ሕዝቅኤል 32:1-32

  • ስለ ፈርዖንና ስለ ግብፅ የተነገረ ሙሾ (1-16)

  • ግብፅ ካልተገረዙት ጋር ትቀበራለች (17-32)

32  በ12ኛውም ዓመት፣ በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ስለ ግብፅ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አውርድ፤* እንዲህም በለው፦‘በብሔራት መካከል እንደ ብርቱ ደቦል አንበሳ ነበርክ፤አሁን ግን አክትሞልሃል። አንተ እንደ ግዙፍ የባሕር ፍጥረት ነበርክ፤+ በወንዞችህ ውስጥ ትንቦጫረቅ፣በእግርህም ውኃውን ታደፈርስ፣ ወንዞቹንም * ታቆሽሽ ነበር።’   ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በብዙ ብሔራት ጉባኤ አማካኝነት መረቤን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤እነሱም በማጥመጃ መረቤ ጎትተው ያወጡሃል።   በምድር ላይ እተውሃለሁ፤አውላላ ሜዳ ላይ እጥልሃለሁ። የሰማይ ወፎች ሁሉ በአንተ ላይ እንዲሰፍሩ አደርጋለሁ፤በመላው ምድር የሚገኙትን የዱር እንስሳትም በአንተ አጠግባለሁ።+   ሥጋህን በተራሮች ላይ እጥላለሁ፤ከሬሳህ በተረፉት ነገሮችም ሸለቆዎቹን እሞላለሁ።+   ምድሪቷ እስከ ተራሮች ድረስ በሚፈሰው ደምህ እንድትርስ አደርጋለሁ፤ጅረቶችም በደምህ ይሞላሉ።’*   ‘አንተም በምትጠፋበት ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤ ከዋክብታቸውንም አጨልማለሁ። ፀሐይን በደመና እሸፍናለሁ፤ጨረቃም ብርሃኗን አትፈነጥቅም።+   በሰማያት ያሉትን ብርሃን ሰጪ አካላት ሁሉ ከአንተ የተነሳ አጨልማቸዋለሁ፤ምድርህንም ጨለማ አለብሳለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።   ‘ከአንተ የተማረኩትን ወደ ሌሎች ብሔራት ይኸውም ወደማታውቃቸው አገሮች በምወስድበት ጊዜ+የብዙ ሰዎችን ልብ አስጨንቃለሁ። 10  ብዙ ሕዝቦች እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ሰይፌንም በፊታቸው ሳወዛውዝ ከአንተ የተነሳ ንጉሦቻቸው በፍርሃት ይርዳሉ። አንተ በምትወድቅበት ቀንእያንዳንዳቸው ለሕይወታቸው በመፍራት ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣሉ።’ 11  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል።+ 12  ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብህ በኃያላን ተዋጊዎች ሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ሁሉም ከብሔራት መካከል እጅግ ጨካኞች ናቸው።+ እነሱም የግብፅን ኩራት ያንኮታኩታሉ፤ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝቧም ሁሉ ይደመሰሳል።+ 13  ከብቶቿን ሁሉ ከብዙ ውኃዎቿ አጠገብ አጠፋለሁ፤+የሰው እግርም ሆነ የከብቶች ኮቴ ዳግመኛ አያደፈርሳቸውም።’+ 14  ‘በዚያን ጊዜ ውኃዎቻቸውን አጠራለሁ፤ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 15  ‘ግብፅን ባድማና ወና በማድረግ ምድሪቱን የሞላውን ነገር ሁሉ በማስወግድበት ጊዜ፣+ነዋሪዎቿንም ሁሉ በምመታበት ጊዜ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 16  ይህ ሙሾ ነው፤ ሰዎችም ያንጎራጉሩታል፤የብሔራት ሴቶች ልጆች ያንጎራጉሩታል። በግብፅና ስፍር ቁጥር በሌለው ሕዝቧ ሁሉ የተነሳ ያንጎራጉሩታል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” 17  ከዚያም በ12ኛው ዓመት፣ ከወሩም በ15ኛው ቀን፣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 18  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ስፍር ቁጥር ለሌለው የግብፅ ሕዝብ ዋይ ዋይ በል፤ እሷንና የኃያላን ብሔራትን ሴቶች ልጆች ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው። 19  “‘በውበት ማንን ትበልጣለህ? ወደ ታች ውረድ፤ ካልተገረዙትም ጋር ተጋደም!’ 20  “‘በሰይፍ በታረዱት መካከል ይወድቃሉ።+ እሷ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እሷንም ሆነ ስፍር ቁጥር የሌለውን ሕዝቧን ሁሉ ጎትቱ። 21  “‘ኃያላኑ ተዋጊዎች እሱንና ረዳቶቹን ከጥልቅ መቃብር* ውስጥ ያነጋግሯቸዋል። እነሱ በእርግጥ ወደ ታች ይወርዳሉ፤ ደግሞም በሰይፍ ታርደው፣ እንዳልተገረዙት ሰዎች ይጋደማሉ። 22  አሦር ከመላ ጉባኤዋ ጋር በዚያ ትገኛለች። መቃብሮቻቸው በእሱ ዙሪያ ናቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀዋል።+ 23  መቃብሮቿ በጥልቅ ጉድጓድ* ውስጥ ይገኛሉ፤ ጉባኤዋም በመቃብሯ ዙሪያ አለ፤ ሁሉም በሰይፍ ተመትተው ወድቀዋል፤ ምክንያቱም በሕያዋን ምድር ሽብር ፈጥረው ነበር። 24  “‘ኤላም+ ስፍር ቁጥር ከሌለው ሕዝቧ ሁሉ ጋር በመቃብሯ ዙሪያ ትገኛለች፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀዋል። በሕያዋን ምድር ሽብር የፈጠሩት እነዚህ ሰዎች ሳይገረዙ ከምድር በታች ወርደዋል። ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት ጋር ኀፍረታቸውን ይከናነባሉ። 25  በመቃብሯ ዙሪያ ከሚገኘው ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝቧ ሁሉ ጋር፣ በታረዱት መካከል መኝታ አዘጋጅተውላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የታረዱ ናቸው፤ ምክንያቱም በሕያዋን ምድር ሽብር ፈጥረው ነበር፤ ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት ጋር ኀፍረታቸውን ይከናነባሉ። እሱ በታረዱት መካከል እንዲቀመጥ ተደርጓል። 26  “‘መሼቅና ቱባል+ እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝባቸው ሁሉ* በዚያ ይገኛሉ። መቃብሮቻቸው* በዙሪያው ናቸው። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተወጉ ናቸው፤ ምክንያቱም በሕያዋን ምድር ሽብር ፈጥረዋል። 27  እነሱ፣ ከወደቁትና ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር ወደ መቃብር* ከወረዱት ያልተገረዙ ኃያላን ተዋጊዎች ጋር ይጋደሙ የለም? ሰይፎቻቸውን ከራሳቸው በታች ያደርጋሉ፤* በኃጢአታቸውም የተነሳ የሚደርስባቸው ቅጣት በአጥንታቸው ላይ ይሆናል፤ ምክንያቱም እነዚህ ኃያላን ተዋጊዎች የሕያዋንን ምድር አሸብረዋል። 28  አንተ ግን ባልተገረዙት መካከል ትደቅቃለህ፤ በሰይፍ ከታረዱትም ጋር ትጋደማለህ። 29  “‘ኤዶም፣+ ነገሥታቷና አለቆቿ ሁሉ በዚያ ይገኛሉ፤ ኃያላን ሆነው ሳለ በሰይፍ በታረዱት መካከል ተጋድመዋል፤ እነሱም ካልተገረዙትና+ ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት ጋር ይጋደማሉ። 30  “‘የሰሜን ገዢዎች* በሙሉ ከሲዶናውያን+ ሁሉ ጋር በዚያ ይገኛሉ፤ ኃይላቸው ሽብር የፈጠረ ቢሆንም ከታረዱት ሰዎች ጋር ኀፍረት ተከናንበው ወርደዋል። በሰይፍ ከታረዱት ጋር ሳይገረዙ ይጋደማሉ፤ ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱትም ጋር ኀፍረታቸውን ይከናነባሉ። 31  “‘ፈርዖን እነዚህን ሁሉ ነገሮች ይመለከታል፤ ደግሞም ስፍር ቁጥር በሌለው ሕዝቡ ላይ ከደረሰው ነገር ሁሉ ይጽናናል፤+ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ በሰይፍ ይታረዳሉ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 32  “‘በሕያዋን ምድር ሽብር ስለፈጠረ ፈርዖንና ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝቡ ሁሉ በሰይፍ ከታረዱት፣ ካልተገረዙት ሰዎች ጋር ለማረፍ ይጋደማሉ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወንዞቻቸውንም።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማ።”
ቃል በቃል “የጅረቶቹም ወለል ከአንተ (በአንተ) ይሞላሉ።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “መቃብር።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “መቃብር።”
ቃል በቃል “ሕዝቧ ሁሉ።”
ቃል በቃል “መቃብሮቿ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ተዋጊዎች ወታደራዊ ክብር እንዲያገኙ ሲባል ከሰይፋቸው ጋር መቀበራቸውን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ወይም “መቃብር።”
ወይም “መሪዎች።”
ወይም “መቃብር።”