መዝሙር 44:1-26

  • እርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

    • ‘ያዳንከን አንተ ነህ’ (7)

    • ‘እንደ እርድ በጎች ተቆጠርን’ (22)

    • “እኛን ለመርዳት ተነስ!” (26)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የቆሬ ልጆች መዝሙር።+ ማስኪል።* 44  አምላክ ሆይ፣ በገዛ ጆሯችን ሰምተናል፤ከረጅም ጊዜ በፊት፣በእነሱ ዘመን ያከናወንካቸውን ተግባሮች፣አባቶቻችን ተርከውልናል።+   በእጅህ ብሔራትን አባረርክ፤+በዚያም አባቶቻችንን አሰፈርክ።+ ብሔራትን ድል አድርገህ አባረርካቸው።+   ምድሪቱን የወረሱት በገዛ ሰይፋቸው አይደለም፤+ድል ያጎናጸፋቸውም የገዛ ክንዳቸው አይደለም።+ ከዚህ ይልቅ በእነሱ ደስ ስለተሰኘህ+ቀኝ እጅህ፣ ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አድርጓል።+   አምላክ ሆይ፣ አንተ ንጉሤ ነህ፤+ለያዕቆብ ፍጹም ድል* እዘዝ።*   በአንተ ኃይል ጠላቶቻችንን እንመክታለን፤+በእኛ ላይ የተነሱትን በስምህ እንረግጣለን።+   በቀስቴ አልታመንምና፤ሰይፌም ሊያድነኝ አይችልም።+   ከጠላቶቻችን ያዳንከን፣የሚጠሉንን ሰዎች ያዋረድካቸው አንተ ነህ።+   ቀኑን ሙሉ ለአምላክ ውዳሴ እናቀርባለን፤ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን። (ሴላ)   አሁን ግን ትተኸናል፤ ደግሞም አዋርደኸናል፤ከሠራዊታችንም ጋር አብረህ አትወጣም። 10  ከጠላታችን ፊት እንድንሸሽ ታደርገናለህ፤+የሚጠሉን ሰዎች የፈለጉትን ሁሉ ይወስዱብናል። 11  እንደ በግ እንዲበሉን ለጠላቶቻችን አሳልፈህ ሰጠኸን፤በብሔራት መካከል በተንከን።+ 12  ሕዝብህን በማይረባ ዋጋ ሸጥክ፤+ከሽያጩ ያገኘኸው ትርፍ የለም። 13  በጎረቤቶቻችን ዘንድ መሳለቂያ አደረግከን፤በዙሪያችን ያሉት ሁሉ እንዲያላግጡብንና እንዲዘብቱብን አደረግክ። 14  በብሔራት መካከል መቀለጃ እንድንሆን፣*ሕዝቦችም ራሳቸውን እንዲነቀንቁብን አደረግክ።+ 15  ቀኑን ሙሉ በኀፍረት ተውጫለሁ፤ውርደትም ተከናንቤአለሁ፤ 16  ይህም ከሚሳለቁና ከሚሳደቡ ሰዎች ድምፅ፣እንዲሁም ከሚበቀለን ጠላታችን የተነሳ ነው። 17  ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደርሷል፤ እኛ ግን አልረሳንህም፤ቃል ኪዳንህንም አላፈረስንም።+ 18  ልባችን አልሸፈተም፤እግራችንም ከመንገድህ አልወጣም። 19  ይሁንና ቀበሮዎች በሚኖሩበት ቦታ ሰባብረኸናል፤በድቅድቅ ጨለማም ሸፍነኸናል። 20  የአምላካችንን ስም ረስተን፣ወይም ወደ ባዕድ አምላክ ለመጸለይ እጃችንን ዘርግተን ከሆነ፣ 21  አምላክ ይህን አይደርስበትም? እሱ በልብ ውስጥ ያለውን ሚስጥር ያውቃል።+ 22  ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ሞትን እንጋፈጣለን፤እንደ እርድ በጎችም ተቆጠርን።+ 23  ይሖዋ ሆይ፣ ተነስ። ለምንስ ትተኛለህ?+ ንቃ! ለዘላለም አትጣለን።+ 24  ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? የደረሰብንን ጉስቁልናና ጭቆና የምትረሳው ለምንድን ነው? 25  ወደ አፈር ተጥለናልና፤*ሰውነታችን ከመሬት ጋር ተጣብቋል።+ 26  እኛን ለመርዳት ተነስ!+ ስለ ታማኝ ፍቅርህ ስትል ታደገን።*+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ታላቅ መዳን።”
ወይም “አጎናጽፍ።”
ቃል በቃል “መተረቻ እንድንሆን።”
ወይም “ነፍሳችን ወደ አፈር ተጥላለችና።”
ቃል በቃል “ዋጀን።”