ሮም 9:1-33

9  የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን እውነትን እናገራለሁ፤ ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር እየዋሸሁ አይደለሁም፤  ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ።  በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ የተረገምኩ ሆኜ ከክርስቶስ ብለይ በወደድኩ ነበር።  እነሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸው፣ ክብር ያገኙት፣ ቃል ኪዳን የተገባላቸው፣ ሕግ የተሰጣቸው፣ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ያገኙትና ተስፋ የተሰጣቸው እነሱ ናቸው፤  አባቶችም የእነሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነሱ ነው። የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም የተባረከ ይሁን። አሜን።  ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ በእርግጥ “እስራኤል” አይደለምና።  በተጨማሪም የአብርሃም ዘር ስለሆኑ ሁሉም ልጆች ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “‘የአንተ ዘር’ ተብሎ የሚጠራው የሚመጣው በይስሐቅ በኩል ነው” ተብሎ ተጽፏል።  ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤ በተስፋው ልጆች የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።  የተስፋው ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ይላልና። 10  ይሁንና ተስፋው የተሰጠው በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ርብቃ ከአንዱ ሰው ይኸውም ከአባታችን ከይስሐቅ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ጭምር ነው፤ 11  ምርጫውን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ በሥራ ሳይሆን በጠሪው ላይ የተመካ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ልጆቹ ከመወለዳቸውና ጥሩም ሆነ ክፉ ከማድረጋቸው በፊት 12  ርብቃ “ታላቁ የታናሹ ባሪያ ይሆናል” ተብሎ ተነግሯት ነበር። 13  ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ፤ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 14  እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም! 15  ምክንያቱም ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ” ብሎታል። 16  ስለዚህ ይህ የተመካው በፈለገ ወይም በሮጠ ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ ነው። 17  ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ፈርዖን ሲናገር “በሕይወት እንድትቆይ ያደረግኩት በአንተ አማካኝነት ኃይሌን ለማሳየትና ስሜ በምድር ሁሉ ላይ እንዲታወቅ ለማድረግ ነው” ይላል። 18  ስለዚህ አምላክ የፈለገውን ይምራል፤ የፈለገውን ደግሞ ግትር እንዲሆን ይፈቅዳል። 19  በመሆኑም “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ በሰዎች ላይ ለምን ስህተት ይፈላልጋል? ለመሆኑ በግልጽ የተቀመጠውን ፈቃዱን ማን ተቃውሞ ያውቃል?” ትለኝ ይሆናል። 20  ለመሆኑ እንዲህ ብለህ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ? አንድ ዕቃ ቅርጽ አውጥቶ የሠራውን ሰው “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋል? 21  ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው አታውቅም? 22  አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ? 23  ይህን ያደረገው አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለጠግነት ለመግለጥ ቢሆንስ? 24  የምሕረት ዕቃዎቹም ከአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም የጠራን እኛ ነን። 25  ይህም በሆሴዕ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው:- “ሕዝቤ ያልሆኑትን ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደች’ ብዬ እጠራለሁ፤ 26  ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም በዚያ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።” 27  ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል:- “የእስራኤል ልጆች ቁጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም እንኳ የሚድኑት ቀሪዎች ናቸው። 28  ምክንያቱም ይሖዋ በምድር የሚኖሩትን ይፋረዳል፤ ይህንም ሳይዘገይ ይፈጽመዋል።” 29  ደግሞም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ነበር፤ ገሞራንም እንድንመስል በተደረግን ነበር።” 30  እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? አሕዛብ ጽድቅን ባይከታተሉም እንኳ ጽድቅን ይኸውም በእምነት አማካኝነት የሚገኘውን ጽድቅ አገኙ፤ 31  ሆኖም እስራኤል የጽድቅን ሕግ ቢከታተልም ግቡ ላይ አልደረሰም፤ ይኸውም ሕጉን አልፈጸመም። 32  ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በእምነት ሳይሆን በሥራ የሚገኝ እንደሆነ አድርጎ ስለተከታተለው ነው። ስለዚህ “በማሰናከያ ድንጋይ” ተሰናከሉ፤ 33  ይህም “እነሆ፣ በጽዮን የማሰናከያ ድንጋይና የሚያደናቅፍ ዐለት አኖራለሁ፤ እምነቱን በእሱ ላይ የሚጥል ግን ለኀፍረት አይዳረግም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች