ሕዝቅኤል 19:1-14

  • ስለ እስራኤል አለቆች የተነገረ ሙሾ (1-14)

19  “ስለ እስራኤል አለቆች ሙሾ አውጣ፤* 2  እንዲህም በል፦‘እናትህ ምን ነበረች? በአንበሶች መካከል ያለች እንስት አንበሳ ነበረች። በብርቱ ደቦል አንበሶች መሃል ተኛች፤ ግልገሎቿንም በዚያ አሳደገች።  3  ከግልገሎቿ መካከል አንዱን ተንከባክባ አሳደገችው፤ እሱም ብርቱ ደቦል አንበሳ ሆነ።+ አድኖ መብላት ተማረ፤ሰዎችንም እንኳ ሳይቀር በላ።  4  ብሔራት ስለ እሱ ሰሙ፤ ጉድጓዳቸው ውስጥ ገብቶም ያዙት፤በስናግም እየጎተቱ ወደ ግብፅ ምድር አመጡት።+  5  እሷም በትዕግሥት ስትጠባበቅ ከቆየች በኋላ የመመለስ ተስፋ እንደሌለው ተገነዘበች። በመሆኑም ከግልገሎቿ መካከል ሌላውን ወስዳ እንደ ብርቱ ደቦል አንበሳ አድርጋ ላከችው።  6  እሱም በአንበሶች መካከል ይጎማለል ጀመር፤ ብርቱ ደቦል አንበሳም ሆነ። አድኖ መብላት ተማረ፤ ሰዎችንም እንኳ ሳይቀር በላ።+  7  በማይደፈሩት ማማዎቻቸው መካከል አደባ፤ ከተሞቻቸውንም አወደመ፤ከዚህም የተነሳ ግሳቱ ወና በሆነችው ምድር ላይ አስተጋባ።+  8  በዙሪያው ባሉ ግዛቶች ያሉ ብሔራት መረባቸውን በእሱ ላይ ለመዘርጋት ተነሱበት፤እሱም ጉድጓዳቸው ውስጥ ገብቶ ተያዘ።  9  በስናግ ጎትተው በእንስሳት ጎጆ ውስጥ በመክተት ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት። ከዚያ በኋላ ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ እንዳይሰማ በዚያ አሰሩት። 10  እናትህ በውኃዎች አጠገብ እንደተተከለ፣ በደምህ ውስጥ ያለ የወይን ተክል* ነበረች።+ ከውኃው ብዛት የተነሳ ፍሬ አፈራች፤ ብዙ ቅርንጫፎችም ነበሯት። 11  ለገዢዎች በትረ መንግሥት የሚሆኑ ጠንካራ ቅርንጫፎች* አወጣች። አድጋ ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ረጅም ሆነች፤ደግሞም ከርዝመቷና ከቅጠሎቿ ብዛት የተነሳ ጎልታ ታየች። 12  ሆኖም በቁጣ ተነቀለች፤+ ወደ ምድርም ተጣለች፤የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀው። ጠንካራ ቅርንጫፎቿ ተሰብረው ደረቁ፤+ እሳትም በላቸው።+ 13  በዚህ ጊዜ በምድረ በዳ፣ውኃ በሌለበት ደረቅ ምድር ተተከለች።+ 14  እሳት ከቅርንጫፎቿ* ወጥቶ ቀንበጦቿንና ፍሬዋን በላ፤በእሷም ላይ አንድም ጠንካራ ቅርንጫፍ፣ ለገዢዎችም የሚሆን በትረ መንግሥት አልተረፈም።+ “‘ይህ ሙሾ ነው፤ ሙሾ ሆኖም ያገለግላል።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማ።”
“በወይን እርሻህ ውስጥ እንዳለ የወይን ተክል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘንጎች።”
ወይም “እሳት ከዘንጎቿ።”