ ምክንያቱም እስራኤላውያን እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ነገድ ውርስ አጽንተው መያዝ አለባቸው።  እስራኤላውያን የቀደሙትን አባቶቻቸውን ውርስ ጠብቀው ማቆየት እንዲችሉ በእስራኤል ነገዶች መካከል ውርስ ያላት የትኛዋም ልጅ የአባቷ ነገድ ተወላጅ የሆነ ሰው ማግባት ይኖርባታል።+  የትኛውም ውርስ ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ መተላለፍ የለበትም፤ ምክንያቱም የእስራኤል ነገዶች እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ውርስ አጽንተው መያዝ አለባቸው።’” 10  የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።+ 11  ስለሆነም የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች+ የሆኑት ማህላ፣ ቲርጻ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ኖኅ የአባታቸውን ወንድሞች ልጆች አገቡ። 12  ውርሻቸው በአባታቸው ቤተሰብ ነገድ ሥር እንደሆነ እንዲቀጥል የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ልጆች ቤተሰቦች የሆኑ ወንዶችን አገቡ። 13  ይሖዋ በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸው ትእዛዛትና ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች