በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 28

ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

መቼም በጣም ሳትደመም አልቀረችም። ስላሉኝ ነገሮች፣ ስላየኋቸው ቦታዎችና ስለማውቃቸው ሰዎች ሁሉ አንድም ሳላስቀር አውርቼላታለሁ። ለጓደኝነት ብጠይቃት ዓይኗን ሳታሽ እሺ እንደምትለኝ እርግጠኛ ነኝ!

ምነው መሬት ተከፍታ በዋጠችኝ! በዘዴ ልነግረው ብሞክርም ሊገባው አልቻለም። ሳላስቀይመው ከዚህ ልጅ መገላገል የምችለው እንዴት ነው?

የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ደርሰሃል እንበል። የአንተ ዓይነት እምነት ካላት ቆንጆ ወጣት ጋር ጓደኝነት ብትመሠርት ደስ ይልሃል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይሁንና ከዚህ በፊት የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት በሞከርክ ቁጥር አልሳካ እያለህ ተቸግረህ ይሆናል። ችግሩ ምን ይሆን? ሴቶች የሚፈልጉት መልከ መልካም ወንዶችን ብቻ ነው? ሊሳ የተባለች ወጣት “ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው ወንድ ደስ ይለኛል” ብላለች። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሴቶች ትኩረት የሚያደርጉት መልክና ቁመና ላይ ብቻ አይደለም። የ18 ዓመቷ ኬሪ “መልከ ቀና የሆኑት ወንዶች ብዙውን ጊዜ ቁም ነገር የላቸውም” በማለት ተናግራለች።

ታዲያ ‘ቁም ነገር ያለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? አንዲትን ወጣት ቀርበህ ለማወቅ ከፈለግክ ልታስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ልታስታውሳቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችስ የትኞቹ ናቸው?

ሊቀድም የሚገባው ነገር

ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ጥያቄ ከማቅረብህ በፊት ልትሠራባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ እነዚህ ነገሮች ከማንኛውም ሰው ጋር ጓደኝነት ለመመሥረትም ይረዱሃል። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

መልካም ምግባር ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “[ፍቅር] ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) ሌሎችን በማክበር እንዲሁም ብስለት እንዳለህና ክርስቶስን እንደምትመስል የሚያሳዩ ባሕርያትን በማፍራት መልካም ምግባር እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። ይሁን እንጂ መልካም ምግባር ከሌሎች ጋር ስትሆን እንደምትደርበውና ቤትህ ስትደርስ አውልቀህ እንደምትጥለው ልብስ አይደለም። ‘ከቤተሰቦቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት መልካም ምግባር እንዳለኝ አሳያለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በቤት ውስጥ መልካም ምግባር ከሌለህ ከሌሎች ጋር በምትሆንበት ጊዜ ጥሩ ጠባይ ለማሳየት ብትሞክር እያስመሰልክ እንደሆነ ይታወቅብሃል። አስተዋይ የሆነች ወጣት ደግሞ እውነተኛ ማንነትህን ለማወቅ ቤተሰቦችህን የምትይዝበትን መንገድ መመልከቷ አይቀርም።—ኤፌሶን 6:1, 2

ሴቶች ምን ይላሉ? “በትናንሽም ሆነ በትላልቅ ነገሮች መልካም ምግባር የሚያሳይ ወንድ ደስ ይለኛል፤ ለምሳሌ በር ከፍቶ ቢያስገባኝ ወይም ደግሞ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቼም ጭምር ደግነትና አሳቢነት ቢያሳየን መልካም ምግባር እንዳለው ይሰማኛል።”—ቲና

“ገና ከመተዋወቃችን ‘የወንድ ጓደኛ አለሽ?’ ወይም ‘ግብሽ ምንድን ነው?’ እንደሚሉት ያሉ የግል ሕይወቴን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን የሚጠይቀኝ ወንድ ይደብረኛል፤ እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያስጨንቅ ከመሆኑም ሌላ ተገቢ አይደለም!”—ካቲ

“ሴቶች ስሜት የሌለን ይመስል በእኛ ለመጫወት የሚሞክሩ ወንዶች አሉ፤ እነዚህ ወንዶች፣ ሁሉም ሴቶች ለማግባት በጣም እንደሚጓጉ ስለሚያስቡ ከእኛ ጋር ሲሆኑ ትልቅ ውለታ እንደዋሉልን አድርገው ይቆጥሩታል። ለሴቶች አክብሮት ያለው ወንድ እንዲህ እንደማያደርግ ይሰማኛል።”—አሌክሲስ

ንጽሕናህን ጠብቅ። ንጽሕናህን በሚገባ መጠበቅህ ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለራስህም አክብሮት እንዳለህ ያሳያል። (ማቴዎስ 7:12) ለራስህ አክብሮት ካለህ ደግሞ ሌሎችም እንደሚያከብሩህ ጥርጥር የለውም። በአንጻሩ ግን ለንጽሕናህ ትኩረት የማትሰጥ ከሆነ አንዲትን ወጣት ለመማረክ የምታደርገው ጥረት መና ይቀራል።

ሴቶች ምን ይላሉ? “ከእኔ ጋር ለመቀራረብ ይፈልግ የነበረ አንድ ወጣት መጥፎ የአፍ ጠረን ነበረው። ይህን በፍጹም ችላ ብዬ ማለፍ አልቻልኩም።”—ኬሊ

የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አዳብር። የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ማዳበር ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ወሳኝ ነው። ከአንዲት ሴት ጋር ስትጨዋወት ስለ ራስህ ብቻ ከማውራት ይልቅ እሷም ስለ ራሷ እንድትናገር እድል ስጣት። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) ሐሳቧን ስትገልጽ ከልብህ አዳምጥ እንዲሁም አመለካከቷን እንደምታከብር አሳይ።

ሴቶች ምን ይላሉ? “ራሱን ሆኖ የሚያዋራኝ፣ የነገርኩትን የሚያስታውስና ጥያቄዎችን እየጠየቀ ጨዋታው እንዲቀጥል የሚያደርግ ወንድ ይማርከኛል።”—ክሪስቲን

“እኔ እንደሚመስለኝ ወንዶችን የሚማርካቸው የሚያዩት ነገር ሲሆን ሴቶችን የበለጠ የሚማርካቸው ግን የሚሰሙት ነገር ነው።”—ሎራ

“ስጦታ ሲሰጠኝ ደስ ቢለኝም ጨዋታ የሚያውቅ እንዲሁም ማጽናናትና ማበረታታት የሚችል ወንድ ከተገኘ . . . በጣም አሪፍ ነው!”—ኤሚ

“ትሑት የሆነና ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን የማያሳይ አንድ ወጣት አውቃለሁ። ‘መዓዛሽ ደስ ይላል’ ወይም ‘ዛሬ በጣም አምሮብሻል’ እንደሚሉ ያሉ አባባሎችን መጠቀም ሳያስፈልገው ቁም ነገር ያለው ወሬ ማውራት እንችላለን። ሳዋራው ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጠኛል፤ ማንኛዋም ሴት ብትሆን ከእንዲህ ዓይነት ወንድ ጋር መሆን ያስደስታታል።”—ቤት

“ቀልድ ከሚያውቅ በሌላ በኩል ደግሞ ቁም ነገርም ማውራት ከሚችል ወንድ ጋር ጓደኝነት ብመሠርት ደስ ይለኛል።”—ኬሊ

ኃላፊነት የሚሰማህ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ይላል። (ገላትያ 6:5) ብዙ ሴቶች ሰነፍ የሆነ፣ አብዛኛውን ጊዜውን በዋዛ በፈዛዛ የሚያጠፋና በዚህም ምክንያት ቋሚ ሥራ የሌለው ወንድ አይወዱም።

ሴቶች ምን ይላሉ? “አንዳንድ ወንዶች ኃላፊነት የሚሰማቸው ቢሆኑ ጥሩ ነበር። አንድ ወንድ ኃላፊነት የሚሰማው ካልሆነ ጨርሶ አይማርከኝም። እንደዚህ ላለው ወንድ ጥሩ ግምት ሊኖረኝ አይችልም።”—ኬሪ

“አንዳንድ ወንዶች በሕይወታቸው ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ አያውቁም። አንዲት ልጅ ከወደዱ የእሷ ግቦች ምን እንደሆኑ ይጠይቁና ‘በጣም ይገርማል! የእኔም ግብ ይሄ ነው’ ይላሉ። ትክክለኛ ግባቸው ይህ እንዳልሆነ ግን ድርጊታቸው ያሳብቅባቸዋል።”—ቤት

ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች እንደሚያሳዩት ኃላፊነት የሚሰማህ መሆንህ ጥሩ ጓደኞች ለማፍራት ያስችልሃል። አሁን ግን ከጓደኞችህ መካከል ከአንዷ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈለግህ እንበል፤ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ቀጣዩ እርምጃ

ቅድሚያውን ውሰድ። ከጓደኞችህ መካከል አንዷ ጥሩ የትዳር ጓደኛ እንደምትሆንህ ካሰብክ ስሜትህን ግለጽላት። ይህን ስታደርግ ግልጽና ቀጥተኛ ሁን። እርግጥ ነው፣ ልጅቷን መጠየቅ በጣም ሊያስጨንቅህ ይችላል። ምክንያቱም ‘እሺ ባትለኝስ’ ብለህ ትፈራ ይሆናል። ሆኖም ቅድሚያውን ወስደህ ስሜትህን መግለጽህ በራሱ ብስለት እንዳለህ ያሳያል። ይሁንና ልትጠነቀቅበት የሚገባ ነገር አለ፤ እየጠየቅሃት ያለኸው እንድትጠናኑ እንጂ እንድትጋቡ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። ስለዚህ አስተዋይ ሁን። ጥያቄውን የምታቀርብበት መንገድ ልጅቷ አንድ ዓይነት ግዴታ ውስጥ እንድትገባ እየጠየቅሃት እንደሆነ እንዲሰማት የሚያደርግ መሆን የለበትም፤ እንዲህ ካደረግህ ጥያቄህን ከመቀበል ይልቅ ልትርቅህ ትችላለች።

ሴቶች ምን ይላሉ? “የሰውን ልብ ማንበብ አልችልም። ስለሆነም አንድ ወንድ እንድንጠናና ከፈለገ ስሜቱን በግልጽ ሊነግረኝ ይገባል።”—ኒና

“አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጓደኛሞች ከነበሩ የፍቅር ጥያቄ ማቅረብ ሊከብድ ይችላል። ያም ቢሆን አንድ ጓደኛዬ የፍቅር ግንኙነት እንድንጀምር ከፈለገ ይህን በግልጽ ቢነግረኝ አከብረዋለሁ።”—ሄለን

ውሳኔዋን አክብርላት። ጓደኛህ ያቀረብክላትን ጥያቄ ባትቀበለውስ? ልጅቷ የምትፈልገውን እንደምታውቅና ‘አይሆንም’ ያለችው ከልቧ እንደሆነ በመቀበል እንደምታከብራት አሳይ። በሌላ በኩል ግን ‘እሺ ካላልሽኝ’ ብለህ የምትነዘንዛት ከሆነ ብስለት እንደሚጎድልህ እያሳየህ ነው። ያቀረብከውን ጥያቄ እንደማትቀበለው በግልጽ ብትነግርህም የማትሰማ ይባስ ብሎም በሰጠችው ምላሽ የምትበሳጭ ከሆነ የእሷን ፍላጎት ከግምት አስገብተሃል ማለት ይቻላል? ወይስ እያሰብክ ያለኸው ስለ ራስህ ብቻ ነው?—1 ቆሮንቶስ 13:11

ሴቶች ምን ይላሉ? “እንደማልፈልግ በግልጽ ከነገርኩት በኋላ ደጋግሞ የሚጠይቀኝ ወንድ ያበሳጨኛል።”—ካሊን

“አንድ ልጅ ከእሱ ጋር የፍቅር ጓደኝነት የመመሥረት ፍላጎት እንደሌለኝ ብገልጽለትም የስልክ ቁጥሬን እንድሰጠው መወትወቱን አላቆመም። እኔ ደግሞ ላስቀይመው አልፈለግሁም። ስሜቱን አውጥቶ ለመናገር ብዙ ተጨንቆ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቶኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን ውሳኔዬን ጠንከር ባለ መንገድ መንገር አስፈልጎኛል።”—ሣራ

ማድረግ የሌለብህ ነገር

አንዳንድ ወጣት ወንዶች፣ በቀላሉ ሴቶችን መማረክ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እንዲያውም ‘የብዙ ሴቶችን ልብ ማማለል የሚችለው ማን ነው?’ በሚል እርስ በርስ ይፎካከሩ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ድርጊት ደግነት የጎደለው ከመሆኑም ሌላ መጥፎ ስም እንድታተርፍ ያደርግሃል። (ምሳሌ 20:11) የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግህ መጥፎ ስም ከማትረፍ ይጠብቅሃል።

አታሽኮርምም። አንድ ወንድ የሽንገላ ቃላት በመጠቀም ወይም በአኳኋኑ አንዲትን ሴት ያሽኮረምም ይሆናል። ይህ ሰው እንዲህ የሚያደርገው ከእሷ ጋር በቁም ነገር የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ዓላማ ሳይኖረው ነው። እንዲህ ያለው ድርጊትና ዝንባሌ “ወጣት ሴቶችን . . . እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይጋጫል። (1 ጢሞቴዎስ 5:2) የማሽኮርመም ልማድ ያላቸው ወንዶች ለትዳር ጓደኝነት ይቅርና ጥሩ ጓደኞች ለመሆን እንኳ አይበቁም። አስተዋይ የሆኑ ሴቶች ደግሞ ይህን ማወቅ አይቸግራቸውም።

ሴቶች ምን ይላሉ? “አንድ ወንድ ባለፈው ወር ለጓደኛችሁ የተናገረውን ነገር ለእናንተም እየደገመ ሲሸነግላችሁ መስማት በጣም ይደብራል።”—ሄለን

“አንድ የሚያምር ልጅ እኔን ለማሽኮርመም ይሞክር ነበር፤ በአብዛኛው ያወራ የነበረው ስለ ራሱ ነው። በመሃል አንዲት ልጅ ስትመጣ እሷንም እንደዚያው ማሽኮርመም ጀመረ። አሁንም ሌላ ወጣት ወደ እኛ ስትመጣ ለእሷም ተመሳሳይ ነገር አላት። ሁኔታው በጣም ያስጠላ ነበር!”—ቲና

በስሜቷ አትጫወት። ከሴቶች ጋር የሚኖርህ ጓደኝነት ከወንዶች ጋር ካለህ ወዳጅነት እንደማይለይ አድርገህ አታስብ። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ይህን አስብ፦ አንድ ጓደኛህ ልብሱ እንዳማረበት ብትነግረው ወይም ብዙ ጊዜ የምታዋራው ቢሆንና ሚስጥረኛህ ብታደርገው ለእሱ የፍቅር ስሜት እንዳለህ አድርጎ እንደማያስብ የታወቀ ነው። አንዲትን ሴት ግን አለባበሷን ብታደንቅላት ወይም ደግሞ ሁልጊዜ ከእሷ ጋር ብታወራና ሚስጥረኛህ ብታደርጋት ከእሷ ጋር የፍቅር ጓደኝነት የመመሥረት ፍላጎት እንዳለህ ልታስብ ትችላለች።

ሴቶች ምን ይላሉ? “ወንዶች፣ ከሴቶች ጋር የሚኖራቸው ቅርበት ከወንዶች ጋር ካላቸው ቅርበት የተለየ መሆን እንዳለበት የሚገባቸው አይመስለኝም።”—ሼረል

“አንድ ወንድ ስልክ ቁጥሬን ወስዶ መልእክት ይልክልኛል። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? አንዲት ልጅ የስልክ መልእክት በመለዋወጥ ብቻ ከአንድ ወንድ ጋር ጓደኝነት ልትመሠርትና ፍቅር ሊይዛት ይችላል፤ ሆኖም የስልክ መልእክት በመላላክ ብቻ አንድን ሰው ምን ያህል ማወቅ ይቻላል?”—ማለሪ

“አንድ ወንድ በተለይ አሳቢና በቀላሉ የሚቀረብ ከሆነ አንዲት ሴት ቶሎ ልትወደው እንደምትችል ወንዶች የሚገባቸው አይመስለኝም። ይህች ሴት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገባው ባል ለማግኘት በጣም ስለምትጓጓ አይደለም። አብዛኞቹ ሴቶች የሚወዱት ሰው ማግኘት ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም የሚስማማቸው ዓይነት ሰው ለማግኘት ይሞክራሉ።”—አሊሰን

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 3 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

እውነተኛ ፍቅርን ከወረት ፍቅር መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

“እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና [ልበሱ]።”—ኤፌሶን 4:24

ጠቃሚ ምክር

አንድ ወጣት ሊያዳብራቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ ባሕርያትና ችሎታዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ብስለት ያላቸው አዋቂ ሰዎችን አማክር፤ ከዚያም በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ እንደሆነ ራስህን ገምግም።

ይህን ታውቅ ነበር?

ከመልክና ቁመናህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውስጣዊ ማንነትህ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

መልካም ምግባር በማዳበር ረገድ ልሠራበት የሚገባ ነጥብ ․․․․․

የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታዬን ለማሻሻል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ለራስህ አክብሮት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

● የአንዲትን ወጣት አመለካከትም ሆነ ስሜት እንደምታከብር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 198 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ብዙ ወንዶች፣ ሴቶችን የሚማርካቸው ለየት ያለ አለባበስ ወይም ቁመና እንደሆነ ያስባሉ። ይህ በተወሰነ መጠን እውነት ቢሆንም ብዙ ሴቶችን ይበልጥ የሚማርካቸው አንድ ወንድ ጥሩ ባሕርያት ያሉት መሆኑ ነው።”—ኬት

[በገጽ 197 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መልካም ምግባር ከሌሎች ጋር ስትሆን እንደምትደርበውና ቤትህ ስትደርስ አውልቀህ እንደምትጥለው ልብስ አይደለም