ምዕራፍ ስምንት
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
1. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለ የትኛው ጸሎት እንወያያለን?
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ አቡነ ዘበሰማያት ወይም አባታችን ሆይ ተብሎ የሚጠራውን ጸሎት በሚገባ ያውቁታል። ኢየሱስ ይህን ጸሎት በመጠቀም፣ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ ስለ ምን ነገሮች ጸልዮአል? በዛሬው ጊዜ ይህን ጸሎት መጸለያችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
2. ኢየሱስ ስለ የትኞቹ ሦስት አስፈላጊ ነገሮች እንድንጸልይ አስተምሮናል?
2 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።’” (ማቴዎስ 6:9-13ን አንብብ።) ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሦስት ነገሮች እንድንጸልይ ያስተማረው ለምንድን ነው?—ተጨማሪ ሐሳብ 20ን ተመልከት።
3. የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
3 የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ተምረናል። አምላክ ለሰው ልጆችም ሆነ ለምድር ያለውን ዓላማም ተመልክተናል። ይሁንና ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ሲል ምን ማለቱ ነው? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ‘የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ምን ነገሮችን ያከናውናል? የአምላክ ስም እንዲቀደስ የሚያደርገውስ እንዴት ነው?’ ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
4. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ንጉሡስ ማን ነው?
4 ይሖዋ በሰማይ አንድ መስተዳድር ያቋቋመ ሲሆን ኢየሱስንም ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መስተዳድር የአምላክ 1 ጢሞቴዎስ 6:15) ከየትኛውም ሰብዓዊ ገዢ ይበልጥ መልካም ነገር ማድረግ ይችላል፤ ሰብዓዊ ገዢዎች አንድ ላይ ቢተባበሩ እንኳ የኢየሱስን ያህል ኃይል ሊኖራቸው አይችልም።
መንግሥት በማለት ይጠራዋል። ኢየሱስ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው።” (5. የአምላክ መንግሥት የሚገዛው የት ሆኖ ነው? የሚገዛውስ ምንን ነው?
5 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከአርባ ቀን በኋላ ወደ ሰማይ ተመልሷል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ የመንግሥቱ ንጉሥ እንዲሆን ኢየሱስን ሾሞታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:33) የአምላክ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ ምድርን ይገዛል። (ራእይ 11:15) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መንግሥት ‘ሰማያዊ መንግሥት’ ብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:18
6, 7. ኢየሱስ ከየትኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ የተሻለ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ከየትኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚበልጥ ይናገራል፤ ምክንያቱም “ያለመሞትን ባሕርይ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 6:16) ሰብዓዊ ገዢዎች የተወሰነ ዕድሜ ኖረው መሞታቸው አይቀርም፤ ኢየሱስ ግን ፈጽሞ አይሞትም።
7 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ፍትሐዊና ሩኅሩኅ ንጉሥ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል፤ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “በእሱም ላይ የይሖዋ መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና ይሖዋን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። ይሖዋን በመፍራትም ደስ ይሰኛል። ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም። ለችግረኞች [ወይም ለድሆች] በትክክል ይፈርዳል።” (ኢሳይያስ 11:2-4) እንዲህ ያለ ንጉሥ በሚገዛው ዓለም ውስጥ መኖር አያስደስትም?
8. ኢየሱስ ብቻውን እንደማይገዛ እንዴት እናውቃለን?
8 አምላክ በሰማይ ባቋቋመው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎችን መርጧል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን 2 ጢሞቴዎስ 2:12) ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚነግሡት ሰዎች ቁጥር ስንት ነው?
“ጸንተን ከኖርን አብረን ደግሞ እንነግሣለን” ብሎታል። (9. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት ነገሥታት ቁጥራቸው ስንት ነው? አምላክ እነዚህን ሰዎች መምረጥ የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው?
9 በምዕራፍ 7 ላይ፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ንጉሡን ኢየሱስንና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙትን 144,000 ነገሥታት በራእይ እንዳየ ተመልክተናል። እነዚህ 144,000 ነገሥታት እነማን ናቸው? ዮሐንስ ‘የኢየሱስ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ እንደተጻፈባቸው’ ተናግሯል። በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦ “ምንጊዜም በጉ [ማለትም ኢየሱስ] በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል። እነዚህ . . . ከሰዎች መካከል ተዋጅተዋል።” (ራእይ 14:1, 4ን አንብብ።) እዚህ ላይ የተጠቀሱት 144,000 ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው እንዲገዙ’ አምላክ የመረጣቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ሲሞቱ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። (ራእይ 5:10) ይሖዋ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታማኝ ክርስቲያኖችን ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት እንዲሆኑ ሲመርጥ ቆይቷል።
10. ይሖዋ ኢየሱስንና 144,000ዎቹን፣ ነገሥታት እንዲሆኑ መምረጡ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል የምንለው ለምንድን ነው?
10 ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎችን መምረጡ ለእኛ ከልብ እንደሚያስብ ያሳያል። ኢየሱስ የሰው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ ስለሚያውቅ ጥሩ ገዢ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን። እሱ ራሱ ሰው ሆኖ መከራ ደርሶበታል። ኢየሱስ እንደሚያዝንልን፣ ‘በድካማችን እንደሚራራልን’ እንዲሁም “እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ” እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 4:15፤ 5:8) ከእሱ ጋር የሚገዙት 144,000ዎቹም ቢሆኑ የተመረጡት ከሰዎች መካከል ነው። እነሱም እንደማንኛውም ሰው ከኃጢአትና ከሕመም ጋር ሲታገሉ ኖረዋል። በመሆኑም ኢየሱስና 144,000ዎቹ ስሜታችንን ብቻ ሳይሆን ያሉብንን ችግሮች ጭምር ይረዳሉ።
የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
11. በሰማይ የነበሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት በሙሉ ምንጊዜም የአምላክን ፈቃድ ይፈጽሙ ነበር?
11 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‘የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም’ ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ይሁንና በአንድ ወቅት በሰማይ የአምላክን ፈቃድ የማይፈጽሙ መንፈሳዊ ፍጥረታት ነበሩ። በምዕራፍ 3 ላይ ሰይጣን ዲያብሎስ በይሖዋ ላይ እንዳመፀ ተመልክተናል። ሰይጣን ካመፀ በኋላ እሱም ሆነ ታማኝ ያልሆኑት መላእክት ማለትም አጋንንት ለተወሰነ ጊዜ በሰማይ እንዲኖሩ ይሖዋ ፈቅዶላቸው ነበር። በመሆኑም በሰማይ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት ሁሉም አልነበሩም። በምዕራፍ 10 ላይ ስለ ሰይጣንም ሆነ ስለ አጋንንት ይበልጥ እንማራለን።
12. በራእይ 12:10 ላይ የተገለጹት ሁለት ክንውኖች ምንድን ናቸው?
12 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ከሆነ በኋላ ከሰይጣን ጋር እንደሚዋጋ ይናገራል። (ራእይ 12:7-10ን አንብብ።) ራእይ ምዕራፍ 12 ቁጥር 10 ሁለት አስፈላጊ ነገሮች እንደሚከናወኑ ይገልጻል። አንደኛ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት መግዛት ይጀምራል፤ ሁለተኛ ደግሞ ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር ይወረወራል። ወደፊት እንደምንመለከተው እነዚህ ሁለት ክንውኖች ተፈጽመዋል።
13. ሰይጣን ወደ ምድር መወርወሩ በሰማይ ምን ውጤት አስገኝቷል?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ከተባረሩ በኋላ ታማኞቹ መላእክት የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጽ “እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ!” ይላል። (ራእይ 12:12) በአሁኑ ጊዜ በሰማይ የሚኖር ሁሉ የአምላክን ፈቃድ ስለሚያደርግ በሰማይ የተሟላ ሰላምና አንድነት አለ።
14. ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር መወርወሩ በምድር ላይ ምን አስከትሏል?
14 በምድር ያለው ሁኔታ ግን ፈጽሞ የተለየ ነው። በሰዎች ላይ ራእይ 12:12) ሰይጣን በጣም ተበሳጭቷል። ከሰማይ የተባረረ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ እንደሚጠፋ ያውቃል። በመሆኑም ከመጥፋቱ በፊት በተቻለው መጠን በመላው ምድር ላይ መከራ ማምጣትና ሰዎችን ማሠቃየት ይፈልጋል።
አሳዛኝ ነገሮች እየደረሱ ነው፤ ምክንያቱም “ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ [ምድር] ወርዷል።” (15. አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
15 ይሁንና አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን ፍጹም የሆኑ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። (መዝሙር 37:29) ታዲያ የአምላክ መንግሥት ይህ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት ነው?
16, 17. ዳንኤል 2:44 ስለ አምላክ መንግሥት ምን ይገልጽልናል?
16 ዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲህ ይላል፦ “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” ይህ ትንቢት ስለ አምላክ መንግሥት ምን ይገልጽልናል?
17 አንደኛ፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን” እንደሆነ ይጠቁመናል። ይህም የአምላክ መንግሥት መግዛት ሲጀምር በምድር ላይ ሌሎች መንግሥታት እንደሚኖሩ ያመለክታል። ሁለተኛ፣ የአምላክ መንግሥት ለዘላለም እንደሚጸና እንዲሁም ይህን መንግሥት የሚተካ ሌላ መስተዳድር እንደማይኖር ያስገነዝበናል። ሦስተኛ፣ ይህ ትንቢት በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ጦርነት እንደሚኖር ይገልጽልናል። የአምላክ መንግሥት እነዚህን መንግሥታት ድል በማድረግ በምድር ላይ የሚገዛ ብቸኛ መስተዳድር ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች ከሁሉ በተሻለው አገዛዝ ሥር ይኖራሉ።
18. በአምላክ መንግሥትና በዓለም መንግሥታት መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ጦርነት ምን ተብሎ ይጠራል?
ራእይ 16:14, 16፤ ተጨማሪ ሐሳብ 10ን ተመልከት።
18 የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ መግዛት የሚጀምረው እንዴት ነው? የአርማጌዶን ጦርነት ተብሎ የሚጠራው የመጨረሻው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አጋንንት ‘የዓለም ነገሥታትን ሁሉ’ በማሳሳት “ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚካሄደው ጦርነት” ይሰበስቧቸዋል። በዚህ ጊዜ ሰብዓዊ መንግሥታት ከአምላክ መንግሥት ጋር ይዋጋሉ።—19, 20. የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጓጓው ለምንድን ነው?
19 የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጓጓው ለምንድን ነው? ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ፣ ኃጢአተኞች ስለሆንን እንታመማለን እንዲሁም እንሞታለን። የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ግን ለዘላለም እንደምንኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዮሐንስ 3:16 እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”
20 የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጓጓበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዓለማችን ክፉ በሆኑ ሰዎች የተሞላች በመሆኗ ነው። ብዙ ሰዎች ይዋሻሉ፣ ያጭበረብራሉ እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ይፈጽማሉ። እኛ፣ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንዳያደርጉ መከልከል አንችልም። አምላክ ግን ክፉ ነገር መፈጸማቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችን በአርማጌዶን ጦርነት ያጠፋቸዋል። (መዝሙር 37:10ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጓጓበት ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ሰብዓዊ መንግሥታት በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አቅም የሌላቸው፣ ጨካኝ ወይም ምግባረ ብልሹ በመሆናቸው ነው። ሰዎች አምላክን እንዲታዘዙ አያበረታቱም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ይላል።—መክብብ 8:9
21. የአምላክ መንግሥት የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም በሚያደርግበት ጊዜ ምን ነገሮች ይከናወናሉ?
ራእይ 20:1-3) በዚያን ጊዜ የሚታመምም ሆነ የሚሞት ሰው አይኖርም። ኢየሱስ በከፈለው ቤዛ አማካኝነት ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ። (ራእይ 22:1-3) ከዚህም በላይ ይህ መንግሥት የአምላክ ስም እንዲቀደስ ያደርጋል። በሌላ አባባል የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚገዛበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁሉ የይሖዋን ስም ያከብራሉ።—ተጨማሪ ሐሳብ 21ን ተመልከት።
21 ከአርማጌዶን በኋላ የአምላክ መንግሥት፣ የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል። ሰይጣንንና አጋንንቱን ከምድር ላይ ያስወግዳል። (ኢየሱስ ንጉሥ የሆነው መቼ ነው?
22. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜም ሆነ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ እንደሄደ ንጉሥ ሆኖ አልተሾመም የምንለው ለምንድን ነው?
22 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። በመሆኑም በወቅቱ የአምላክ መንግሥት ገና አልተቋቋመም ነበር። ይሖዋ በቅድሚያ መንግሥቱን ካቋቋመ በኋላ ኢየሱስን የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ይሾመዋል። ይሁንና ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደሄደ ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል? አልተሾመም፤ የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ነበረበት። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስና ጳውሎስ የተናገሩት ሐሳብ ይህን ነጥብ ግልጽ ያደርግልናል፤ በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ጠቅሰዋል። በትንቢቱ ላይ ይሖዋ “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ [ተቀመጥ]” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32-35፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ታዲያ ኢየሱስ፣ ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ እስኪሾመው ድረስ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርበታል?
ሁለቱም ስለ ኢየሱስ ሲናገሩየአምላክ መንግሥት፣ የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል
23. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን ይብራራል?
23 ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች 1914 ከመድረሱ ከበርካታ ዓመታት በፊት ይህ ዓመት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ዓመት እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ከ1914 አንስቶ በዓለማችን ላይ የተፈጸሙት ሁኔታዎች እነዚህ ክርስቲያኖች ትክክል እንደነበሩ አረጋግጠዋል። ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው በዚያ ዓመት ነው። (መዝሙር 110:2) ኢየሱስ መግዛት እንደጀመረ ሰይጣን ወደ ምድር የተወረወረ ሲሆን አሁን ‘የቀረው ጥቂት ጊዜ ነው።’ (ራእይ 12:12) የሚቀጥለው ምዕራፍ፣ አሁን የምንኖረው ሰይጣን በቀረው ጥቂት ዘመን ላይ እንደሆነ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያስችሉንን ተጨማሪ ማስረጃዎች ያብራራል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም እንደሚያደርግ ይገልጻል።—ተጨማሪ ሐሳብ 22ን ተመልከት።