ዕብራውያን 12:1-29

12  እንግዲህ እጅግ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ፤  የምንሮጠውም የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት በመመልከት ነው። እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት* ላይ እስከመሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።  እንግዲህ እንዳትደክሙና በነፍሳችሁ እንዳትዝሉ የራሳቸውን ጥቅም የሚጻረር ነገር የሚያደርጉ ኃጢአተኞች የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን ተቃውሞ በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ።  እናንተ ከዚያ ኃጢአት ጋር እያደረጋችሁ ባላችሁት ትግል ደማችሁ እስኪፈስ ድረስ ገና አልታገላችሁም፤  ከዚህም በተጨማሪ እንደ ልጆች አድርጎ የሚመክራችሁን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ረስታችኋል:- “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት፤ በሚያርምህም ጊዜ አትታክት፤  ይሖዋ የሚወደውን ይገሥጻል፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይገርፋል።”  መጽናታችሁ እንደ ተግሣጽ ሆኖ ያገለግላችኋል። አምላክ የያዛችሁ እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው። ለመሆኑ አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?  ሆኖም ሁሉም የሚቀበሉትን ተግሣጽ ካልተቀበላችሁ ዲቃላዎች ናችሁ እንጂ ልጆች አይደላችሁም።  ከዚህም በላይ የሚገሥጹን ሥጋዊ አባቶች ነበሩን፤ እኛም እናከብራቸው ነበር። ታዲያ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አባት ለሆነው እንዴት አብልጠን ልንታዘዝ አይገባንም? 10  ምክንያቱም እነሱ መልካም መስሎ በታያቸው መንገድ ለጥቂት ጊዜ ይገሥጹን ነበር፤ እሱ ግን ከቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል። 11  እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም፤ በኋላ ግን በእሱ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች ሰላማዊ ፍሬ ይኸውም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። 12  ስለዚህ የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤ 13  አንካሳ የሆነው እንዲፈወስ እንጂ ከቦታው ወጥቶ እንዳይናጋ ዘወትር ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ። 14  ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ፤ ቅድስናንም ፈልጉ፣ ያለ ቅድስና ማንም ሰው ጌታን ማየት አይችልም፤ 15  ማንም የአምላክን ጸጋ እንዳያጣ እንዲሁም መርዛማ ሥር በቅሎ ችግር እንዳይፈጥርና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ፤ 16  በተጨማሪም ሴሰኛ የሆነ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። 17  ምክንያቱም በኋላ በረከቱን ለመውረስ በፈለገም ጊዜ እንደተከለከለ ታውቃላችሁ፤ የአባቱን ሐሳብ ለማስቀየር እያለቀሰ ብርቱ ጥረት ቢያደርግም እንኳ አልተሳካለትም። 18  እናንተ ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደተቀጣጠለው ተራራ፣ ወደ ጥቁር ደመናው፣ ወደ ድቅድቅ ጨለማውና ወደ አውሎ ነፋሱ አልቀረባችሁም፤ 19  እንዲሁም ወደ መለከት ድምፅና ቃል ያሰማ ወደነበረው ድምፅ አልቀረባችሁም፤ ሕዝቡ ይህን ድምፅ ሲሰሙ ሌላ ተጨማሪ ቃል እንዳይነገራቸው ተማጽነዋል። 20  ምክንያቱም “እንስሳ ተራራውን ከነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ ሊሸከሙት የሚችሉት አልነበረም። 21  በተጨማሪም በዚያ ይታይ የነበረው ነገር በጣም አስፈሪ ስለነበረ ሙሴ “ፈራሁ፣ ተንቀጠቀጥኩም” ሲል ተናግሯል። 22  ሆኖም እናንተ ወደ ጽዮን ተራራና የሕያው አምላክ ከተማ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ቀርባችኋል፤ እንዲሁም ወደ አእላፋት* መላእክት 23  ጠቅላላ ጉባኤ፣ በሰማያት ወደተመዘገበው ወደ በኩራት ጉባኤ፣ የሁሉ ፈራጅ ወደሆነው አምላክ፣ ፍጽምና እንዲያገኙ ወደተደረጉት ጻድቃን መንፈሳዊ ሕይወት፣ 24  የአዲስ ቃል ኪዳን አስታራቂ ወደሆነው ወደ ኢየሱስና ከአቤል ደም በተሻለ ሁኔታ ወደሚናገረው ወደተረጨው ደም ቀርባችኋል። 25  እየተናገረ ያለውን እሱን ከመስማት ወደኋላ እንዳትሉ ተጠንቀቁ። ምክንያቱም በምድር ላይ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው የነበረውን ከመስማት ወደኋላ ያሉት ሰዎች ካላመለጡ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረውን እሱን ከመስማት ዞር ብንል እንዴት እናመልጣለን? 26  በዚያን ጊዜ ድምፁ ምድርን አናውጦ ነበር፤ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ” ሲል ቃል ገብቷል። 27  እንግዲህ “አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚለው አባባል የማይናወጡ ነገሮች ጸንተው እንዲኖሩ የሚናወጡ ይኸውም የተፈጠሩ ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ያመለክታል። 28  ስለዚህ እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ ከጸጋው ጥቅም ማግኘታችንን እንቀጥል፤ ይህም በጸጋው አማካኝነት በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት ለአምላክ ተቀባይነት ባለው መንገድ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ነው።  29  ምክንያቱም አምላካችን የሚባላ እሳት ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዕብ 12:2 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 6ኛውን ርዕስ ተመልከት።
ዕብ 12:22 * ወይም፣ “አሥር ሺህዎች።”