በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

ምዕራፍ 24

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

ሣራ ከናታን ጋር የፍቅር ጓደኝነት ከጀመረች ገና ሁለት ወሯ ቢሆንም ዕድሜዋን ሁሉ እንደምታውቀው ሆኖ ይሰማታል። አዘውትረው በሞባይል መልእክት ይለዋወጣሉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በስልክ ለሰዓታት ያወራሉ፣ እንዲሁም እርስ በርስ ይናበባሉ! ዛሬም በጨረቃ በደመቀው ምሽት መኪናቸውን አቁመው እያወሩ ነው፤ ናታን ግን ከወሬ ያለፈ ነገር እንዲያደርጉ ፈልጓል።

ባለፉት ሁለት ወራት ናታንና ሣራ እጅ ለእጅ ከመያያዝና ለሰላምታ ያህል ከንፈር ለከንፈር ከመሳሳም ያለፈ ምንም ነገር አድርገው አያውቁም። ሣራ ከዚህ እንዲያልፉ አትፈልግም። በሌላ በኩል ደግሞ ናታንን እንዳታጣው ፈርታለች። ናታን በጣም ቆንጆና ልዩ እንደሆነች እንዲሰማት ያደርጋታል። ‘ደግሞም እኔና ናታን እስከተዋደድን ድረስ ምን ችግር አለው?’ በማለት ከራሷ ጋር ትሟገታለች።

ሣራና ናታን ወዴት እያመሩ እንደሆነ መገመት አያቅትሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው በሕይወታቸው ላይ ምን ያህል መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ላትገነዘቢ ትችያለሽ። እስቲ የሚከተለውን አስቢ፦

እንደ ስበት ሕግ ያሉ የተፈጥሮ ሕጎችን ብትጥሺ እንዲህ ማድረግ ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አትችዪም። ‘ከዝሙት ራቁ’ እንደሚለው ያለውን የሥነ ምግባር ሕግ ብትጥሺም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ይህን ትእዛዝ መጣስ ምን መዘዝ ያስከትላል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዝሙት የሚፈጽም ሰው በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው’ ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? እስቲ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትላቸውን ሦስት ጉዳቶች ቀጥሎ ባሉት ክፍት ቦታዎች ላይ ለመጻፍ ሞክሪ።

1 ․․․․․

2 ․․․․․

3 ․․․․․

የጻፍሽውን ነገር መለስ ብለሽ ተመልከቺው። ከጻፍሻቸው ነገሮች መካከል የአባለ ዘር በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና ወይም የአምላክን ሞገስ ማጣት የሚሉት ይገኙበታል? አምላክ ዝሙትን አስመልክቶ የሰጠውን የሥነ ምግባር ሕግ የሚጥሱ ሰዎች እንደ እነዚህ ያሉ አስከፊ መዘዞች እንደሚያጋጥሟቸው የታወቀ ነው።

ያም ሆኖ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ትፈተኚ ይሆናል። ‘እንዲህ ባደርግ ምንም አልሆንም’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ደግሞስ ሁሉም ሰው የፆታ ግንኙነት ይፈጽም የለ? በትምህርት ቤት ያሉት እኩዮችሽ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸውን እንደ ጀብዱ አድርገው ያወሩታል፤ ደግሞም ይህን በማድረጋቸው እነሱ ምንም ዓይነት ጉዳት የደረሰባቸው አይመስሉም። ምናልባትም በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰችው እንደ ሣራ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ከፍቅር ጓደኛሽ ጋር ይበልጥ እንደሚያቀራርባችሁ ይሰማሽ ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ድንግል በመሆንሽ እንዲቀለድብሽ አትፈልጊም። ታዲያ ከዚህ ሁሉ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ የሚቀርብልሽን ጥያቄ ብትቀበዪ አይሻልም?

እስቲ ቆም ብለሽ ለማሰብ ሞክሪ! ከሁሉ በፊት ማወቅ ያለብሽ ነገር ቢኖር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽመው ሁሉም ሰው አለመሆኑን ነው። እውነት ነው፣ በርካታ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ የሚገልጽ አኃዛዊ መረጃ ተመልክተሽ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአገሪቱ ከሚኖሩ 3 ወጣቶች መካከል 2ቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ ይኸው አኃዝ እንደሚያመለክተው ከ3 ወጣቶች 1ዱ የፆታ ግንኙነት እንደማይፈጽም ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም። ይሁንና የፆታ ግንኙነት ስለሚፈጽሙት ወጣቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ተመራማሪዎች እንደገለጹት ከእነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ከታች እንደተዘረዘሩት ያሉ ያልጠበቋቸው ሁኔታዎች ወይም ዱብ ዕዳዎች አጋጥመዋቸዋል።

ዱብ ዕዳ 1 ጸጸት። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አብዛኞቹ ወጣቶች በኋላ ላይ በድርጊታቸው እንደተቆጩ ተናግረዋል።

ዱብ ዕዳ 2 አለመተማመን። ወጣቶቹ የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ‘ከእኔ ሌላ ከማን ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽማ/ፈጽሞ ይሆን?’ እያሉ ማሰብ ይጀምራሉ።

ዱብ ዕዳ 3 ግራ መጋባት። ማንም ሴት ብትሆን የወንድ ጓደኛዋ ከጉዳት እንዲጠብቃት እንጂ መጠቀሚያ እንዲያደርጋት አትፈልግም። ብዙዎቹ ወንዶች ደግሞ ከአንዲት ሴት የፈለጉትን ካገኙ በኋላ ያቺ ሴት ያን ያህል አትማርካቸውም።

ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ብዙ ወጣት ወንዶች ከአንዲት ሴት ጋር የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ከእሷ ጋር ትዳር መመሥረት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ለምን? ንጽሕናዋን የጠበቀች ወጣት ማግባት ስለሚመርጡ ነው!

ይህ ያስገርምሽ አልፎ ተርፎም ያናድድሽ ይሆናል። ከሆነ ልታስታውሺው የሚገባ አንድ ሐቅ አለ፦ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ እውነታው በፊልምና በቴሌቪዥን ላይ ከሚቀርበው በጣም የተለየ ነው። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው በጣም አስደሳችና ምንም ጉዳት የሌለው ነገር እንደሆነ አልፎ ተርፎም እነዚህ ወጣቶች ከልባቸው እንደሚዋደዱ የሚያሳይ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ይሁን እንጂ በዚህ አትሞኚ! ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ የሚያባብሉሽ ሁሉ ይህን የሚያደርጉት የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) አንድ ሰው እውነት የሚወድሽ ከሆነ አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት የሚያስከትልብሽ ነገር እንድታደርጊ ይገፋፋሻል? (ምሳሌ 5:3, 4) ደግሞስ ከልቡ የሚያስብልሽ ሰው ከአምላክ ጋር ያለሽን ዝምድና የሚያበላሽ ድርጊት እንድትፈጽሚ ይጠይቅሻል?—ዕብራውያን 13:4

ወደ ወንዶች ስንመጣ ደግሞ፣ ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ጀምረህ ከሆነ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ስለ ግንኙነታችሁ በቁም ነገር እንድታስብ ሊያደርጉህ ይገባል። ‘ለሴት ጓደኛዬ ከልቤ አስብላታለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። መልስህ ‘አዎ’ ከሆነ ይህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክን ሕጎች ለማክበር የሚያስችል ጥንካሬ እና ወደ ፈተና ሊያስገቡ ከሚችሉ ሁኔታዎች ለመራቅ የሚረዳ ጥበብ እንዳለህ በማሳየት ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ለሴት ጓደኛህ በማሰብ ለእሷ ፍቅር እንዳለህ አሳይ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሴት ጓደኛህ “ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ” በማለት እንደተናገረችው ጥሩ ሥነ ምግባር ያላት ሱላማጢስ ልጃገረድ ዓይነት ስሜት ይኖራታል። (ማሕልየ መሓልይ 2:16) በአጭሩ፣ ከልቧ ታደንቅሃለች!

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ በጣም ውድ የሆነ ነገርን አውጥተው የጣሉ ያህል ነው፤ እንዲህ ሲያደርጉ ራሳቸውን ያዋርዳሉ። (ሮም 1:24) ብዙዎች የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ በጣም ውድ የሆነ ነገር የተነጠቁ ያህል የባዶነትና የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑ ምንም አያስደንቅም! ይህ ሁኔታ በአንቺ ላይ እንዲደርስ አትፍቀጂ! አንድ ሰው “ብትወጂኝ ኖሮ እሺ ትዪኝ ነበር” እያለ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ ሊያባብልሽ ከሞከረ ፈርጠም ብለሽ “አንተም ብትወደኝ ኖሮ እንዲህ ያለ ነገር አትጠይቀኝም ነበር!” በማለት መልሺለት።

ሰውነትሽን እንደ ውድ ነገር ልትመለከቺው ይገባል፤ እንደማይረባ ነገር አታቃልዪው። አምላክ ከዝሙት እንድንርቅ የሰጠውን ትእዛዝ ለመጠበቅ የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለሽ በተግባር አሳዪ። ደግሞም የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ስታገቢ ትደርሺበታለሽ። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ከሚያስከትለው ጭንቀትና ጸጸት ነፃ ሆነሽ በፆታ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ ሙሉ በሙሉ ማጣጣም የምትችዪው ካገባሽ በኋላ ነው።—ምሳሌ 7:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 4 እና 5 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ማስተርቤሽን ያን ያህል ስህተት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

‘ከዝሙት ሽሹ። ዝሙት የሚፈጽም ሰው በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።’—1 ቆሮንቶስ 6:18

ጠቃሚ ምክር

ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ የሚከተለው ሐሳብ ጥሩ መመሪያ ይሆንሻል፦ ወላጆችሽ ቢኖሩ ኖሮ የማታደርጊውን ነገር በሌላ ጊዜም ልታደርጊው አይገባም።

ይህን ታውቅ ነበር?

አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ከአንዲት ሴት ጋር የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ እሷን ትተው ከሌላ ሴት ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት ይፈልጋሉ።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ከተቃራኒ ፆታ ጋር በምሆንበት ጊዜ ከሚከተሉት ሁኔታዎች መራቅ ይኖርብኛል፦ ․․․․․

አንድ ወጣት ጭር ባለ አካባቢ እንድንገናኝ ቢጠይቀኝ እንዲህ እለዋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አስደሳች ቢመስልም ይህን ማድረግ ትክክል ያልሆነው ለምንድን ነው?

● አንድ ሰው የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ቢጠይቅሽ ምን ታደርጊያለሽ?

[በገጽ 176 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ክርስቲያን በመሆናችን በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንድንሆን የሚያደርጉን ባሕርያት አሉን። ስለዚህ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም ስንጠየቅ ንቁ መሆንና ጥያቄውን መቃወም ይኖርብናል። ላሉን መልካም ባሕርያት ትልቅ ቦታ ልንሰጥ ይገባል። በማይረባ ነገር አንለውጣቸው!”—ጆሽዋ

[በገጽ 176 እና 177 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድን ውብ ሥዕል የበር ምንጣፍ እንደ ማድረግ ነው