በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 4

የገንዘብ አያያዝ

የገንዘብ አያያዝ

“መመካከር ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል።”—ምሳሌ 20:18

ሁላችንም ብንሆን ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ገንዘብ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 30:8) ደግሞም “ገንዘብ ጥበቃ” ያስገኛል። (መክብብ 7:12) ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስለ ገንዘብ መነጋገር አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ገንዘብ በትዳራችሁ ውስጥ ችግር እንዲፈጥር አትፍቀዱ። (ኤፌሶን 4:32) ባልና ሚስት ገንዘባቸውን እንዴት ማውጣት እንዳለባቸው በሚወስኑበት ጊዜ እርስ በርስ መተማመንና መተባበር ይኖርባቸዋል።

1 በጥንቃቄ ዕቅድ አውጡ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” (ሉቃስ 14:28) ገንዘባችሁን እንዴት እንደምትጠቀሙበት አንድ ላይ ሆናችሁ ዕቅድ ማውጣታችሁ አስፈላጊ ነው። (አሞጽ 3:3) ምን መግዛት እንደሚያስፈልጋችሁና ማውጣት የምትችሉት ምን ያህል እንደሆነ ወስኑ። (ምሳሌ 31:16) አንድን ነገር ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ስላላችሁ ብቻ የግድ መግዛት ይኖርባችኋል ማለት አይደለም። ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። በእጃችሁ ካለው ገንዘብ በላይ አታውጡ።—ምሳሌ 21:5፤ 22:7

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን ሁሉ ከሸፈናችሁ በኋላ በተረፈው ገንዘብ ምን እንደምታደርጉበት አንድ ላይ ሆናችሁ ወስኑ

  • ወጪያችሁ ከገቢያችሁ ከበለጠ ወጪያችሁን ለመቀነስ ምን እንደምታደርጉ ግልጽ የሆነ ዕቅድ አውጡ። ለምሳሌ ያህል፣ ምግብ ቤት በመብላት ፋንታ ቤት ውስጥ ምግብ ማዘጋጀት ትችላላችሁ

2 ግልጽና ምክንያታዊ ሁኑ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በይሖዋ ፊት ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ፊት ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት [አከናውኑ]።” (2 ቆሮንቶስ 8:21) ገቢና ወጪህን በተመለከተ ለትዳር ጓደኛህ ሐቀኛ ሁን።

ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ከበድ ያለ ውሳኔ ስታደርግ ምንጊዜም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተመካከር። (ምሳሌ 13:10) ስለ ገንዘብ መነጋገራችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ሰላም እንዲኖር ይረዳል። ገቢህን እንደ ግል ገንዘብህ ሳይሆን እንደ ቤተሰቡ ገንዘብ አድርገህ ተመልከተው።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • አንዳችሁ ሌላውን ሳታማክሩ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምትችሉ ተነጋግራችሁ ወስኑ

  • ስለ ገንዘብ ለመነጋገር ችግር እስኪፈጠር አትጠብቁ