ዘኁልቁ 23:1-30

  • የመጀመሪያው የበለዓም ምሳሌያዊ አነጋገር (1-12)

  • ሁለተኛው የበለዓም ምሳሌያዊ አነጋገር (13-30)

23  ከዚያም በለዓም ባላቅን “እዚህ ቦታ ላይ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤+ እንዲሁም ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅልኝ” አለው።  ባላቅም ወዲያውኑ በለዓም እንዳለው አደረገ። ባላቅና በለዓም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።+  ከዚያም በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ እዚህ የሚቃጠለው መባህ አጠገብ ቆይ፤ እኔ ግን ልሂድ። ምናልባት ይሖዋ ይገለጥልኝ ይሆናል። እሱ የሚገልጥልኝን ማንኛውንም ነገር እነግርሃለሁ።” በመሆኑም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኮረብታ ሄደ።  በለዓምም ከአምላክ ጋር በተገናኘ ጊዜ+ “ሰባቱን መሠዊያዎች በመደዳ አቁሜያቸዋለሁ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቅርቤያለሁ” አለው።  ይሖዋም በበለዓም አፍ ላይ ይህን ቃል አስቀመጠ፦+ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ ብለህ ንገረው።”  በመሆኑም በለዓም ተመለሰ፤ እሱም ባላቅን ከሞዓብ መኳንንት ሁሉ ጋር በሚቃጠለው መባው አጠገብ ቆሞ አየው።  ከዚያም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+ “የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ከአራም፣+ከምሥራቅ ተራሮች አመጣኝ፤ ‘ና፣ ያዕቆብን እርገምልኝ። አዎ ና፣ እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።+   አምላክ ያልረገመውን እኔ እንዴት ልረግም እችላለሁ? ይሖዋ ያላወገዘውንስ እኔ እንዴት ላወግዝ እችላለሁ?+   ከዓለቶቹ አናት ላይ ሆኜ አያቸዋለሁ፤ከኮረብቶቹም ላይ ሆኜ እመለከታቸዋለሁ። በዚያ እንደ አንድ ሕዝብ ብቻቸውን ሰፍረዋል፤+ከሌሎች ብሔራት እንደ አንዱ አድርገው ራሳቸውን አይቆጥሩም።+ 10  ከብዛቱ የተነሳ እንደ አፈር የሆነውን ያዕቆብን ማን ሊቆጥረው ይችላል?+የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቆጥረዋል? የቅኖች ዓይነት አሟሟት ልሙት፤*መጨረሻዬም እንደ እነሱ ይሁን።” 11  ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? እኔ እኮ ያመጣሁህ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ነው፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አልፈየድክልኝም።”+ 12  እሱም መልሶ “እኔ መናገር ያለብኝ ይሖዋ በአፌ ላይ ያስቀመጠውን ብቻ አይደለም?” አለ።+ 13  ከዚያም ባላቅ እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ እነሱን ማየት ወደምትችልበት ሌላ ቦታ አብረን እንሂድ። እርግጥ ሁሉንም አታያቸውም፤ የምታያቸው በከፊል ብቻ ነው። እዚያ ሆነህ እርገምልኝ።”+ 14  እሱም በጲስጋ አናት+ ላይ ወደሚገኘው የጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ በዚያም ሰባት መሠዊያዎችን ሠርቶ በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።+ 15  በለዓምም ባላቅን “እኔ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ አንተ እዚሁ የሚቃጠለው መባህ አጠገብ ቆይ” አለው። 16  ይሖዋም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ በአፉም ላይ ይህን ቃል አስቀመጠ፦+ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ ብለህ ንገረው።” 17  በመሆኑም በለዓም ወደ ባላቅ ተመለሰ፤ ባላቅንም በሚቃጠለው መባው አጠገብ ሲጠብቀው አገኘው፤ የሞዓብ መኳንንትም ከእሱ ጋር ነበሩ። ከዚያም ባላቅ “ለመሆኑ ይሖዋ ምን አለ?” ሲል ጠየቀው። 18  በለዓምም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+ “ባላቅ ተነስ፤ አዳምጥ። የሴፎር ልጅ ሆይ፣ ጆሮህን ስጠኝ። 19  አምላክ እንደ ሰው አይዋሽም፤+እንደ ሰው ልጅም ሐሳቡን አይለውጥም።*+ እሱ ያለውን አያደርገውም? የተናገረውንስ አይፈጽመውም?+ 20  እንግዲህ የእኔ ተልእኮ መባረክ ነው፤እሱ እንደሆነ ባርኳል፤+ እኔ ደግሞ ልለውጠው አልችልም።+ 21  ያዕቆብን ለማጥቃት የታሰበን ማንኛውንም አስማታዊ ኃይል ዝም ብሎ አያልፍም፤በእስራኤል ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዲደርስ አይፈቅድም። አምላኩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነው፤+በመካከላቸውም እንደ ንጉሥ ከፍ ባለ ድምፅ ይወደሳል። 22  አምላክ ከግብፅ አውጥቷቸዋል።+ እሱም ለእነሱ ልክ እንደ ጎሽ ቀንዶች ነው።+ 23  በያዕቆብ ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ድግምት የለምና፤+በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ሟርት የለም።+ በዚህ ጊዜ ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል ‘አምላክ ያደረገውን ተመልከቱ!’ ይባላል። 24  ልክ እንደ አንበሳ የሚነሳው ሕዝብ ይህ ነው፤እሱም እንደ አንበሳ ተነስቶ ይቆማል።+ ያደነውን እስኪበላ፣የተገደሉትንም ደማቸውን እስኪጠጣ ድረስ አይተኛም።” 25  ከዚያም ባላቅ በለዓምን “እንግዲያው ልትረግመው ካልቻልክ ልትባርከውም አይገባም” አለው። 26  በለዓምም መልሶ ባላቅን “‘እኔ የማደርገው ይሖዋ የሚናገረውን ብቻ ነው’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።+ 27  ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ና፤ እስቲ አሁንም ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ። ምናልባትም እውነተኛው አምላክ እዚያ ሆነህ እሱን እንድትረግምልኝ ይፈቅድ ይሆናል።”+ 28  ስለዚህ ባላቅ በለዓምን፣ የሺሞንን* ፊት ለፊት ማየት ወደሚቻልበት ወደ ፌጎር አናት ወሰደው።+ 29  ከዚያም በለዓም ባላቅን “እዚህ ቦታ ላይ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤ እንዲሁም ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅልኝ” አለው።+ 30  ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፤ ከዚያም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሴ የቅኖች ዓይነት አሟሟት ትሙት።”
ወይም “አይጸጸትም።”
“በረሃውን፤ ምድረ በዳውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።