ማርቆስ 12:1-44

12  ከዚያም እንዲህ በማለት በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር:- “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።  ወቅቱ ሲደርስም ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ።  እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።  በድጋሚም ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፣ አዋረዱትም።  እንደገናም ሌላ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።  አሁን የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር። ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው።  እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፣ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ።  ስለዚህ ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ እርሻ ውጭም ጣሉት።  እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣና ገበሬዎቹን ያጠፋቸዋል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል። 10  እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ከቶ አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ። 11  ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ይህም ለዓይናችን ድንቅ ነው።’” 12  በዚህ ጊዜ ምሳሌውን የተናገረው እነሱን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ ስለተረዱ እሱን የሚይዙበትን መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሆኖም ሕዝቡን ፈሩ። ስለሆነም ትተውት ሄዱ። 13  ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንንና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ። 14  እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት:- “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለማንም እንደማታዳላ፣ የሰውንም ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? 15  እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡና አሳዩኝ” አላቸው። 16  እነሱም አመጡለት። እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት። 17  ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ። 18  ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ደግሞ ወደ እሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት:- 19  “መምህር፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ከእሷ ዘር መተካት እንዳለበት ጽፎልናል። 20  ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አገባና ዘር ሳይተካ ሞተ። 21  ሁለተኛውም አገባት፤ ሆኖም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ። 22  ሰባቱም ዘር አልተኩም። በመጨረሻ ሴትየዋም ሞተች። 23  እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?” 24  ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም? 25  ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ። 26  ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚናገረው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም? 27  እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።” 28  እዚያ መጥቶ ሲከራከሩ ይሰማ የነበረ ከጸሐፍት ወገን የሆነ አንድ ሰው ጥሩ አድርጎ እንደመለሰላቸው አስተውሎ “ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። 29  ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “የመጀመሪያው ይህ ነው፣ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፣ ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤ 30  አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’ 31  ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” 32  ጸሐፊውም እንዲህ አለው:- “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ ማንም የለም’፤ 33  እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ የማሰብ ችሎታና በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕቶች ሁሉ እጅግ ይበልጣል።” 34  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በማስተዋል እንደመለሰ ተረድቶ “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ግን ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። 35  ይሁን እንጂ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እያስተማረ ሳለ እንዲህ በማለት መልስ ሰጠ:- “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? 36  ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‘ይሖዋ ጌታዬን:- “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ብሏል። 37  ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም በደስታ ያዳምጠው ነበር። 38  ማስተማሩንም በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ይወዳሉ፣ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ፣ 39  በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣ በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ ይፈልጋሉ። 40  የመበለቶችን ቤት የሚያራቁቱትና ለታይታ ጸሎታቸውን የሚያስረዝሙት እነሱ ናቸው፤ እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።” 41  ኢየሱስ በመዋጮ ዕቃዎቹ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ መመልከት ጀመረ፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር። 42  በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች። 43  ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው:- “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የከተተችው ይህች ድሃ መበለት ነች። 44  ምክንያቱም ሁሉም የከተቱት ከትርፋቸው ነው፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ከተተች።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማር 12:10 ማቴዎስ 21:42 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ማር 12:31 * “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።