ሕዝቅኤል 11:1-25

  • ክፉዎቹ አለቆች ተወገዙ (1-13)

    • ከተማዋ በድስት ተመሰለች (3-12)

  • ተመልሰው እንደሚቋቋሙ ቃል ተገባላቸው (14-21)

    • “አዲስ መንፈስ” ይሰጣቸዋል (19)

  • የአምላክ ክብር ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ሄደ (22, 23)

  • ሕዝቅኤል በራእይ ወደ ከለዳውያን ምድር ተመለሰ (24, 25)

11  መንፈስም ወደ ላይ አንስቶ በምሥራቅ ትይዩ ወዳለው የይሖዋ ቤት የምሥራቅ በር+ አመጣኝ። በዚያም በበሩ መግቢያ ላይ 25 ሰዎች አየሁ፤ ከእነሱም መካከል የሕዝቡ አለቆች+ የሆኑት የአዙር ልጅ ያአዛንያህና የበናያህ ልጅ ጰላጥያህ ነበሩ። 2  ከዚያም አምላክ እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ክፋትን የሚያቅዱና በዚህች ከተማ* መጥፎ ምክር የሚመክሩ ናቸው። 3  እነሱ ‘አሁን ቤት የምንሠራበት ጊዜ አይደለም?+ ከተማዋ* ድስት ናት፤+ እኛ ደግሞ ሥጋ* ነን’ ይላሉ። 4  “ስለዚህ በእነሱ ላይ ትንቢት ተናገር። የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር።”+ 5  ከዚያም የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ መጣ፤+ እንዲህም አለኝ፦ “እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ቤት ሆይ፣ የተናገራችሁት ነገር ትክክል ነው፤ የምታስቡትን ነገር* አውቃለሁ። 6  በዚህች ከተማ ብዙዎች እንዲሞቱ አድርጋችኋል፤ ጎዳናዎቿንም በሙታን ሞልታችኋል።”’”+ 7  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ በከተማዋ ዙሪያ የጣላችኋቸው ሬሳዎች፣ እነሱ ሥጋው ናቸው፤ ከተማዋ ደግሞ ድስቱ ናት።+ እናንተ ግን ከውስጧ ትወሰዳላችሁ።’” 8  “‘ሰይፍን ፈርታችኋል፤+ እኔም ሰይፍ አመጣባችኋለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 9  ‘ከእሷ አውጥቼ ለባዕዳን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የፍርድ እርምጃም እወስድባችኋለሁ።+ 10  በሰይፍ ትወድቃላችሁ።+ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።+ 11  ከተማዋ ድስት አትሆንላችሁም፤ እናንተም በውስጧ እንዳለ ሥጋ አትሆኑም፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ 12  እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ። በሥርዓቴ አልተመላለሳችሁምና፤ ድንጋጌዎቼንም አላከበራችሁም፤+ ይልቁንም በዙሪያችሁ ያሉትን ብሔራት ድንጋጌዎች ተከተላችሁ።’”+ 13  ትንቢት ተናግሬ እንደጨረስኩ የበናያህ ልጅ ጰላጥያህ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ወዮ! የእስራኤልን ቀሪዎች ፈጽመህ ልታጠፋ ነው?” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮኽኩ።+ 14  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 15  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ወንድሞችህን ይኸውም የመቤዠት መብት ያላቸውን ወንድሞችህንና የእስራኤልን ቤት ሁሉ ‘ከይሖዋ ራቁ። ምድሪቱ የእኛ ናት፤ ለእኛ ርስት ሆና ተሰጥታለች’ ብለዋቸዋል። 16  ስለዚህ እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሩቅ ወዳሉ ብሔራት በግዞት እንዲወሰዱና በብዙ አገሮች መካከል እንዲበተኑ ባደርግም+ በሄዱባቸው አገሮች ውስጥ ለጥቂት ጊዜ መቅደስ እሆናቸዋለሁ።”’+ 17  “ስለዚህ እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ደግሞም ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች አመጣችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ።+ 18  እነሱም ወደዚያ ይመለሳሉ፤ በላይዋም ላይ ያሉትን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉና ጸያፍ የሆኑ ልማዶች ሁሉ ያስወግዳሉ።+ 19  እኔም አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤+ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አኖራለሁ፤+ ድንጋይ የሆነውንም ልብ ከሰውነታቸው አውጥቼ+ የሥጋ ልብ* እሰጣቸዋለሁ፤+ 20  ይህም ደንቦቼን አክብረው እንዲመላለሱ እንዲሁም ድንጋጌዎቼን እንዲጠብቁና እንዲታዘዙ ነው። በዚህ ጊዜ እነሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”’ 21  “‘“ሆኖም አስጸያፊ ነገሮቻቸውንና ጸያፍ የሆኑ ልማዶቻቸውን አጥብቀው ለመከተል በልባቸው ቆርጠው የተነሱትን በተመለከተ፣ መንገዳቸው የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።’” 22  በዚህ ጊዜ ኪሩቦቹ ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘረጉ፤ መንኮራኩሮቹም* በአጠገባቸው ነበሩ፤+ የእስራኤል አምላክ ክብርም በላያቸው ነበር።+ 23  ከዚያም የይሖዋ ክብር+ ከከተማዋ ተነስቶ ወደ ላይ ወጣ፤ ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራም ላይ ቆመ።+ 24  ከዚያም መንፈስ፣ በአምላክ ኃይል* አማካኝነት በተሰጠኝ ራእይ ወደ ላይ አነሳኝ፤ ደግሞም በከለዳውያን ምድር ወዳሉት ግዞተኞች አመጣኝ። ከዚያም ያየሁት ራእይ ከእኔ ተለየ። 25  እኔም ይሖዋ ያሳየኝን ነገር ሁሉ በግዞት ላሉት ሰዎች መናገር ጀመርኩ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከተማ ላይ።”
ቃል በቃል “እሷ።” የኢየሩሳሌምን ከተማ የሚያመለክት ሲሆን አይሁዳውያን በእሷ ውስጥ ጥበቃ እናገኛለን ብለው ያስቡ ነበር።
በውስጡ በጥሩ ሁኔታ የተቀመጠን ሥጋ ያመለክታል።
ወይም “በመንፈሳችሁ የመጡትን ነገሮች።”
ለአምላክ አመራር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥን ልብ ያመለክታል።
የሠረገላ ተሽከርካሪ እግር።
ቃል በቃል “መንፈስ።”