ዮሐንስ 10:1-42

10  “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው።  በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው።  በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ፤ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል።  የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።  እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።”  ኢየሱስ ይህን ንጽጽር ነገራቸው፤ ሆኖም እየነገራቸው የነበረው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው አልገባቸውም።  ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የበጎቹ በር እኔ ነኝ።  አስመሳይ ሆነው በእኔ ስም የመጡ ሁሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም።  በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፣ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። 10  ሌባው ለመስረቅ፣ ለመግደልና ለማጥፋት ካልሆነ በቀር ለሌላ አይመጣም። እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው። 11  እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል። 12  እረኛ ያልሆነና በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ተቀጣሪ ሠራተኛ ተኩላ ሲመጣ ሲያይ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፤ ተኩላውም በጎቹን ይነጥቃል እንዲሁም ይበታትናል፤ 13  ሠራተኛው እንዲህ የሚያደርገው ተቀጣሪ ስለሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። 14  እኔ በጣም ጥሩ እረኛ ነኝ፤ በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤ 15  ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ነው፤ ነፍሴንም ለበጎቹ ስል አሳልፌ እሰጣለሁ። 16  “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። 17  አብ የሚወደኝ ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም መልሼ አገኛት ዘንድ ነፍሴን አሳልፌ እሰጣለሁ። 18  በራሴ ተነሳስቼ አሳልፌ እሰጣታለሁ እንጂ ማንም ሰው ከእኔ አልወሰዳትም። ነፍሴን አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመቀበልም ሥልጣን አለኝ። ይህን በተመለከተ ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” 19  ከዚህ ንግግር የተነሳ በአይሁዳውያን መካከል እንደገና ክፍፍል ተፈጠረ። 20  ብዙዎቹም “ይህ ሰው ጋኔን አለበት፤ እብድ ነው። ለምን ትሰሙታላችሁ?” ይሉ ነበር። 21  ሌሎቹ ደግሞ “ጋኔን የያዘው ሰው እንዲህ አይናገርም። ጋኔን የዓይነ ስውራንን ዓይን ሊከፍት አይችልም፤ ይችላል እንዴ?” ይሉ ነበር። 22  በዚያ ወቅት በኢየሩሳሌም የመታደስ በዓል* ይከበር ነበር። ጊዜውም ክረምት ነበር፤ 23  ኢየሱስም በቤተ መቅደሱ በሚገኘውና መጠለያ ባለው የሰለሞን መተላለፊያ ውስጥ እየሄደ ነበር። 24  በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን ከበውት “እስከ መቼ ድረስ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንክ በግልጽ ንገረን” ይሉት ጀመር። 25  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም። በአባቴ ስም እየሠራኋቸው ያሉት ነገሮች ስለ እኔ ይመሠክራሉ። 26  ሆኖም እናንተ ከበጎቼ መካከል ስላልሆናችሁ አታምኑም። 27  በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል። 28  የዘላለም ሕይወትም እሰጣቸዋለሁ፤ መቼም ቢሆን ከቶ ጥፋት አይደርስባቸውም፤ ከእጄ የሚነጥቃቸውም የለም። 29  አባቴ የሰጠኝ በጎች ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጣሉ፤ እነሱንም ከአባቴ እጅ ሊነጥቃቸው የሚችል የለም። 30  እኔና አብ አንድ ነን።” 31  አይሁዳውያኑም ሊወግሩት እንደገና ድንጋይ አነሱ። 32  ኢየሱስም መልሶ “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎች አሳየኋችሁ። ታዲያ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በየትኛው የተነሳ ነው?” አላቸው። 33  አይሁዳውያኑም “እኛ የምንወግርህ ስለ መልካም ሥራህ ሳይሆን አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ ራስህን አምላክ በማድረግ አምላክን ስለተዳፈርክ ነው” ሲሉ መለሱለት። 34  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “በሕጋችሁ ላይ ‘“እናንተ አማልክት ናችሁ” አልኩ’ ተብሎ ተጽፎ የለም? 35  የአምላክ ቃል የተቃወማቸውን እሱ ‘አማልክት’ ብሎ ከጠራቸውና ቅዱስ መጽሐፉ ሊሻር የማይችል ከሆነ 36  አብ የቀደሰኝንና ወደ ዓለም የላከኝን እኔን፣ የአምላክ ልጅ ነኝ ስላልኩ ‘አምላክን ትዳፈራለህ’ ትሉኛላችሁ? 37  እኔ የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ካልሆንኩ አትመኑኝ። 38  የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለውና እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁና ይህን ይበልጥ እያወቃችሁ እንድትሄዱ ሥራዬን እመኑ።” 39  በዚህ ጊዜ እንደገና ሊይዙት ሞከሩ፤ እሱ ግን አምልጧቸው ሄደ። 40  ከዚያም ዮሐንስ በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ቦታ ዳግመኛ ሄደ፤ በዚያም ቆየ። 41  ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው “እርግጥ ዮሐንስ አንድም ተአምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ሆኖም ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር” ይሉ ጀመር። 42  በዚያም ብዙዎች በእሱ አመኑ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዮሐ 10:22 * ወይም፣ “ቤተ መቅደሱ ለአምላክ የተወሰነበት በዓል (ሃኑካ)።”