ቲቶ 1:1-16

1  የአምላክ ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ አገልግሎቱ ከአምላክ ምርጦች እምነትና ከእውነት ትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማ ሲሆን ይህ እውነት ለአምላክ ከማደር ጋር የሚጣጣም ነው፤  ይህ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት በሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው፤  ይሁንና አዳኛችን በሆነው አምላክ ትእዛዝ በአደራ በተሰጠኝ የስብከቱ ሥራ አማካኝነት ራሱ በወሰነው ጊዜ ቃሉ ይፋ እንዲሆን አደረገ፤  የጋራችን በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለቲቶ:- አባት ከሆነው አምላክና አዳኛችን ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን።  አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከሉትን ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው፤  ይኸውም ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም በስድነት ወይም በሥርዓት አልበኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ካለ እንድትሾም ነው።  ምክንያቱም የበላይ ተመልካች በአምላክ የተሾመ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን ከክስ ነፃ መሆን አለበት፤ በራሱ ሐሳብ የሚመራ፣ ግልፍተኛ፣ እየሰከረ የሚበጠብጥ፣ የሚማታና አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚስገበገብ ሊሆን አይገባም፤  ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ጻድቅ፣ ታማኝ፣ ራሱን የሚገዛ  እንዲሁም ጤናማ በሆነው ትምህርት አጥብቆ መምከርም ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መገሠጽ ይችል ዘንድ ከማስተማር ጥበቡ ጋር በተያያዘ የታመነውን ቃል አጥብቆ የሚይዝ ሊሆን ይገባል። 10  ምክንያቱም ሥርዓት አልበኞች የሆኑ፣ በከንቱ የሚለፈልፉና የሰዎችን አእምሮ የሚያስቱ በተለይም ግርዘትን በጥብቅ የሚከተሉ ብዙ ሰዎች አሉ። 11  እነዚህ ሰዎች አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ትምህርት እያስተማሩ የመላውን ቤተሰብ እምነት እያፈረሱ ስለሆነ አፋቸውን ማዘጋት ያስፈልጋል። 12  ከእነሱ መካከል አንዱ፣ የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ሁልጊዜ የሚዋሹ፣ ክፉ አውሬዎችና ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሏል። 13  ይህ ምሥክርነት እውነት ነው። ለዚህም ሲባል እነሱን አጥብቀህ መገሠጽህን ቀጥል፤ ይኸውም በእምነት ጤናሞች እንዲሆኑ 14  እንዲሁም ለአይሁዳውያን ተረቶችና ከእውነት የራቁ ሰዎች ለሚሰጡት ትእዛዝ ትኩረት እንዳይሰጡ ነው። 15  ንጹሕ ለሆኑ ሰዎች ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው። ለረከሱና እምነት ለሌላቸው ሰዎች ግን ምንም ንጹሕ ነገር የለም፤ ከዚህ ይልቅ አእምሯቸውም ሆነ ሕሊናቸው የረከሰ ነው። 16  አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል፤ ምክንያቱም አስጸያፊና የማይታዘዙ እንዲሁም ለማንኛውም ዓይነት መልካም ሥራ የማይበቁ ናቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች