ራእይ 12:1-17

12  በሰማይም ታላቅ ምልክት ታየ፤ ፀሐይን የተጎናጸፈች አንዲት ሴት ታየች፤ ጨረቃም ከእግሯ ሥር ነበረች፤ በራሷም ላይ አሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል ነበር፤  እሷም ነፍሰ ጡር ነበረች። ምጥ ይዟትም ለመውለድ እያጣጣረች ትጮኽ ነበር።  ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች የደፋ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ታላቅ ዘንዶ ታየ፤  ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት አንድ ሦስተኛ ጎትቶ ወደ ምድር ወረወራቸው። ዘንዶውም በምትወልድበት ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆሞ ይጠብቅ ነበር።  እሷም ሕዝቦችን ሁሉ እንደ እረኛ በብረት በትር የሚያግደውን ልጅ፣ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጇም ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።  ሴቲቱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቧት አምላክ ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ ምድረ በዳ ሸሸች።  በሰማይም ጦርነት ተነሳ:- ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤  ሆኖም ዘንዶው ማሸነፍ አልቻለም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።  ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተወረወረ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ። 10  በሰማይም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ:- “አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኃይልና መንግሥት እንዲሁም የእሱ መሲሕ ሥልጣን ሆኗል፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ወደ ታች ተወርውሯል! 11  እነሱም ከበጉ ደም የተነሳና ከምሥክርነታቸው ቃል የተነሳ ድል ነሱት፤ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ለነፍሳቸው አልሳሱም። 12  ከዚህም የተነሳ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” 13  ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተወረወረ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ በወለደችው ሴት ላይ ስደት አደረሰባት። 14  ሆኖም ሴቲቱ በምድረ በዳ ወደተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል የታላቁ ንስር ሁለት ክንፎች ተሰጧት፤ ከእባቡ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለግማሽ ዘመን እንድትመገብ የተደረገው በዚያ ነው። 15  እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትሰምጥ ከአፉ የወጣ እንደ ወንዝ ያለ ውኃ ከበስተኋላዋ ለቀቀባት። 16  ይሁን እንጂ ምድሪቱ ለሴቲቱ ደረሰችላት፤ ምድሪቱም አፏን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ የለቀቀውን ወንዝ ዋጠች። 17  ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ እጅግ ተቆጥቶ የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁትንና ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ የተሰጣቸውን ከዘሯ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች