ሕዝቅኤል 12:1-28

  • የስደት ጉዞው በምሳሌያዊ መንገድ ተገለጸ (1-20)

    • የስደተኛ ጓዝ (1-7)

    • አለቃው በጨለማ ይወጣል (8-16)

    • የጭንቀት ምግብ፣ የፍርሃት ውኃ (17-20)

  • አሳሳች የሆነው አባባል ውሸት መሆኑ ተረጋገጠ (21-28)

    • “ከተናገርኩት ቃል ውስጥ የሚዘገይ አይኖርም” (28)

12  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የምትኖረው በዓመፀኛ ሕዝብ መካከል ነው። እነሱ የሚያዩበት ዓይን አላቸው፣ ግን አያዩም፤ የሚሰሙበት ጆሮ አላቸው፣ ነገር ግን አይሰሙም፤+ እነሱ ዓመፀኛ ሕዝብ ናቸውና።+  የሰው ልጅ ሆይ፣ አንተ ግን በግዞት እንደሚወሰድ ሰው ለመሄድ ጓዝህን አዘጋጅ። ከዚያም እነሱ እያዩህ በቀን ጉዞ ጀምር። እነሱ እያዩህ ከቤትህ ተነስተህ ወደ ሌላ ቦታ እንደ ግዞተኛ ሂድ። ዓመፀኛ ሕዝብ ቢሆኑም እንኳ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ይገባቸው ይሆናል።  በቀን እነሱ እያዩህ በግዞት እንደሚወሰድ ሰው ለመሄድ ጓዝህን አዘጋጅተህ አውጣ፤ ከዚያም ምሽት ላይ እነሱ እያዩህ በግዞት እንደሚወሰድ ሰው ውጣ።+  “እነሱ እያዩ ግንቡን ነድለህ በዚያ በኩል ጓዝህን ተሸክመህ ውጣ።+  እነሱ እያዩ ጓዝህን በትከሻህ ተሸክመህ በጨለማ ይዘኸው ውጣ። መሬቱን እንዳታይ ፊትህን ሸፍን፤ ለእስራኤል ቤት ምልክት አደርግሃለሁና።”+  እኔም ልክ እንደታዘዝኩት አደረግኩ። ቀን ላይ በግዞት እንደሚሄድ ሰው ጓዝ፣ ጓዜን ጠቅልዬ አወጣሁ፤ ከዚያም ምሽት ላይ ግንቡን በእጄ ነደልኩት። ሲጨልምም ዓይናቸው እያየ ጓዜን በትከሻዬ ተሸክሜ ወጣሁ።  ጠዋት ላይ የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ዓመፀኛ ሕዝብ የሆኑት የእስራኤል ቤት ሰዎች ‘ምን እያደረግክ ነው?’ ብለው አልጠየቁህም? 10  እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ቃል የተነገረው በኢየሩሳሌም ለሚኖረው አለቃና+ በከተማዋ ውስጥ ለሚኖረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ነው።”’ 11  “እንዲህ በል፦ ‘እኔ ለእናንተ ምልክት ነኝ።+ ልክ እኔ እንዳደረግኩት በእነሱም ላይ እንዲሁ ይደረግባቸዋል። ተማርከው በግዞት ይወሰዳሉ።+ 12  በመካከላቸው ያለው አለቃ በጨለማ ጓዙን በትከሻው ተሸክሞ ይወጣል። ግንቡን ይነድልና ጓዙን ተሸክሞ በዚያ በኩል ይወጣል።+ መሬቱን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።’ 13  መረቤን በእሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ እሱም በማጥመጃ መረቤ ይያዛል።+ ከዚያም ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ምድሪቱን ግን አያይም፤ በዚያም ይሞታል።+ 14  በእሱም ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ይኸውም ረዳቶቹንና ወታደሮቹን በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤+ እነሱንም ለማሳደድ ሰይፍ እመዛለሁ።+ 15  በብሔራት መካከል ስበትናቸውና በአገሮችም መካከል ስዘራቸው እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። 16  ይሁንና በሚሄዱባቸው ብሔራት መካከል አስጸያፊ ስለሆኑት ልማዶቻቸው ሁሉ እንዲናገሩ ከእነሱ መካከል ጥቂት ሰዎች ከሰይፍ፣ ከረሃብና ከቸነፈር እንዲተርፉ አደርጋለሁ፤ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።” 17  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 18  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ምግብህን እየተንቀጠቀጥክ ብላ፤ ውኃህንም በስጋትና በጭንቀት ጠጣ።+ 19  ለምድሪቱም ሕዝብ እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ምድር ላሉት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ ይላል፦ “ምግባቸውን በጭንቀት ይበላሉ፤ ውኃቸውንም በፍርሃት ይጠጣሉ፤ በምድሪቱ ላይ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ከሚፈጽሙት ዓመፅ የተነሳ ምድራቸው ፈጽማ ባድማ ትሆናለችና።+ 20  ሰው ይኖርባቸው የነበሩት ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም ወና ትሆናለች፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’”+ 21  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 22  “የሰው ልጅ ሆይ፣ በእስራኤል ምድር ‘ዘመኑ አልፏል፤ ራእይም ሁሉ መና ቀርቷል’ የምትሉት ይህ አባባል ምንድን ነው?+ 23  ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህን አባባል አስቀራለሁ፤ በእስራኤልም ምድር ይህን አባባል ዳግመኛ አይጠቀሙበትም።”’ ሆኖም እንዲህ በላቸው፦ ‘ዘመኑ ቀርቧል፤+ እያንዳንዱም ራእይ ይፈጸማል።’ 24  በእስራኤል ቤት መካከል ከእንግዲህ የሐሰት ራእይ ወይም አሳሳች* ሟርት አይኖርምና።+ 25  ‘“እኔ ይሖዋ እናገራለሁና። የተናገርኩት ቃል ሁሉ ከእንግዲህ ሳይዘገይ ይፈጸማል።+ ዓመፀኛው ቤት ሆይ፣ በእናንተ ዘመን+ እኔ እናገራለሁ፤ የተናገርኩትንም እፈጽማለሁ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።’” 26  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 27  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የእስራኤል ሰዎች* ‘እሱ የሚያየው ራእይ የሚፈጸመው ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው፤ ትንቢት የሚናገረውም በጣም ሩቅ ስለሆነ ጊዜ ነው’ ይላሉ።+ 28  ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ከተናገርኩት ቃል ውስጥ የሚዘገይ አይኖርም፤ የተናገርኩት ቃል ሁሉ ይፈጸማል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አታላይ።”
ቃል በቃል “ቤት።”