ሕዝቅኤል 17:1-24

  • የሁለቱ ንስሮችና የወይን ተክሉ እንቆቅልሽ (1-21)

  • ለጋ የሆነው ቀንበጥ የሚያምር አርዘ ሊባኖስ ሆነ (22-24)

17  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ስለ እስራኤል ቤት እንቆቅልሽና ምሳሌ ተናገር።+  እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ትላልቅ ክንፎችና ረጃጅም ማርገብገቢያዎች ያሉት እንዲሁም መላ አካሉ ዥጉርጉር በሆኑ ላባዎች የተሸፈነው ታላቁ ንስር+ ወደ ሊባኖስ+ መጥቶ የአርዘ ሊባኖስን ጫፍ ያዘ።+  አናቱ ላይ ያለውን ቀንበጥ ቀጥፎ ወደ ነጋዴዎች* ምድር አመጣው፤ በነጋዴዎችም ከተማ ተከለው።+  ከዚያም ከምድሪቱ ዘር የተወሰነውን ወስዶ+ ለም በሆነ መሬት ላይ ዘራው። እንደ ሪጋ* ዛፍ ብዙ ውኃ ባለበት ቦታ አጠገብ ተከለው።  በመሆኑም ዘሩ በቀለ፤ አጭርና የተንሰራፋ እንዲሁም ወደ ራሱ አቅጣጫ የበቀሉ ቅጠሎች ያሉት የወይን ተክል ሆነ፤+ ሥሮቹም ከበታቹ አደጉ። በዚህ ሁኔታ የወይን ተክል ሆነ፤ ቀንበጦችና ቅርንጫፎችም አወጣ።+  “‘“ደግሞም ትላልቅ ክንፎች ያሉትና የክንፎቹ ላባዎች ረጃጅም የሆኑ ሌላ ታላቅ ንስር መጣ።+ ከዚያም ይህ የወይን ተክል ሥሮቹን ከተተከለበት የአትክልት መደብ አሻግሮ በታላቅ ጉጉት ወደ እሱ ዘረጋ፤ ውኃ ያጠጣውም ዘንድ ቅርንጫፎቹን ወደ እሱ ሰደደ።+  ቅርንጫፎችን እንዲያወጣና ፍሬ እንዲያፈራ እንዲሁም ያማረ የወይን ተክል እንዲሆን ብዙ ውኃ ባለበት አቅራቢያ መልካም መሬት ላይ ተተክሎ ነበር።”’+  “እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ያድግ ይሆን? ሰው ሥሮቹን ነቅሎ አይጥልም?+ ፍሬው እንዲበሰብስ አያደርግም? ቀንበጦቹስ እንዲጠወልጉ አያደርግም?+ የወይኑ ተክል በጣም ስለሚደርቅ ከሥሩ ለመንቀል ብርቱ ክንድም ሆነ ብዙ ሰው አያስፈልግም። 10  ተነቅሎ በሌላ ቦታ ቢተከልስ ያድግ ይሆን? የምሥራቅ ነፋስ ሲነፍስበት ሙሉ በሙሉ አይደርቅም? በበቀለበት የአትክልት መደብ ላይ ይደርቃል።”’” 11  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 12  “እባክህ፣ ለዓመፀኛው ቤት ይህን ተናገር፦ ‘የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አትገነዘቡም?’ እንዲህ በል፦ ‘እነሆ፣ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ንጉሥዋንና መኳንንቷን ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ይዟቸው ተመለሰ።+ 13  በተጨማሪም ከንጉሣውያን ዘር አንዱን ወስዶ+ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በመሐላም ቃል አስገባው።+ ከዚያም የምድሪቱን ታላላቅ ሰዎች ወሰደ፤+ 14  ይህም መንግሥቲቱ ዝቅ እንድትልና ማንሰራራት እንዳትችል እንዲሁም የእሱን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ብቻ እንድትኖር ለማድረግ ነው።+ 15  ንጉሡ ግን በመጨረሻ ፈረሶችና+ ብዙ ሠራዊት እንዲልኩለት መልእክተኞቹን ወደ ግብፅ በመስደድ+ በእሱ ላይ ዓመፀ።+ ታዲያ ይሳካለት ይሆን? እነዚህን ነገሮች ያደረገው ከቅጣት ያመልጣል? ቃል ኪዳኑንስ አፍርሶ ማምለጥ ይችላል?’+ 16  “‘“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ “እሱን ንጉሥ* አድርጎ የሾመው ንጉሥ* በሚኖርበት ቦታ ይኸውም በባቢሎን ይሞታል፤ ይህ ሰው መሐላውን አቃሎበታል፤ ቃል ኪዳኑንም አፍርሶበታል።+ 17  ብዙ ሕይወት* ለማጥፋት የአፈር ቁልል በሚደለደልበትና ለከበባ የሚያገለግል ግንብ በሚሠራበት ጊዜ የፈርዖን ታላቅ ሠራዊትና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወታደሮች ሊረዱት አይችሉም።+ 18  እሱ መሐላውን አቃሏል፤ ቃል ኪዳኑንም አፍርሷል። ቃል ቢገባለትም* እንኳ እነዚህን ነገሮች ሁሉ አድርጓል፤ ስለዚህ ፈጽሞ አያመልጥም።”’ 19  “‘በመሆኑም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕያውነቴ እምላለሁ፤ መሐላዬን መናቁና ቃል ኪዳኔን ማፍረሱ የሚያስከትልበትን መዘዝ በራሱ ላይ አመጣበታለሁ።+ 20  መረቤን በላዩ ላይ እዘረጋለሁ፤ እሱም በማጥመጃ መረቤ ይያዛል።+ ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ በእኔ ላይ ክህደት ስለፈጸመ በዚያ እፋረደዋለሁ።+ 21  ከወታደሮቹ መካከል የሸሹት ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በሕይወት የተረፉትም በየአቅጣጫው* ይበታተናሉ።+ በዚህ ጊዜም እኔ ይሖዋ ራሴ እንደተናገርኩ ታውቃላችሁ።”’+ 22  “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከረጅሙ አርዘ ሊባኖስ ጫፍ ላይ ቀንበጥ+ ቀጥፌ እተክለዋለሁ፤ ከቀንበጦቹም ጫፍ ላይ ለጋ የሆነውን ቀጥፌ+ ረጅምና ግዙፍ በሆነ ተራራ ላይ እኔ ራሴ እተክለዋለሁ።+ 23  ረጅም በሆነ የእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፤ ቅርንጫፎቹም ያድጋሉ፤ ፍሬም ያፈራል፤ ደግሞም የሚያምር አርዘ ሊባኖስ ይሆናል። በሥሩም የወፍ ዓይነቶች ሁሉ ይኖራሉ፤ በቅጠሎቹም ጥላ ሥር ያርፋሉ። 24  የዱር ዛፎች ሁሉ፣ ከፍ ያለውን ዛፍ ዝቅ ዝቅ ያደረግኩት፣ ዝቅ ያለውን ዛፍ ደግሞ ከፍ ከፍ ያደረግኩት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ፤+ ለምለሙን ዛፍ አድርቄአለሁ፤ ደረቁም ዛፍ እንዲለመልም አድርጌአለሁ።+ እኔ ይሖዋ ራሴ ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አድርጌአለሁ።”’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከነአን።”
የአኻያ ዛፍ የሚመስል።
ሴዴቅያስን ያመለክታል።
ናቡከደነጾርን ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “እጁን ቢሰጠውም።”
ቃል በቃል “ወደ ነፋስ ሁሉ።”