ሕዝቅኤል 7:1-27

  • ፍጻሜው ደርሷል (1-27)

    • “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥፋት” (5)

    • “ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ” (19)

    • ቤተ መቅደሱ ይረክሳል (22)

7  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “አንተ የሰው ልጅ ሆይ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ‘ፍጻሜ! በአራቱ የምድሪቱ ማዕዘናት ላይ ፍጻሜ መጥቷል።  አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል፤ ቁጣዬንም በአንቺ ላይ አወርዳለሁ፤ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ።  ዓይኔ አያዝንልሽም፤ ደግሞም አልራራልሽም፤+ የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁና፤ የፈጸምሻቸው አስጸያፊ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን መዘዝ ትቀምሻለሽ።+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’+  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ ጥፋት፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥፋት እየመጣ ነው!+  ፍጻሜ እየመጣ ነው፤ ፍጻሜው ይመጣል፤ በአንቺ ላይ ይነሳል።* እነሆ፣ ፍጻሜው እየመጣ ነው!  አንቺ በምድሪቱ የምትኖሪ፣ ተራሽ ደርሷል።* ጊዜው እየደረሰ ነው፤ ቀኑ ቀርቧል።+ በተራሮች ላይ የእልልታ ሳይሆን የሁከት ድምፅ ይሰማል።  “‘በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ አወርዳለሁ፤+ ንዴቴንም ሁሉ በአንቺ ላይ እወጣለሁ፤+ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ።  ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም።+ የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁ፤ የፈጸምሻቸው አስጸያፊ ድርጊቶች የሚያስከትሉብሽን መዘዝ ትቀምሻለሽ። እናንተም የምመታችሁ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።+ 10  “‘እነሆ ቀኑ! እነሆ ቀኑ እየመጣ ነው!+ ተራሽ ደርሷል፤* በትሩ አብቧል፤ እብሪትም አቆጥቁጧል። 11  ዓመፅ አድጎ የክፋት በትር ሆኗል።+ እነሱም ሆኑ ሀብታቸው ደግሞም ሕዝባቸውም ሆነ ታላቅነታቸው ይጠፋል። 12  ጊዜው ይደርሳል፤ ቀኑም ይመጣል። የሚገዛ አይደሰት፤ የሚሸጥም አይዘን፤ በሕዝባቸው ሁሉ ላይ ቁጣ ነዷልና።*+ 13  ሻጩ በሕይወት ቢተርፍ እንኳ ወደተሸጠው ነገር አይመለስም፤ ራእዩ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ነውና። ማንም አይመለስም፤ ከፈጸመውም በደል የተነሳ* ማንም ሕይወቱን ማትረፍ አይችልም። 14  “‘መለከት ነፍተዋል፤+ ሁሉም ቢዘጋጁም ወደ ውጊያ የሚሄድ አንድም ሰው የለም፤ ምክንያቱም ቁጣዬ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ነዷል።+ 15  በውጭ ሰይፍ፣+ በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ረሃብ አለ። በሜዳ ያለ ሁሉ በሰይፍ ይሞታል፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን ደግሞ ረሃብና ቸነፈር ይፈጃቸዋል።+ 16  አምልጠው መትረፍ የቻሉት ሁሉ ወደ ተራሮች ይሄዳሉ፤ እያንዳንዳቸውም በሸለቆ ውስጥ እንዳሉ ርግቦች በበደላቸው ይቃትታሉ።+ 17  እጃቸው ሁሉ ይዝላል፤ ጉልበታቸውም ሁሉ በውኃ ይርሳል።*+ 18  ማቅ ለብሰዋል፤+ ብርክም ይዟቸዋል። ሁሉም ኀፍረት ይከናነባሉ፤ ራስም ሁሉ ይመለጣል።*+ 19  “‘ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም አስጸያፊ ነገር ይሆንባቸዋል። በይሖዋ የቁጣ ቀን ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም።+ በልተው አይጠግቡም፤* ሆዳቸውንም አይሞሉም፤ በኃጢአት እንዲወድቁ እንቅፋት ሆኖባቸዋልና።* 20  በጌጦቻቸው ውበት ታበዩ፤ በእነዚህም* ጸያፍ የሆኑ ምስሎቻቸውን ይኸውም አስጸያፊ ጣዖቶቻቸውን ሠሩ።+ በዚህም ምክንያት ብሩንና ወርቁን ርኩስ ነገር አደርግባቸዋለሁ። 21  ባዕዳን የሆኑ ሰዎች እንዲዘርፉት፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ክፉ ሰዎችም እንዲበዘብዙት አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤* እነሱም ያረክሱታል። 22  “‘ፊቴን ከእነሱ አዞራለሁ፤+ እነሱም የተሰወረውን ቦታዬን* ያረክሳሉ፤ ዘራፊዎችም ወደ እሷ ይገባሉ፤ ደግሞም ያረክሷታል።+ 23  “‘ምድሪቱ ነፍስ ግድያ በሚያስከትል የተዛባ ፍርድ ስለተሞላች፣+ ከተማዋም በዓመፅ ስለተሞላች+ ሰንሰለት*+ ሥራ። 24  ከብሔራት መካከል እጅግ የከፉትን አመጣለሁ፤+ እነሱም ቤቶቻቸውን ይወርሳሉ፤+ የብርቱዎቹንም ኩራት አጠፋለሁ፤ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ።+ 25  መከራ ሲመጣባቸው ሰላምን ይሻሉ፤ ሆኖም ሰላም አይኖርም።+ 26  በጥፋት ላይ ጥፋት ይመጣል፤ በወሬም ላይ ወሬ ይናፈሳል፤ ሰዎችም ከነቢይ ራእይ ይሻሉ፤+ ሆኖም ሕግ* ከካህን፣ ምክርም ከሽማግሌዎች ዘንድ ይጠፋል።+ 27  ንጉሡ ያለቅሳል፤+ አለቃውም በተስፋ መቁረጥ* ስሜት ይዋጣል፤ የምድሪቱም ሕዝብ ከመሸበሩ የተነሳ እጁ ይንቀጠቀጣል። እንደ መንገዳቸው አደርግባቸዋለሁ፤ ደግሞም እነሱ እንደፈረዱት እፈርድባቸዋለሁ። እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ይነቃል።”
“የአበባው ጉንጉን መጥቷል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“የአበባው ጉንጉን መጥቷል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በሁሉም ላይ ጥፋት ስለሚመጣ የሚገዛም ሆነ የሚሸጥ የሚያገኘው ጥቅም እንደሌለ ያመለክታል።
“በበደሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከፍርሃት የተነሳ ሽንታቸውን እንደሚለቁ ያመለክታል።
በሐዘን ምክንያት ፀጉራቸውን እንደሚላጩ ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳቸው በልታ አትጠግብም።”
ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመለክታል።
ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎቻቸውን ያመለክታል።
ጣዖቶች ለመሥራት የተጠቀሙባቸውን ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመለክታል።
የይሖዋን መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
በግዞት ሲወሰዱ የሚታሰሩበትን ሰንሰለት ያመለክታል።
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ወይም “በባዶነት።”