ሕዝቅኤል 14:1-23
14 ከእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።+
2 ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
3 “የሰው ልጅ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን* ለመከተል ቆርጠው ተነስተዋል፤ ሰዎች ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርግ የማሰናከያ ድንጋይ አስቀምጠዋል። ታዲያ እኔን እንዲጠይቁኝ ልፈቅድላቸው ይገባል?+
4 እንግዲህ ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንድ እስራኤላዊ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቹን ለመከተል ቆርጦ ተነስቶና ሰዎች ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርግ የማሰናከያ ድንጋይ አስቀምጦ አንድን ነቢይ ለመጠየቅ ቢመጣ እኔ ይሖዋ፣ እንደ አስጸያፊ ጣዖቶቹ ብዛት በተገቢው መንገድ እመልስለታለሁ።
5 የእስራኤልን ቤት ሰዎች ልብ አሸብራለሁና፤* ምክንያቱም ሁሉም ከእኔ ርቀዋል፤ እንዲሁም አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን ተከትለዋል።”’+
6 “ስለሆነም የእስራኤልን ቤት ሰዎች እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ተመለሱ፤ አስጸያፊ ከሆኑት ጣዖቶቻችሁ ራቁ፤ ቀፋፊ ከሆኑት ልማዶቻችሁ ሁሉ ፊታችሁን መልሱ።+
7 ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ከእኔ በመለየት አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቹን ለመከተል ቆርጦ ተነስቶና ሰዎች ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርግ የማሰናከያ ድንጋይ አስቀምጦ የእኔን ነቢይ ለመጠየቅ ቢመጣ+ እኔ ይሖዋ፣ አዎ እኔ ራሴ እመልስለታለሁ።
8 ፊቴን ወደዚህ ሰው አዞራለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’
9 “‘ይሁንና ነቢዩ ቢሞኝና ምላሽ ቢሰጥ፣ ያንን ነቢይ ያሞኘሁት እኔ ይሖዋ ነኝ።+ ከዚያም እጄን በእሱ ላይ ዘርግቼ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ።
10 የፈጸሙት በደል የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ይሸከማሉ፤ ነቢዩን ሊጠይቅ የመጣው ሰው በደል ነቢዩ ከፈጸመው በደል ጋር አንድ ዓይነት ይሆናል፤
11 ይህም የሚሆነው የእስራኤል ቤት ሰዎች ከእኔ ርቀው እንዳይባዝኑና በሚፈጽሙት በደል ሁሉ ራሳቸውን ከማርከስ እንዲቆጠቡ ነው። እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”
12 የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
13 “የሰው ልጅ ሆይ፣ አንድ አገር ታማኝ ሳይሆን ቀርቶ በእኔ ላይ ኃጢአት ቢፈጽም እጄን በእሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ የምግብ አቅርቦቱም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፤*+ ረሃብም እሰድበታለሁ+ እንዲሁም ሰውንም ሆነ እንስሳን ከዚያ አጠፋለሁ።”+
14 “‘እነዚህ ሦስት ሰዎች ይኸውም ኖኅ፣+ ዳንኤልና+ ኢዮብ+ በዚያ ቢኖሩ እንኳ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን* ብቻ ነው’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”
15 “‘ወይም አደገኛ የዱር አራዊትን ወደዚያ አገር ብሰድ፣ በአገሩ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ቢፈጁና* አገሩ በዱር አራዊቱ የተነሳ ማንም ሰው የማያልፍበት ወና እንዲሆን ቢያደርጉ፣+
16 በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘እነዚህ ሦስት ሰዎች በዚያ ቢኖሩ እንኳ ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው፤ አገሩም ባድማ ይሆናል።’”
17 “‘ወይም ደግሞ በአገሩ ላይ ሰይፍ ባመጣና+ “በአገሩ መካከል ሰይፍ ይለፍ” ብል፣ በአገሩም ላይ ያለውን ሰውም ሆነ እንስሳ ባጠፋ፣+
18 እነዚህ ሦስት ሰዎች በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው።’”
19 “‘ወይም በአገሩ ላይ ቸነፈር ብሰድና+ ሰውንም ሆነ እንስሳን ለማጥፋት ደም በማፍሰስ በአገሩ ላይ ቁጣዬን ባወርድ፣
20 ኖኅ፣+ ዳንኤልና+ ኢዮብ+ በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን* ብቻ ነው።’”+
21 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሰውንም ሆነ እንስሳን ለማጥፋት+ በኢየሩሳሌም ላይ አራት ቅጣቶቼን*+ ይኸውም ሰይፍን፣ ረሃብን፣ አደገኛ የዱር አራዊትንና ቸነፈርን በምሰድበት ጊዜ+ ምንኛ የከፋ ይሆን!
22 ሆኖም በዚያ የሚቀሩ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በሕይወት ይተርፋሉ፤ ደግሞም ከዚያ ይወሰዳሉ።+ ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ መንገዳቸውንና ሥራቸውንም በምታዩበት ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ ካመጣሁት ጥፋት፣ በእሷም ላይ ካደረስኩት ነገር ሁሉ በእርግጥ ትጽናናላችሁ።’”
23 “‘መንገዳቸውንና ሥራቸውን ስታዩ ያጽናኗችኋል፤ በእሷም ላይ ላደርገው የሚገባኝን ነገር ያደረግኩት ያለምክንያት አለመሆኑን ትገነዘባላችሁ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
^ ቃል በቃል “የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዛለሁና።”
^ ቃል በቃል “የዳቦ በትሮቹንም እሰብራለሁ።” ዳቦ ለማስቀመጥ የሚያገለግሉ በትሮችን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ ወይም “ነፍሳቸውን።”
^ ወይም “ልጆች ቢጨርሱና።”
^ ወይም “ነፍሳቸውን።”
^ ወይም “አደገኛ የሆኑትን አራት የፍርድ እርምጃዎቼን።”