ማርቆስ 16:1-20

16  ሰንበት ካለፈ በኋላም መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው ሊቀቡት ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞች ገዙ።  ከዚያም በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በማለዳ ፀሐይ እንደወጣች ወደ መታሰቢያ መቃብሩ መጡ።  እርስ በርሳቸውም “በመታሰቢያ መቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር።  ቀና ብለው ሲመለከቱ ግን ድንጋዩ በጣም ትልቅ ቢሆንም ከቦታው ተንከባሎ አዩ።  ወደ መታሰቢያ መቃብሩ ሲገቡ ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ አንድ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።  እሱም እንዲህ አላቸው:- “አትደንግጡ። የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው። እሱ ተነስቷል፤ እዚህ የለም። ተመልከቱ! እሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውና።  ይልቁንስ ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደነገራችሁ እዚያ ታዩታላችሁ’ በሏቸው።”  እነሱም በአድናቆት ተውጠውና በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ከወጡ በኋላ ከመታሰቢያ መቃብሩ ሸሹ። ከፍርሃታቸውም የተነሳ ለማንም ምንም ነገር አልተናገሩም። አጭር መደምደሚያ በእጅ የተጻፉ አንዳንድ የቅርብ ጊዜ ቅጂዎች እንዲሁም አንዳንድ ትርጉሞች ከማርቆስ 16:8 በኋላ የሚከተለውን አጭር መደምደሚያ ይጨምራሉ:- ሆኖም የታዘዙትን ነገር ሁሉ ከጴጥሮስ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። በተጨማሪም ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ራሱ ቅዱስ የሆነውንና የማይለወጠውን የዘላለም መዳን አዋጅ በእነሱ በኩል ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ላከው። ረጅም መደምደሚያ አንዳንድ በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች (ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ፣ ኮዴክስ ኤፍሬማይ፣ ኮዴክስ ቤዜ) እና ጥንታዊ ትርጉሞች (ላቲን ቩልጌት፣ ኩሪቶኒያን ሲሪያክ፣ ሲሪያክ ፐሺታ) የሚከተለውን ረጅም መደምደሚያ ይጨምራሉ፤ ሆኖም ኮዴክስ ሳይናይቲከስ፣ ኮዴክስ ቫቲካነስ፣ ሳይናይቲክ ሲሪያክ ኮዴክስና አርሜንያን ቨርዥን ይህን አይጨምሩም:-  በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በማለዳ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመጀመሪያ የታየው ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ነበር። 10  እሷም ሄዳ በሐዘንና በለቅሶ ላይ ለነበሩት ተከታዮቹ ነገረቻቸው። 11  እነሱ ግን ሕያው መሆኑንና እሷ እንዳየችው ሲሰሙ አላመኗትም። 12  ከዚህም በኋላ ከእነሱ ሁለቱ ወደ ገጠር እየሄዱ ሳሉ በሌላ መልክ ታያቸው፤ 13  እነሱም ተመልሰው መጥተው ለቀሩት ነገሯቸው። ይሁንና እነዚህንም ቢሆን አላመኗቸውም። 14  በኋላ ግን በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ለራሳቸው ተገለጠላቸው፤ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያዩትን ሰዎች ስላላመኗቸውም፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ደንዳናነት ነቀፈ። 15  እንዲህም አላቸው:- “ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ምሥራቹን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 16  ያመነና የተጠመቀ ይድናል፤ የማያምን ግን ይፈረድበታል። 17  በተጨማሪም እነዚህ ምልክቶች በሚያምኑት ላይ ይታያሉ:- በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በልሳን ይናገራሉ፤ 18  እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ ማንኛውንም የሚገድል ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም። እጃቸውን በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነሱም ይድናሉ።” 19  ከዚያም ጌታ ኢየሱስ ካናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ተወሰደ፤ በአምላክ ቀኝም ተቀመጠ። 20  እነሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ መልእክቱንም በሚፈጽሟቸው ምልክቶች ያጠናክር ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች