በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ሁለት

የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

1, 2. የይሖዋ ወዳጆች የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን ጥቀስ።

ጓደኛህ እንዲሆን የምትፈልገው ምን ዓይነት ሰው ነው? የምትወደውና የምትግባባው ሰው ጓደኛህ እንዲሆን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ደግ የሆነና ሌሎች ግሩም ባሕርያት ያሉት ሰው ጓደኛህ ቢሆን እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም።

2 በጥንት ዘመን ይሖዋ ወዳጆቹ አድርጎ የመረጣቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ ነበር። (ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ዳዊትን ይወደው ነበር። ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ [ሰው]” በማለት ጠርቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22) ነቢዩ ዳንኤልም በይሖዋ ዘንድ ‘እጅግ የተወደደ’ ነበር።—ዳንኤል 9:23

3. አብርሃም፣ ዳዊትና ዳንኤል የይሖዋ ወዳጆች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?

3 አብርሃም፣ ዳዊትና ዳንኤል የይሖዋ ወዳጆች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ይሖዋ፣ አብርሃምን ‘ቃሌን ሰምተሃል’ ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ይሖዋ፣ በትሕትና የሚታዘዙትን ሰዎች ወዳጆቹ ያደርጋቸዋል። ሌላው ቀርቶ ብዙ ሰዎችን ያቀፈ ብሔርም እንኳ የእሱ ወዳጅ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን “ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ኤርምያስ 7:23) ስለዚህ አንተም የይሖዋ ወዳጅ መሆን ከፈለግክ እሱን መታዘዝ ይኖርብሃል።

ይሖዋ ለወዳጆቹ ጥበቃ ያደርጋል

4, 5. ይሖዋ ለወዳጆቹ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን [ማሳየት]” እንደሚፈልግ ይገልጻል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) መዝሙር 32:8 ላይ ይሖዋ ለወዳጆቹ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ። ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ።”

5 ይሁንና ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት እንዲቋረጥ የሚፈልግ አንድ ኃይለኛ ጠላት አለ። ይሖዋ ግን ጥበቃ ያደርግልናል። (መዝሙር 55:22ን አንብብ።) የይሖዋ ወዳጆች እንደመሆናችን መጠን በሙሉ ልባችን እናገለግለዋለን። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም እንኳ ለእሱ ታማኝ እንሆናለን። መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም” ብሏል። እኛም እንደ መዝሙራዊው በይሖዋ እንተማመናለን። (መዝሙር 16:8፤ 63:8) ታዲያ ሰይጣን፣ ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት እንዲቋረጥ ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው?

ሰይጣን የሰነዘረው ክስ

6. ሰይጣን ሰዎችን በተመለከተ ምን ብሏል?

6 በምዕራፍ 11 ላይ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ጥያቄ እንዳነሳ ተመልክተናል፤ ሰይጣን፣ ይሖዋን ውሸታም ብሎ የከሰሰው ከመሆኑም ሌላ ትክክልና ስህተት የሆነውን ራሳቸው እንዳይወስኑ በመከልከል በአዳምና በሔዋን ላይ በደል እንደፈጸመ አድርጎ ተናግሯል። ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ፣ ሰይጣን የአምላክ ወዳጅ መሆን በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ክስ እንደሰነዘረ ይገልጻል። ሰይጣን፣ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ስለሚወዱት ሳይሆን ከእሱ ጥቅም ለማግኘት ስለሚፈልጉ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም ‘ማንኛውንም ሰው ከአምላክ እንዲርቅ ማድረግ እችላለሁ’ ሲል ገልጿል። ከኢዮብ ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንዲሁም ይሖዋ ጥበቃ ያደረገለት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

7, 8. (ሀ) ኢዮብ ማን ነው? (ለ) ሰይጣን ስለ ኢዮብ ምን ብሏል?

7 ኢዮብ ማን ነው? ኢዮብ ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ይኖር የነበረ ጥሩ ሰው ነው። ይሖዋ በዚያ ዘመን በምድር ላይ እንደ ኢዮብ ዓይነት ሰው እንዳልነበረ ተናግሯል። ኢዮብ ለአምላክ ከፍተኛ አክብሮት የነበረው ከመሆኑም ሌላ ክፋትን ይጠላ ነበር። (ኢዮብ 1:8) በእርግጥም ኢዮብ የይሖዋ ወዳጅ ነበር።

8 ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለራሱ ጥቅም ሲል እንደሆነ ተናግሯል። ሰይጣን ይሖዋን እንዲህ ብሎታል፦ “እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፤ ከብቱም በምድሪቱ ላይ በዝቷል። ሆኖም እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”—ኢዮብ 1:10, 11

9. ይሖዋ፣ ሰይጣን ምን እንዲያደርግ ፈቅዶለታል?

9 ሰይጣን በኢዮብ ላይ ክስ ሰንዝሯል፤ ‘ኢዮብ ይሖዋን የሚያገለግለው ከእሱ ጥቅም ለማግኘት ሲል ብቻ ነው’ ሲል ተናግሯል። በተጨማሪም ሰይጣን፣ ኢዮብ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲያቆም ማድረግ እንደሚችል ተናግሯል። ይሖዋ ሰይጣን በተናገረው ሐሳብ ባይስማማም ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት፤ ይህም ኢዮብ የይሖዋ ወዳጅ የሆነው ለእሱ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ መሆን አለመሆኑን ለማሳየት ያስችላል።

ሰይጣን በኢዮብ ላይ ጥቃት ሰነዘረ

10. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ጥቃት የሰነዘረው እንዴት ነው? ሆኖም ኢዮብ ምን አላደረገም?

10 በመጀመሪያ ሰይጣን፣ ኢዮብ እንስሳቱን በሙሉ እንዲያጣ አደረገው። ከዚያም ሰይጣን አብዛኞቹን የኢዮብ አገልጋዮች ገደላቸው። ኢዮብ ሁሉንም ነገር አጣ። በመጨረሻም ሰይጣን አሥሩ የኢዮብ ልጆች በአውሎ ነፋስ እንዲሞቱ አደረገ። ሆኖም ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ ሆኗል። “ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኃጢአት አልሠራም ወይም አምላክን በደል ሠርቷል ብሎ አልወነጀለም።”—ኢዮብ 1:12-19, 22

ኢዮብ የይሖዋ ታማኝ ወዳጅ በመሆኑ ይሖዋ ባርኮታል

11. (ሀ) ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ሌላ ጥቃት ሰነዘረ? (ለ) በዚህ ጊዜ ኢዮብ ምን ብሏል?

11 የሰይጣን ጥቃት በዚህ አላበቃም። አምላክን “በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል” አለው። በመሆኑም ሰይጣን ኢዮብን በከባድ በሽታ እንዲሠቃይ አደረገው። (ኢዮብ 2:5, 7) በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ ሆኗል። “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 27:5

12. ኢዮብ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው?

12 ኢዮብ፣ ሰይጣን ስለሰነዘረው ክስ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ አልተገነዘበም። ይህን ሁሉ ችግር ያመጣበት ይሖዋ እንደሆነ አድርጎ አስቦ ነበር። (ኢዮብ 6:4፤ 16:11-14) ያም ሆኖ ኢዮብ ለይሖዋ እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ ሆኗል። ሰይጣን ለሰነዘረው ክስ መልስ ሰጥቷል። ኢዮብ የአምላክ ወዳጅ የሆነው ጥቅም ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ይሖዋን ስለሚወድ ነው። ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ውሸት እንደሆነ ተረጋግጧል!

13. ኢዮብ ታማኝ መሆኑ ምን ውጤት አስገኝቷል?

13 ኢዮብ በሰማይ ስለተከናወነው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር ባይኖርም እንኳ ለአምላክ ታማኝ ሆኗል፤ ሰይጣን ክፉ መሆኑንም አረጋግጧል። ኢዮብ የይሖዋ ታማኝ ወዳጅ መሆኑን ስላስመሠከረ ይሖዋ ባርኮታል።—ኢዮብ 42:12-17

ሰይጣን በአንተ ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል?

14, 15. ሰይጣን በሁሉም ሰው ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል?

14 ከኢዮብ ታሪክ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። ሰይጣን፣ እኛም ይሖዋን የምናገለግለው ጥቅም ለማግኘት እንደሆነ ተናግሯል። በኢዮብ 2:4 ላይ ሰይጣን “ሰውም ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” ብሏል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሰይጣን፣ ኢዮብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ራስ ወዳድ እንደሆነ ተናግሯል። ኢዮብ ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም እንኳ ሰይጣን ይሖዋን መስደቡንና የእሱን አገልጋዮች መክሰሱን አላቆመም። ምሳሌ 27:11 “ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ [ወይም ለሚሰድበኝ] መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው” ይላል።

15 ይሖዋን በመታዘዝና የእሱ ታማኝ ወዳጅ በመሆን ሰይጣን ውሸታም እንደሆነ ማሳየት ትችላለህ። የአምላክ ወዳጅ ለመሆን በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ቢያስፈልግህም እንኳ በዚህ ውሳኔህ አትቆጭም! ይህ ውሳኔ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለም። ሰይጣን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙህ ለይሖዋ ታማኝ እንደማትሆን ተናግሯል። እኛን በማታለል ለአምላክ ታማኝ እንዳንሆን ለማድረግ ይሞክራል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

16. (ሀ) ሰይጣን፣ ሰዎች ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ የትኞቹን ዘዴዎች ይጠቀማል? (ለ) ዲያብሎስ፣ አንተ ይሖዋን ማገልገልህን እንድታቆም ለማድረግ የትኛውን ዘዴ ለመጠቀም የሚሞክር ይመስልሃል?

16 ሰይጣን የአምላክ ወዳጆች እንዳንሆን ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ” ሊያጠቃን ይሞክራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ጓደኞችህ፣ የቤተሰብህ አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህንና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግህን እንድታቆም ለማድረግ ቢሞክሩ ልትደናገጥ አይገባም። በዚህ ወቅት ጥቃት እየደረሰብህ እንዳለ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። * (ዮሐንስ 15:19, 20) በተጨማሪም ሰይጣን “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል።” እኛን ለማታለልና የይሖዋን ትእዛዝ እንዳናከብር ለማድረግ ይሞክራል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ከዚህም ሌላ ሰይጣን፣ ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንን እንዲሰማን በማድረግ አምላክን ማገልገላችንን እንድናቆም ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል።—ምሳሌ 24:10

የይሖዋን ትእዛዛት ጠብቅ

17. ይሖዋን የምንታዘዘው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋን ስንታዘዝ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እናሳያለን። ታዛዥ ለመሆን ምን ይረዳናል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ይላል። (ዘዳግም 6:5) ይሖዋን የምንታዘዘው ስለምንወደው ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ እሱ የጠየቀንን ሁሉ ለማድረግ እንነሳሳለን። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም” በማለት ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:3

18, 19. (ሀ) ይሖዋ የሚጠላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም የምንለው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ የሚጠላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ “ ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ጥሉ” በሚለው ሣጥን ላይ ተጠቅሰዋል። መጀመሪያ ላይ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆኑ አድርገህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶቹን አንብበህ በሚገባ ስታስብባቸው የይሖዋን ሕግጋት መታዘዝ ምን ጥቅም እንዳለው ግልጽ ይሆንልሃል። በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግህም ሊሰማህ ይችላል። ይህን ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆን ቢችልም እነዚህን ለውጦች ማድረግህ የይሖዋ ታማኝ ወዳጅ እንድትሆን ያስችልሃል፤ ይህ ደግሞ ሰላምና ደስታ ያስገኝልሃል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እነዚህን ለውጦች ማድረግ ይቻላል የምንለው ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠይቀንም። (ዘዳግም 30:11-14) ይሖዋ ወዳጃችን እንደመሆኑ መጠን እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል። ጠንካራ ጎናችንንም ሆነ ደካማ ጎናችንን በሚገባ ያውቃል። (መዝሙር 103:14) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:13) ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አንተም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም እንድትችል ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ይሰጥሃል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ጳውሎስ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት የይሖዋን እርዳታ በማግኘቱ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” በማለት ተናግሯል።—ፊልጵስዩስ 4:13

አምላክ የሚወዳቸውን ነገሮች ውደድ

20. የትኞቹን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርብሃል? ለምንስ?

20 የይሖዋ ወዳጆች መሆን ከፈለግን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች መጥላታችን ብቻ በቂ አይደለም። (ሮም 12:9) የአምላክ ወዳጆች እሱ የሚወዳቸውን ነገሮች ይወዳሉ። በመዝሙር 15:1-5 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የተገለጸውን ብቃት ያሟላሉ። የይሖዋ ወዳጆች እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት በማንጸባረቅ እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ።—ገላትያ 5:22, 23

21. አምላክ የሚወዳቸውን ባሕርያት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

21 አምላክ የሚወዳቸውን ባሕርያት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ በማንበብና በማጥናት ይሖዋ የሚወዳቸውን ነገሮች ማወቅ ይኖርብሃል። (ኢሳይያስ 30:20, 21) እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ያድጋል፤ ለእሱ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ ደግሞ እሱን ለመታዘዝ ይበልጥ ትነሳሳለህ።

22. ይሖዋን መታዘዝህ ምን ውጤት ያስገኛል?

22 በሕይወትህ ውስጥ የምታደርገው ለውጥ አሮጌ ልብስ አውልቆ አዲስ ልብስ ከመልበስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አሮጌውን ስብዕና ገፈህ መጣልና አዲሱን ስብዕና መልበስ’ እንደሚያስፈልግህ ይናገራል። (ቆላስይስ 3:9, 10) እንዲህ ማድረግ ቀላል ባይሆንም እንኳ እነዚህን ለውጦች በማድረግ ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆነ ይሖዋ “ትልቅ ወሮታ” ወይም ሽልማት እንደምናገኝ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 19:11) ይሖዋን በመታዘዝ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት ትችላለህ። ይሖዋን የምታገለግለው ወደፊት በረከት ስለምታገኝ ብቻ መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስተህ ልታገለግለው ይገባል። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ!

^ አን.16 እንዲህ ሲባል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህን እንድታቆም ለማድረግ የሚሞክሩትን ሰዎች ሰይጣን እየተቆጣጠራቸው ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ሰይጣን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” ከመሆኑም ሌላ ‘መላው ዓለም በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው።’ በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ለማድረግ ቢሞክሩ ሊያስገርመን አይገባም።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19