ዘኁልቁ 19:1-22

  • ቀይ ላምና የሚያነጻው ውኃ (1-22)

19  ይሖዋ ሙሴንና አሮንን በድጋሚ እንዲህ አላቸው፦  “ይሖዋ ያዘዘው የሕጉ ደንብ ይህ ነው፦ ‘እንከን የሌለባትና+ ቀንበር ተጭኖባት የማታውቅ በጥሩ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አንዲት ቀይ ላም እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው።  ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጡት፤ እሱም ከሰፈሩ ውጭ ይወስዳትና በፊቱ ትታረዳለች።  ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ከደሙ ላይ በጣቱ ወስዶ ደሙን በቀጥታ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።+  ከዚያም ላሟ ዓይኑ እያየ ትቃጠላለች። ቆዳዋ፣ ሥጋዋና ደሟ ከፈርሷ ጋር አብሮ ይቃጠላል።+  ካህኑም የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ሂሶጵና+ ደማቅ ቀይ ማግ ወስዶ ላሟ የምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምራል።  ከዚያም ካህኑ ልብሶቹን በውኃ ያጥባል፤ ገላውንም ይታጠባል፤ ከዚያ በኋላ ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል፤ ሆኖም ካህኑ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።  “‘ላሟን ያቃጠለውም ሰው ልብሶቹን በውኃ ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።  “‘ንጹሕ የሆነ ሰው የላሟን አመድ+ አፍሶ ከሰፈሩ ውጭ ባለ ንጹሕ ቦታ ያጠራቅመዋል፤ የእስራኤል ማኅበረሰብም ለማንጻት የሚያገለግለውን ውኃ+ ለማዘጋጀት እንዲውል አመዱን ያስቀምጠው። ይህ የኃጢአት መባ ነው። 10  የላሟን አመድ የሚያፍሰው ሰው ልብሶቹን ያጥባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። “‘ይህም ለእስራኤላውያንና በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።+ 11  የሞተ ሰው* የነካ ማንኛውም ሰው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።+ 12  ይህ ሰው በሦስተኛው ቀን ራሱን በውኃው ያንጻ፤ በሰባተኛውም ቀን ንጹሕ ይሆናል። በሦስተኛው ቀን ራሱን ካላነጻ ግን በሰባተኛው ቀን ንጹሕ አይሆንም። 13  የሞተ ሰው* የነካና ራሱን ያላነጻ ሰው ሁሉ የይሖዋን የማደሪያ ድንኳን አርክሷል፤+ ይህ ሰው* ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ የሚያነጻው ውኃ+ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው። አሁንም ከርኩሰቱ አልነጻም። 14  “‘አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፦ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ ቀድሞውኑም በድንኳኑ ውስጥ የነበረ ሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 15  መክደኛው ላዩ ላይ ያልታሰረ ክፍት ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።+ 16  በሰይፍ የተገደለን ወይም በድንን ወይም አፅምን ወይም መቃብርን የነካ በሜዳ ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።+ 17  ለረከሰውም ሰው ከተቃጠለው የኃጢአት መባ አመድ ላይ ወስደው በዕቃ በማድረግ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ይጨምሩበት። 18  ከዚያም ንጹሕ የሆነ ሰው+ ሂሶጵ+ ወስዶ ውኃው ውስጥ ከነከረ በኋላ በድንኳኑ፣ በዕቃዎቹ ሁሉ፣ እዚያ በነበረው ሰው* ሁሉና አፅሙን ወይም የተገደለውን ሰው አሊያም በድኑን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል። 19  ንጹሕ የሆነውም ሰው ውኃውን በረከሰው ሰው ላይ በሦስተኛው ቀንና በሰባተኛው ቀን ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ከኃጢአት ያነጻዋል፤+ ከዚያም ሰውየው ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ ማታም ላይ ንጹሕ ይሆናል። 20  “‘ሆኖም የረከሰውና ራሱን ያላነጻው ሰው የይሖዋን መቅደስ ስላረከሰ ይህ ሰው* ከጉባኤው መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ የሚያነጻው ውኃ ስላልተረጨበት ሰውየው ርኩስ ነው። 21  “‘ይህ ለእነሱ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል፦ የሚያነጻውን ውኃ+ የሚረጨው ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22  የረከሰው ሰው የሚነካው ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ ይህን የነካ ሰውም* እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የማንኛውንም ሰው ነፍስ አስከሬን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “አስከሬን ይኸውም የማንኛውንም የሞተ ሰው ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስም።”