ሮም 10:1-21

10  ወንድሞች፣  ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ አምላክን የምማጸነው እንዲድኑ ነው።  ምክንያቱም በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁ፤  የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም።  እምነቱን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ መጽደቅ ይችል ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው።  ሙሴ በሕጉ የሚገኘውን ጽድቅ የፈጸመ ሰው ባገኘው ጽድቅ በሕይወት እንደሚኖር ጽፏል።  ሆኖም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በተመለከተ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል:- “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤  ወይም ‘ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሳት ነው።”  ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው”፤ ይህም እኛ የምንሰብከው የእምነት “ቃል” ነው።  ‘በአፍህ ውስጥ ያለውን ይህን ቃል’ ይኸውም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህ። 10  ምክንያቱም አንድ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል። 11  ቅዱስ መጽሐፉ “እምነቱን በእሱ ላይ የሚጥል ሁሉ አያፍርም” ይላል። 12  የሁሉም ጌታ አንድ ስለሆነ በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ እሱም የሚለምኑትን ሁሉ ባለጠጋ ያደርጋል። 13  “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” 14  ይሁንና ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል? ደግሞስ የሚሰብክላቸው ሳይኖር እንዴት ይሰማሉ? 15  ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 16  ሆኖም ምሥራቹን የታዘዙት ሁሉም አይደሉም። ኢሳይያስ “ይሖዋ ሆይ፣ እኛ የተናገርነውን ቃል ማን አመነ?” ብሏልና። 17  ስለዚህ እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው። ቃሉ የሚሰማው ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር ሰው ሲኖር ነው። 18  ነገር ግን ሳይሰሙ ቀርተው ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ። በእርግጥ ሰምተዋል፤ “ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ወጣ፤ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻዎች ተሰማ” ተብሏልና። 19  ይሁንና እስራኤላውያን ሳያውቁ ቀርተው ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ። ሙሴ አስቀድሞ “እናንተን፣ ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናችኋለሁ፤ ማስተዋል በጎደለው ሕዝብም አማካኝነት ክፉኛ አስቆጣችኋለሁ” ብሏል። 20  ሆኖም ኢሳይያስ በድፍረት “ያልፈለጉኝ ሰዎች አገኙኝ፤ እኔን ለማግኘት ላልጠየቁ ሰዎችም ተገለጥኩ” ብሏል። 21  እስራኤልን በተመለከተ ግን “ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ” ብሏል።

የግርጌ ማስታወሻዎች