ክፍል 8

መከራ ሲያጋጥማችሁ

መከራ ሲያጋጥማችሁ

“አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው።”—1 ጴጥሮስ 1:6

አስደሳች ትዳርና የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራችሁ የተቻላችሁን ሁሉ ለማድረግ ብትጥሩም እንኳ ደስታችሁን የሚያሳጡ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። (መክብብ 9:11) ችግሮች ሲያጋጥሙን መቋቋም እንድንችል አፍቃሪው አምላካችን እርዳታ ያደርግልናል። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች የምትከተሉ ከሆነ በጣም የከፋ ችግር ቢያጋጥማችሁም እንኳ ልትቋቋሙት ትችላላችሁ።

1 በይሖዋ ታመኑ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።” (1 ጴጥሮስ 5:7) ለደረሱባችሁ መከራዎች ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ ምንጊዜም አትዘንጉ። (ያዕቆብ 1:13) ወደ አምላክ ስትቀርቡ እሱም ከሁሉ በላቀ መንገድ ይረዳችኋል። (ኢሳይያስ 41:10) “ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።”—መዝሙር 62:8

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በየዕለቱ ስታነቡና ስታጠኑ መጽናኛ ታገኛላችሁ። ይህም ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን’ እንዴት እንደሆነ በራሳችሁ ሕይወት ለማየት ያስችላችኋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ሮም 15:4) ይሖዋ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ሊሰጣችሁ ቃል ገብቷል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • መረጋጋትና አጥርታችሁ ማሰብ እንድትችሉ ይሖዋ እንዲረዳችሁ ጸልዩ

  • ያሏችሁን አማራጮች ከገመገማችሁ በኋላ የተሻለውን አካሄድ ምረጡ

2 ራሳችሁንም ሆነ ቤተሰባችሁን ተንከባከቡ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአስተዋይ ሰው ልብ እውቀትን ያገኛል፤ የጥበበኛም ጆሮ እውቀትን ለማግኘት ይጥራል።” (ምሳሌ 18:15) የተሟላ መረጃ ለማግኘት ሞክሩ። እያንዳንዱ የቤተሰባችሁ አባል ምን እንደሚያስፈልገው ለማወቅ ጥረት አድርጉ። እርስ በርስ ተነጋገሩ፤ አንዳችሁ ሌላው አዳምጡ።—ምሳሌ 20:5

አንድ የቤተሰባችሁ አባል ቢሞትስ? ሐዘናችሁን ለመግለጽ አትፍሩ። ኢየሱስም እንኳ ‘እንባውን እንዳፈሰሰ’ አስታውሱ። (ዮሐንስ 11:35፤ መክብብ 3:4) በቂ እረፍትና እንቅልፍ ማግኘትም አስፈላጊ ነው። (መክብብ 4:6) እንዲህ ማድረጋችሁ ያጋጠማችሁን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ይረዳችኋል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ከቤተሰባችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ለማዳበር መከራ እስኪያጋጥማችሁ አትጠብቁ። እንዲህ ዓይነት ልማድ ካላችሁ ችግር በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ማውራት ቀላል ይሆንላችኋል

  • ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሌሎች ሰዎችንም አነጋግሩ

3 እርዳታ ሲያስፈልጋችሁ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” (ምሳሌ 17:17) ወዳጆቻችሁ ሊረዷችሁ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ለእነሱ ከመንገር ወደኋላ አትበሉ። (ምሳሌ 12:25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያደርጉላችሁ ጠይቁ። እነሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰጧችሁ ምክር ይጠቅማችኋል።—ያዕቆብ 5:14

በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ካላቸውና እሱ በገባቸው ተስፋዎች ከሚተማመኑ ሰዎች ጋር አዘውትራችሁ በመሰብሰብ፣ የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ማግኘት ትችላላችሁ። ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች መርዳትም በእጅጉ ያጽናናችኋል። በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ስላላችሁ እምነት ለሌሎች ተናገሩ። የተቸገሩትን በመርዳት ራሳችሁን በሥራ አስጠምዱ፤ እንዲሁም ከሚወዷችሁና ከሚያስቡላችሁ ሰዎች ራሳችሁን አታግልሉ።—ምሳሌ 18:1፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ለምትቀርቡት ወዳጃችሁ ስሜታችሁን አውጥታችሁ ንገሩ፤ የሚያደርግላችሁን እርዳታም ተቀበሉ

  • የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች በግልጽና በሐቀኝነት ተናገሩ