ምዕራፍ ሦስት
አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
1. አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
አምላክ ለሰው ልጆች አስደሳች ዓላማ አለው። የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን የፈጠረው ውብ በሆነ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲኖሩ ነበር። የአምላክ ዓላማ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ፣ መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጉና እንስሳትን እንዲንከባከቡ ነበር።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15፤ ተጨማሪ ሐሳብ 6ን ተመልከት።
2. (ሀ) አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) አምላክ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? የሚኖሩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?
2 በገነት ውስጥ የምንኖርበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል? ይሖዋ “ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11) አዎ፣ አምላክ ዓላማውን ይፈጽማል፤ ደግሞም እንዲህ እንዳያደርግ ሊከለክለው የሚችል ምንም ነገር የለም። ይሖዋ ምድርን የፈጠረው በዓላማ እንደሆነ ተናግሯል። ‘ምድርን የፈጠረው ለከንቱ’ አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) አምላክ የሰው ልጆች በመላዋ ምድር ላይ እንዲኖሩ ይፈልጋል። በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? የሚኖሩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን [ታዛዥ የሆኑ ሰዎች] ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4
3. የሰው ልጆች መታመማቸውና መሞታቸው ምን ጥያቄ ያስነሳል?
3 ሆኖም በዛሬው ጊዜ ሰዎች ይታመማሉ እንዲሁም ይሞታሉ። በብዙ ቦታዎች ሰዎች እርስ በርስ ይዋጋሉ እንዲሁም ይገዳደላሉ።
የአምላክ ዓላማ ይህ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? መልሱን ሊሰጠን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።የአምላክ ጠላት
4, 5. (ሀ) በኤደን የአትክልት ስፍራ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያናገራት ማን ነው? (ለ) ሐቀኛ የነበረ ሰው ሌባ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
4 አምላክ፣ “ዲያብሎስና ሰይጣን” ተብሎ የሚጠራ ጠላት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰይጣን፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ ተጠቅሞ ነበር። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:1) ሰይጣን፣ እባቡ እያወራ ያለ እንዲመስል አድርጎ ነበር።—ተጨማሪ ሐሳብ 7ን ተመልከት።
5 ይህን መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ዲያብሎስ አድርጎ የፈጠረው አምላክ ነው? በፍጹም! አምላክ ምድርን ለአዳምና ለሔዋን ምቹ መኖሪያ አድርጎ ሲያዘጋጃት አንድ መልአክ በሰማይ ሆኖ ይመለከት ነበር፤ ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። (ኢዮብ 38:4, 7) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ ወቅት ሐቀኛ የነበረ ሰው ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ሌባ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ሌባ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ የእሱ ያልሆነን ነገር ለማግኘት ይመኛል። ስለዚያ ነገር ማሰቡን ሲቀጥል ያን ነገር ለማግኘት ያለው ምኞት እየጨመረ ይሄዳል። ከዚያም ሁኔታዎች ሲመቻቹለት የተመኘውን ነገር ይሰርቃል። በዚህ መንገድ ሐቀኛ የነበረው ሰው ተለውጦ ሌባ ይሆናል።—ያዕቆብ 1:13-15ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 8ን ተመልከት።
6. አንድ መልአክ የአምላክ ጠላት የሆነው እንዴት ነው?
6 በተመሳሳይም ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። ይሖዋ፣ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ልጆች እንዲወልዱና ‘ምድርን እንዲሞሏት’ ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ይህ መልአክ፣ ‘ሰዎች በይሖዋ ፋንታ እኔን እንዲያመልኩ ማድረግ እኮ እችላለሁ!’ ብሎ አስቦ ይሆናል። ስለዚህ ነገር ባሰበ ቁጥር፣ ይህ ምኞቱ እየጨመረ ሄደ። መልአኩ ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ መውሰድ ፈለገ። ሰዎች እሱን እንዲያመልኩት ስለፈለገ ሔዋንን ውሸት በመናገር አታለላት። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ።) ይህ መልአክ እንዲህ በማድረግ ሰይጣን ዲያብሎስ ሆነ፤ በሌላ አነጋገር የአምላክ ጠላት ሆነ።
7. (ሀ) አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምንድን ነው? (ለ) የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?
7 አዳምና ሔዋን አምላክን አልታዘዙም፤ አትብሉ የተባሉትን ፍሬ በሉ። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6) በይሖዋ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ከጊዜ በኋላ ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:17-19) የአዳምና የሔዋን ልጆችም ኃጢአተኞች በመሆናቸው ሞተዋል። (ሮም 5:12ን አንብብ።) የአዳምና የሔዋን ልጆች ኃጢአተኛ የሆኑበትን ምክንያት ለመረዳት እንድንችል እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንዲት ሴት ስንጥቅ ባለው ምጣድ ላይ እንጀራ እየጋገረች ነው እንበል። እንጀራው በምጣዱ ላይ ያለውን ስንጥቅ ይዞ መውጣቱ አይቀርም። አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ኃጢአተኛ ሆኗል። ሁላችንም የአዳም ልጆች ነን፤ በመሆኑም እንጀራው የምጣዱን ስንጥቅ ይዞ እንደሚወጣ ሁሉ እኛም እንደ አዳም ኃጢአተኞች ሆነናል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን እናረጃለን ደግሞም እንሞታለን።—ሮም 3:23፤ ተጨማሪ ሐሳብ 9ን ተመልከት።
8, 9. (ሀ) ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ምን ብለው እንዲያስቡ ለማሳመን ጥረት አድርጓል? (ለ) ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?
8 ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ይሖዋን መታዘዝ እንደሌለባቸው ሲነግራቸው በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ እያደረጋቸው ነበር። አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋን ውሸታምና ለእነሱ የማያስብ ክፉ ገዢ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ለማሳመን ጥረት አድርጓል። በተዘዋዋሪ ሰይጣን ‘የሰው ልጆች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አምላክ ሊነግራቸው አይገባም’ ያለ ያህል ነው፤ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው ቢወስኑ የተሻለ እንደሆነ ገልጿል። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ማጥፋት ይችል ነበር። ይሁንና እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ሰይጣን የተናገረው ነገር ውሸት እንደሆነ ሊረጋገጥ ይችል ነበር? በፍጹም።
9 በመሆኑም ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ አላጠፋቸውም። ከዚህ ምዕራፍ 11 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ እንማራለን። ይሁንና አዳምና ሔዋን ስላደረጉት ነገር ምን ይሰማሃል? ሰይጣንን ማመናቸውና የአምላክን ትእዛዝ አለማክበራቸው ተገቢ ነው? ለአዳምና ለሔዋን ሁሉንም ነገር የሰጣቸው ይሖዋ ነው። ፍጹም ሕይወት፣ ውብ መኖሪያና አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸዋል። ሰይጣን ግን ምንም መልካም ነገር አድርጎላቸው አያውቅም። አንተ በአዳምና በሔዋን ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?
ይልቅ የሰው ልጆች ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ጊዜ ሰጣቸው። ይሖዋ እንዲህ ማድረጉ፣ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና ለሰው ልጆች የተሻለውን ነገር የሚያውቀው ይሖዋ እንደሆነ ለማሳየት ያስችላል።10. እያንዳንዳችን ምን ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል?
10 በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችን ተመሳሳይ ምርጫ ቀርቦልናል፤ ደግሞም ሕይወታችን የተመካው በምናደርገው ምርጫ ላይ ነው። ይሖዋን በመታዘዝና ለእሱ በመገዛት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት እንችላለን። አለዚያ የሰይጣን ተገዢዎች እንሆናለን። (መዝሙር 73:28፤ ምሳሌ 27:11ን አንብብ።) በዚህ ዓለም ላይ አምላክን የሚታዘዙት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። እንዲያውም ይህን ዓለም እየገዛ ያለው አምላክ አይደለም። ታዲያ ማን ነው?
ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው?
11, 12. (ሀ) ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት ግብዣ ምን ያሳያል? (ለ) ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዢ እንደሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
11 ኢየሱስ ዓለምን የሚገዛው ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።” ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ [ወይም ብትሰግድልኝ] እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” በማለት ቃል ገባለት። (ማቴዎስ 4:8, 9፤ ሉቃስ 4:5, 6) እስቲ አስበው፣ እነዚህ መንግሥታት የሰይጣን ባይሆኑ ኖሮ ለኢየሱስ በስጦታ መልክ ሊያቀርብለት ይችል ነበር? አይችልም። የዓለም መንግሥታት በሙሉ የሰይጣን ናቸው።
12 ይሁንና ‘ሰይጣን እንዴት የዚህ ዓለም ገዢ ሊሆን ይችላል? ጽንፈ ዓለሙን የፈጠረውና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይሖዋ አይደለም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። (ራእይ 4:11) እርግጥ ነው፣ ጽንፈ ዓለሙን የፈጠረው ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” ሰይጣን እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን ዲያብሎስን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ሐዋርያው ዮሐንስም “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” በማለት ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:19
የሰይጣን ዓለም የሚጠፋው እንዴት ነው?
13. አዲስ ዓለም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
13 በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ሄደዋል። በዓለም ላይ ጦርነት፣ ሙስና፣ አታላይነትና ዓመፅ በጣም ተስፋፍቷል። የሰው ልጆች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ እነዚህን ችግሮች ሊያስወግዱ አይችሉም። አምላክ ግን ይህን በክፋት የተሞላ ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት አስወግዶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያቋቁማል።—ራእይ 16:14-16፤ ተጨማሪ ሐሳብ 10ን ተመልከት።
14. የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?
14 ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማይ ያለው መስተዳድር ወይም መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “የሰላም መስፍን” ሆኖ እንደሚገዛና መንግሥቱም መጨረሻ እንደማይኖረው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።” (ማቴዎስ 6:10) በምዕራፍ 8 ላይ የአምላክ መንግሥት፣ የዓለምን መንግሥታት አጥፍቶ ብቻውን የሚገዛው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። (ዳንኤል 2:44ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት ምድር ውብ ገነት እንድትሆን ያደርጋል።—ተጨማሪ ሐሳብ 11ን ተመልከት።
አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!
15. “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?
15 መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል” በማለት ቃል ገብቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ዘፍጥረት 11:1) በመሆኑም ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ አምላክን የሚታዘዙና የእሱን በረከት የሚያገኙ ሰዎችን ያመለክታል።
16. አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ልዩ ስጦታ ይሰጣቸዋል? ይህን ስጦታ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 ኢየሱስ፣ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) ይህን ስጦታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እባክህ ዮሐንስ 3:16ን እና 17:3ን አንብብ። ምድር ገነት ስትሆን ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖሩ ይሆን? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።
17, 18. ወደፊት በምድር ሁሉ ላይ ሰላም እንደሚሰፍንና ተረጋግተን እንደምንኖር እንዴት ማወቅ እንችላለን?
17 ክፋት፣ ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመፅ አይኖርም። በምድር ላይ ክፉ ሰዎች ፈጽሞ አይኖሩም። (መዝሙር 37:10, 11) አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) ምድር አምላክን በሚወዱና እሱን በሚታዘዙ ሰዎች ትሞላለች። በምድር ላይ ለዘላለም ሰላም ይሰፍናል።—መዝሙር 72:7
18 የይሖዋ ሕዝቦች ተረጋግተው ይኖራሉ። በጥንት ዘመን እስራኤላውያን አምላክን ሲታዘዙ ጥበቃ ያደርግላቸው ስለነበር ተረጋግተው ይኖሩ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:18, 19) ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ምንጊዜም ተረጋግተን እንኖራለን!—ኢሳይያስ 32:18ን እና ሚክያስ 4:4ን አንብብ።
19. አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የተትረፈረፈ ምግብ እንደሚኖር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
19 የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል። “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።” (መዝሙር 72:16) ይሖዋ “አምላካችን ይባርከናል”፤ በመሆኑም “ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች።”—መዝሙር 67:6
20. ምድር ገነት እንደምትሆን እንዴት እናውቃለን?
20 መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። ሰዎች የሚያማምሩ ቤቶችና ኢሳይያስ 65:21-24ን እና ራእይ 11:18ን አንብብ።) መላዋ ምድር እንደ ኤደን ገነት ውብ ትሆናለች። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ” ይላል።—መዝሙር 145:16
የአትክልት ቦታዎች ይኖሯቸዋል። (21. ወደፊት ሰዎችና እንስሳት በሰላም እንደሚኖሩ እንዴት ማወቅ እንችላለን?
21 ሰዎችና እንስሳት በሰላም ይኖራሉ። በዚያን ጊዜ እንስሳት በሰው ልጆች ላይ ጉዳት አያደርሱም። አሁን የምንፈራቸውን አደገኛ እንስሳት ወደፊት ትናንሽ ልጆች እንኳ አይፈሯቸውም።—ኢሳይያስ 11:6-9ን እና 65:25ን አንብብ።
22. ወደፊት ኢየሱስ ለታመሙ ሰዎች ምን ያደርጋል?
22 የሚታመም ሰው አይኖርም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 5:5-9) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት የታመሙትን ሁሉ ይፈውሳል። በዚያን ጊዜ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6
23. የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
23 የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ። አምላክ በሞት ያንቀላፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት እንደሚያስነሳ ቃል ገብቷል። ‘ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት ይነሳሉ።’—ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
24. በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት በተመለከተ ምን ይሰማሃል?
24 ሁላችንም ምርጫ ቀርቦልናል። ስለ ይሖዋ መማርና እሱን ማገልገል እንችላለን፤ አለዚያ ደግሞ በመረጥነው መንገድ መኖር እንችላለን። ይሖዋን ለማገልገል ከመረጥን አስደሳች ተስፋ ይጠብቀናል። ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 23:43) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንማራለን፤ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠንን አስደሳች ተስፋዎች የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።