1 ተሰሎንቄ 1:1-10

1  አባት ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነት ላለው የተሰሎንቄ ሰዎች ጉባኤ፣ ከጳውሎስና ከስልዋኖስ* እንዲሁም ከጢሞቴዎስ የተላከ ደብዳቤ:- ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  በጸሎታችን ስለ ሁላችሁ ስንጠቅስ ሁልጊዜ አምላክን እናመሰግናለን፤  ምክንያቱም የእምነት ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁንና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላችሁ ተስፋ የተነሳ የምታሳዩትን ጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።  በአምላክ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እሱ እንደመረጣችሁ እናውቃለን፤  ምክንያቱም የሰበክንላችሁ ምሥራች በመካከላችሁ የተገለጠው በቃል ብቻ ሳይሆን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም በጽኑ እምነት ነው። ደግሞም ለጥቅማችሁ ስንል ለእናንተ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን ታውቃላችሁ፤  በተጨማሪም ብዙ መከራ ቢደርስባችሁም ቃሉን ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ደስታ ስለተቀበላችሁት የእኛንና የጌታን ምሳሌ ኮርጃችኋል፤  ስለዚህ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙ አማኞች ሁሉ ምሳሌ ሆናችኋል።  የይሖዋ ቃል ከእናንተ ወጥቶ የተሰማው በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ላይ ያላችሁ እምነት በሌሎች ቦታዎችም ሁሉ ተሰራጭቷል፤ ስለዚህ እኛ ምንም መናገር አያስፈልገንም።  ምክንያቱም መጀመሪያ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደተገናኘን እንዲሁም ሕያው የሆነውንና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ጣዖቶቻችሁን በመተው እንዴት ወደ አምላክ እንደተመለሳችሁ እነሱ ራሳቸው ሁልጊዜ ይናገራሉ፤ 10  በተጨማሪም ወደ አምላክ የተመለሳችሁት ከሞት ያስነሳውንና ከሚመጣው ቁጣ የሚያድነንን የልጁን ይኸውም የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት ለመጠባበቅ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

1ተሰ 1:1 * ወይም፣ “ሲላስ።”