ማርቆስ 11:1-33

11  ወደ ኢየሩሳሌም፣ በደብረ ዘይት ተራራ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በተቃረቡ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ላካቸው፤  እንዲህም አላቸው:- “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደሩም እንደገባችሁ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ ውርንጭላ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት።  ማንም ሰው ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ ‘ጌታ ይፈልገዋል፤ ደግሞም ወዲያውኑ ወደዚህ ይመልሰዋል’ በሉ።”  እነሱም ሄዱ፤ ውርንጭላውንም በአንድ ጠባብ መንገድ ዳር፣ ደጃፍ ላይ ታስሮ አገኙት።  በዚያ ከቆሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ “ምን ማድረጋችሁ ነው? ውርንጭላውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” ይሏቸው ጀመር።  እነሱም ልክ ኢየሱስ ያላቸውን ነገሯቸው፤ ከዚያም ፈቀዱላቸው።  ውርንጭላውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ መደረቢያቸውንም በውርንጭላው ጀርባ ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠበት።  ብዙዎችም መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም ቅርንጫፎችን ከሜዳ ቆረጡ።  ከፊት የሚሄዱትና ከኋላ የሚከተሉት እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር:- “እባክህ አድነው!* በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! 10  የሚመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከ ነው! በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እባክህ አድነው!” 11  ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያውም ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ፤ ሰዓቱም ገፍቶ ስለነበር ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ሄደ። 12  በማግስቱ ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። 13  ቅጠሏ የለመለመ አንዲት የበለስ ዛፍ ከሩቅ ተመለከተና ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ለማየት ሄደ። ወደ እሷ በቀረበ ጊዜ ግን በለስ የሚያፈራበት ወቅት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14  ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏን “ከእንግዲህ ወዲህ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ይሰሙት ነበር። 15  ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። በዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ፤ 16  ማንም ሰው ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ አቋርጦ እንዳያልፍም ከለከለ። 17  እንዲሁም “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም? እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” እያለ ያስተምር ነበር። 18  የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ይህን በሰሙ ጊዜ እሱን የሚያጠፉበትን መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ዘወትር በትምህርቱ ስለሚገረም ይፈሩት ነበር። 19  አመሻሽ ላይም ከከተማዋ ይወጡ ነበር። 20  ማለዳ ላይ በመንገድ ሲያልፉ የበለስ ዛፏ ከነሥሯ ደርቃ አዩአት። 21  ጴጥሮስም ትዝ አለውና “ረቢ፣* ተመልከት! የረገምካት የበለስ ዛፍ ደርቃለች” አለው። 22  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው:- “በአምላክ ላይ እምነት ይኑራችሁ። 23  እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና በልቡ ሳይጠራጠር የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም ቢያምን ይሆንለታል። 24  ስለዚህ እላችኋለሁ፣ በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፣ ታገኙታላችሁም። 25  በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ ያላችሁን ቅሬታ ሁሉ ይቅር በሉ።” 26*   —— 27  እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በቤተ መቅደሱም ሲዘዋወር የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ወደ እሱ መጥተው 28  “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ይሉት ጀመር። 29  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30  የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።” 31  እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር:- “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ 32  ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ?” ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ። 33  ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማር 11:9 * ቃል በቃል፣ “ሆሳዕና።”
ማር 11:21 * “መምህር” ማለት ነው።
ማር 11:26 ማቴዎስ 17:21 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።