1 ዮሐንስ 1:1-10

1  ከመጀመሪያ የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዓይናችን ያየነውን፣ በትኩረት የተመለከትነውንና በእጃችን የዳሰስነውን የሕይወትን ቃል በተመለከተ እንጽፍላችኋለን፤  (አዎ፣ ይህ ሕይወት እንዲገለጥ ተደርጓል፤ እኛም አይተናል፣ ደግሞም እየመሠከርን ነው፤ እንዲሁም ከአብ ጋር የነበረውንና ለእኛ እንዲገለጥ የተደረገውን የዘላለም ሕይወት ለእናንተ እየነገርናችሁ ነው፤)  እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እየነገርናችሁ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ኅብረታችን ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።  እነዚህን ነገሮች እየጻፍንላችሁ ያለነውም ደስታችን የተሟላ እንዲሆን ነው።  ከእሱ የሰማነውና ለእናንተ የምናስታውቀው መልእክትም ይህ ነው:- አምላክ ብርሃን ነው፤ በእሱ ዘንድም ፈጽሞ ጨለማ የለም።  “ከእሱ ጋር ኅብረት አለን” ብለን እየተናገርን በጨለማ መመላለሳችንን የምንቀጥል ከሆነ እየዋሸን ነው፣ እውነትንም ተግባራዊ እያደረግን አይደለም።  ይሁን እንጂ እሱ ራሱ በብርሃን እንዳለ ሁሉ እኛም በብርሃን የምንመላለስ ከሆነ እርስ በርሳችን ኅብረት አለን፤ እንዲሁም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።  “ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያሳሳትን ነው፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።  ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፣ እንዲሁም ከክፋት ሁሉ ያነጻናል። 10  “ኃጢአት አልሠራንም” ብለን የምንናገር ከሆነ እሱን ውሸታም እያደረግነው ነው፤ ቃሉም በውስጣችን የለም።

የግርጌ ማስታወሻዎች