ራእይ 14:1-20

14  እኔም አየሁ፤ እነሆ፣ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሟል፤ ከእሱም ጋር የእሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።  ከሰማይም እንደ ብዙ ውኃዎችና እንደ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁትም ድምፅ በገናቸውን እየተጫወቱ በበገና ራሳቸውን እንደሚያጅቡ ዘማሪዎች ዓይነት ድምፅ ነው።  እነሱም በዙፋኑ ፊት እንዲሁም በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና በሽማግሌዎቹ ፊት እንደ አዲስ መዝሙር ያለ መዝሙር እየዘመሩ ነበር፤ ከምድር ከተዋጁት ከአንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ በስተቀር ማንም ይህን መዝሙር ጠንቅቆ ሊያውቀው አልቻለም።  ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱት እነዚህ ናቸው፤ እንዲያውም ድንግሎች ናቸው። ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። እነዚህ ለአምላክና ለበጉ እንደ በኩራት ሆነው ከሰዎች መካከል ተዋጅተዋል፤  በአፋቸውም ውሸት የሚባል ነገር አልተገኘም፤ ምንም ዓይነት እንከን የሌለባቸው ናቸው።  ሌላም መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ እንዲሁም ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ ልክ እንደ አስደሳች ዜና የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር፤  በታላቅ ድምፅም “አምላክን ፍሩ፣ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም እሱ ፍርድ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል፤ በመሆኑም ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ” አለ።  ሌላም ሁለተኛ መልአክ “ወደቀች! ብሔራት ሁሉ የዝሙቷን የቁጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገችው ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!” እያለ ተከተለው።  ሌላም ሦስተኛ መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው:- “ማንም አውሬውንና ምስሉን የሚያመልክና በግምባሩ ወይም በእጁ ላይ ምልክት የሚቀበል ከሆነ 10  እሱም ሳይበረዝ ወደ ቁጣው ጽዋ ከተቀዳው የአምላክ የቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፤ እንዲሁም በቅዱሳኑ መላእክት ፊትና በበጉ ፊት በእሳትና በድኝ ይሠቃያል። 11  የሥቃያቸውም ጭስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል፤ ደግሞም አውሬውንና ምስሉን የሚያመልኩ እንዲሁም የስሙን ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ምንም እረፍት አይኖራቸውም። 12  የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን እምነት አጥብቀው የሚከተሉ ቅዱሳን፣ ጽናት የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው።” 13  ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ:- “ይህን ጻፍ:- ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከጌታ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው የሚሞቱ ሙታን ደስተኞች ናቸው። መንፈስም፣ አዎ፣ ያከናወኑት ሥራ ወዲያው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ይረፉ ይላል።” 14  እኔም አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ደመና ነበር፤ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጧል፤ እሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቷል፣ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዟል። 15  ሌላም መልአክ ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው “የአጨዳው ሰዓት ስለደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ ምክንያቱም የምድር መከር ደርሷል” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 16  በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች። 17  አሁንም ሌላ መልአክ በሰማይ ካለው ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ ወጣ፤ እሱም እንዲሁ ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር። 18  አሁንም ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጣ፤ እሱም በእሳቱ ላይ ሥልጣን ነበረው። በታላቅ ድምፅ ጮኾም ስለታም ማጭድ የያዘውን መልአክ “የምድሪቱ የወይን ፍሬዎች ስለበሰሉ ስለታም ማጭድህን ስደድና የምድርን የወይን ዘለላዎች ሰብስብ” አለው። 19  መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር በመስደድ የምድርን ወይን ሰበሰበ፤ ከዚያም ወደ ታላቁ የአምላክ የቁጣ ወይን መጭመቂያ ወረወረው። 20  የወይኑ መጭመቂያም ከከተማው ውጭ ተረገጠ፤ ከመጭመቂያውም እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስ ከፍታ ያለውና አንድ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ* ርቀት ያለው ደም ወጣ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ራእይ 14:20 * 296 ኪሎ ሜትር ገደማ።