በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 2

አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ

አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ

“አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማርቆስ 10:9

ይሖዋ ‘ታማኝነትን እንድንወድ’ ይጠብቅብናል። (ሚክያስ 6:8) በተለይ በትዳራችሁ ውስጥ ታማኝነት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ታማኝነት ከሌለ መተማመን አይኖርም። ፍቅራችሁ እያደገ እንዲሄድ ደግሞ መተማመን መኖሩ የግድ አስፈላጊ ነው።

በዛሬው ጊዜ በትዳር ውስጥ ታማኝነትን ማጉደል የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። ትዳራችሁን እንዲህ ካለው አደጋ መጠበቅ እንድትችሉ ሁለት ነገሮችን ለማድረግ መቁረጥ አለባችሁ።

1 ለትዳራችሁ ቅድሚያ ስጡ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።” (ፊልጵስዩስ 1:10) በሕይወታችሁ ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ትዳራችሁ ነው። ትዳራችሁ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ይሖዋ ለትዳር ጓደኛችሁ ትኩረት እንድትሰጡና ‘ተደስታችሁ እንድትኖሩ’ ይፈልጋል። (መክብብ 9:9) ይሖዋ የትዳር ጓደኛችሁን ፈጽሞ ችላ ማለት እንደሌለባችሁ ይልቁንም አንዳችሁ ሌላውን ማስደሰት የምትችሉባቸውን መንገዶች መፈለግ እንዳለባችሁ በግልጽ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) የትዳር ጓደኛህ ተፈላጊ እንደሆነችና እንደምታደንቃት እንዲሰማት አድርግ።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ዘወትር አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲሁም ለትዳር ጓደኛችሁ ሙሉ ትኩረታችሁን ስጡ

  • “እኔ” ከማለት ይልቅ “እኛ” እያላችሁ አስቡ

2 ልባችሁን ጠብቁ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ማቴዎስ 5:28) አንድ ሰው ስለ ፆታ ብልግና የሚያውጠነጥን ከሆነ ለትዳር ጓደኛው ያለውን ታማኝነት እያጓደለ ነው ሊባል ይችላል።

ይሖዋ ‘ልባችሁን መጠበቅ’ እንደሚያስፈልጋችሁ ይናገራል። (ምሳሌ 4:23፤ ኤርምያስ 17:9) ይህን ለማድረግ ደግሞ ዓይናችሁን መጠበቅ አለባችሁ። (ማቴዎስ 5:29, 30) ሌላዋን ሴት ፈጽሞ በምኞት ላለመመልከት ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን የገባውን የኢዮብን ምሳሌ ተከተሉ። (ኢዮብ 31:1) የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ፈጽሞ ላለመመልከትና ላለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲሁም ከትዳር ጓደኛችሁ ሌላ ለማንም ሰው ምንም ዓይነት የፍቅር ስሜት እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ለትዳር ጓደኛህ ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆንህ ለሌሎች በግልጽ እንዲታይ አድርግ

  • የትዳር ጓደኛህን ስሜት ግምት ውስጥ አስገባ፤ ከሌላ ሴት ጋር ያለህ ቅርርብ እሷን ቅር የሚያሰኛት ከሆነ ግንኙነቱን ወዲያውኑ አቋርጥ