1 ጢሞቴዎስ 5:1-25

5  ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው። ከዚህ ይልቅ እንደ አባት በአክብሮት ምከረው፤ ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች፣  አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።  በእርግጥ መበለት የሆኑትን መበለቶች አክብራቸው።  ሆኖም አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ካሏት እነዚህ ልጆች በመጀመሪያ በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅን እንዲሁም ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው የሚገባቸውን ብድራት መክፈልን ይማሩ፤ ምክንያቱም ይህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው።  ይሁን እንጂ በእርግጥ መበለት የሆነችና ምንም የሌላት ሴት ተስፋዋን በአምላክ ላይ ትጥላለች እንዲሁም ያለማሰለስ ሌሊትና ቀን ምልጃና ጸሎት ታቀርባለች።  የሥጋ ፍላጎቷን ለማርካት ያደረች መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት።  ስለዚህ ከነቀፋ ነፃ መሆን ይችሉ ዘንድ እነዚህን ትእዛዛት መስጠትህን ቀጥል።  በእርግጥም አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።  ከስልሳ ዓመት ያላነሰ ዕድሜ ያላት መበለት በመዝገብ ላይ እንድትጻፍ አድርግ፤ የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ 10  እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ማንኛውንም ጥሩ ሥራ በትጋት በማከናወን በመልካም ተግባር የተመሠከረላት መሆን አለባት። 11  በዕድሜ ያልገፉት መበለቶች ግን መዝገብ ላይ መጻፍ የለባቸውም፤ ምክንያቱም የፆታ ስሜታቸው አይሎ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ ማግባት ይፈልጋሉ፤ 12  በዚህም መጀመሪያ ላይ የገቡትን የእምነት ቃል ችላ ስለሚሉ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ። 13  ከዚህም በተጨማሪ ሥራ መፍታትን ይማራሉ እንዲሁም በየቤቱ ይዞራሉ፤ ሥራ መፍታትም ብቻ ሳይሆን ማውራት የማይገባቸውን ነገር እያወሩ ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ። 14  ስለዚህ በዕድሜ ያልገፉ መበለቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩና ተቃዋሚው ሊነቅፍበት የሚችል ነገር እንዲያገኝ ከማድረግ እንዲቆጠቡ እፈልጋለሁ። 15  እንዲያውም ቀደም ሲል አንዳንዶቹ ሰይጣንን ለመከተል ዘወር ብለዋል። 16  አንዲት አማኝ የሆነች ሴት፣ መበለት የሆኑ ዘመዶች ቢኖሯት እሷ ትርዳቸው እንጂ ሸክሙ ጉባኤው ላይ እንዲሆን አታድርግ። በዚህ መንገድ ጉባኤው በእርግጥ መበለት የሆኑትን መርዳት ይችላል። 17  በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር እንደሚገባቸው ተደርገው መታየት ይኖርባቸዋል። 18  ምክንያቱም የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር”፤ እንዲሁም “ለሠራተኛው ደሞዙ ይገባዋል” ይላል። 19  በሁለት ወይም በሦስት ምሥክሮች ማስረጃ ካልሆነ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብን ክስ አትቀበል። 20  ሌሎቹም እንዲፈሩ ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። 21  እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ያለ በቂ ማስረጃ ከመፍረድ እንድትቆጠብና ማንኛውንም ነገር በአድልዎ እንዳታደርግ በአምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት አጥብቄ አዝሃለሁ። 22  በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል፤ እንዲሁም በሌሎች ኃጢአት ተካፋይ አትሁን፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ። 23  ከእንግዲህ ውኃ አትጠጣ፤ ከዚህ ይልቅ ለሆድህና በተደጋጋሚ ለሚነሳብህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ። 24  የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት በይፋ የታወቀ ስለሚሆን ወዲያውኑ ፍርድ ያስከትላል፤ ይሁንና የሌሎቹም ሰዎች ኃጢአት ቢሆን ዘግየት ብሎ መገለጡ አይቀርም። 25  በተመሳሳይም መልካም ሥራዎች በይፋ የታወቁ ናቸው፤ በይፋ ያልታወቁትም ቢሆኑ ተደብቀው ሊቀሩ አይችሉም።

የግርጌ ማስታወሻዎች