መዝሙር 42:1-11

  • ታላቅ አዳኝ የሆነውን አምላክ ማወደስ

    • ርኤም ውኃ እንደምትጠማ አምላክን መጠማት (1, 2)

    • “ተስፋ የምቆርጠው ለምንድን ነው?” (5, 11)

    • “አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ” (5, 11)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የቆሬ ልጆች ማስኪል።*+ 42  ርኤም* ጅረቶችን እንደምትናፍቅ፣አምላክ ሆይ፣ አንተን እናፍቃለሁ።*   አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማሁ።*+ ወደ አምላክ የምሄደውና በፊቱ የምቀርበው መቼ ይሆን?+   እንባዬ ቀን ከሌት ምግብ ሆነኝ፤ሰዎች ቀኑን ሙሉ “አምላክህ የት አለ?” እያሉ ይሳለቁብኛል።+   እነዚህን ነገሮች አስታውሳለሁ፤ ነፍሴንም* አፈሳለሁ፤በአንድ ወቅት ከብዙ ሰዎች ጋር እጓዝ ነበር፤በእልልታና በምስጋና ድምፅ፣በዓል በሚያከብር ሕዝብ ድምፅ፣ከፊታቸው ሆኜ ወደ አምላክ ቤት በኩራት* እሄድ ነበር።+   ተስፋ የምቆርጠው* ለምንድን ነው?+ ውስጤ የሚረበሸው ለምንድን ነው? አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤+እሱን እንደ ታላቅ አዳኜ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና።+   አምላኬ ሆይ፣ ተስፋ ቆርጫለሁ።*+ ከዮርዳኖስ ምድርና ከሄርሞን አናት፣ከሚዛር ተራራ*የማስብህ ለዚህ ነው።+   በፏፏቴህ ድምፅ አማካኝነትጥልቁ ውኃ፣ ጥልቁን ውኃ ይጣራል። ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ ዋጠኝ።+   ይሖዋ በቀን ታማኝ ፍቅሩን ያሳየኛል፤እኔ ደግሞ በሌሊት ስለ እሱ እዘምራለሁ፤ ሕይወት ለሰጠኝ አምላክ ጸሎት አቀርባለሁ።+   ዓለቴ የሆነውን አምላክ እንዲህ እለዋለሁ፦ “ለምን ረሳኸኝ?+ ጠላት ከሚያደርስብኝ ግፍ የተነሳ በሐዘን ተውጬ ለምን እሄዳለሁ?”+ 10  ለእኔ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ሊገድሉኝ የሚሹ* ጠላቶቼ ይሳለቁብኛል፤ቀኑን ሙሉ “አምላክህ የት አለ?” እያሉ ይሳለቁብኛል።+ 11  ተስፋ የምቆርጠው* ለምንድን ነው? ውስጤ የሚረበሸው ለምንድን ነው? አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤+እሱን እንደ ታላቅ አዳኜና አምላኬ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።
ወይም “ነፍሴ አንተን ትናፍቃለች።”
ወይም “ነፍሴ ተጠማች።”
ወይም “በዝግታ።”
ወይም “ነፍሴ ተስፋ የምትቆርጠው።”
ወይም “ነፍሴ ተስፋ ቆርጣለች።”
ወይም “ከትንሹ ተራራ።”
“አጥንቶቼን ያደቀቁ ያህል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴ ተስፋ የምትቆርጠው።”