በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ላድርግ?

ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ላድርግ?

ምዕራፍ 21

ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ላድርግ?

በቀን ውስጥ ምን ያህል ተጨማሪ ሰዓት ብታገኝ ደስ ይልሃል?

ተጨማሪ ሰዓት ማግኘት የምትፈልገው ለምንድን ነው?

□ ከጓደኞቼ ጋር ለመሆን

□ ለመተኛት

□ ለማጥናት

□ ሌላ ․․․․․

ጊዜ በፍጥነት እንደሚጋልብ ፈረስ ነው፤ በአግባቡ ልትጠቀምበት ከፈለግህ እንዴት እንደምትቆጣጠረው ማወቅ አለብህ። ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም ከቻልክ ያለብህን ውጥረት መቀነስ፣ በትምህርት ጥሩ ውጤት ማምጣት እንዲሁም ወላጆችህ ይበልጥ እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ ትችላለህ። “ቢሆንማ ጥሩ ነው፤ ግን ይህን ማድረጉ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም!” ትል ይሆናል። እርግጥ ነው፣ በዚህ ረገድ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊገጥሙህ ይችላሉ። ይሁንና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ልትወጣቸው ትችላለህ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ #1፦ ፕሮግራም ማውጣት

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። በፕሮግራም መመራት የሚለውን ነገር ገና ስታስበው መፈናፈኛ እንደምታጣ ይሰማህ ይሆናል! ማንኛውንም ነገር ባሰኘህ ሰዓት ማድረግ እንጂ እያንዳንዱን ነገር በፕሮግራም ማከናወን አትፈልግ ይሆናል።

ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ንጉሥ ሰለሞን “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 21:5) ሰለሞን ሥራ የሚበዛበት ሰው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ባለትዳርና የልጆች አባት እንዲሁም ንጉሥ ነበር። ዕድሜው እየገፋ ሲሄድም ፕሮግራሙ ይበልጥ እየተጣበበ የመጣ ይመስላል። አንተም ጊዜ እንደሚያጥርህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ ሕይወትህ ይበልጥ በሥራ የተወጠረ መሆኑ አይቀርም። እንግዲያው ከአሁኑ በፕሮግራም መመራትን ብትለምድ የተሻለ ነው!

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “በቋሚነት ፕሮግራም ማውጣት ከጀመርኩ ስድስት ወር ገደማ ይሆነኛል። ይህን ያደረግኩት ጊዜዬ በጣም የተጣበበ ስለነበር ነው፤ በፕሮግራም መመራቴ ሕይወቴን ቀላል ለማድረግ ጠቅሞኛል።”—ጆዪ

“ላደርጋቸው ያሰብኳቸውን ነገሮች በዝርዝር መጻፌ ፕሮግራሜን እንድከተል ረድቶኛል። ማከናወን የሚኖርብኝ ተጨማሪ ነገር ሲኖር ደግሞ እኔና እናቴ ሁሉንም ነገር በዝርዝር እንጽፋለን፤ ከዚያም ተረዳድተን ግቦቻችን ላይ መድረስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንነጋገራለን።”—ማለሪ

ምን ሊረዳህ ይችላል? እስቲ ነገሩን በዚህ መልክ ለማሰብ ሞክር፦ ከቤተሰብህ ጋር ወደ አንድ ቦታ ልትጓዙ አስባችኋል እንበል። ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸውን ሻንጣ የመኪናው ዕቃ መጫኛ ውስጥ ዝም ብለው ቢያጉሩት ምን የሚፈጠር ይመስልሃል? ቦታው የሚበቃ ላይመስል ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሁሉንም ሻንጣዎች ካወጣህ በኋላ መጀመሪያ ትላልቆቹን ሻንጣዎች አስገባ፤ ከዚያም ትናንሾቹን ሻንጣዎች የቀረው ቦታ ላይ ማስገባት ትችላለህ።

ከጊዜ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም ትችላለህ። ጊዜህን ያን ያህል አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች ካስያዝክ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ለማግኘት ልትቸገር ትችላለህ። በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በቅድሚያ አከናውን፤ ይህን ካደረግህ በኋላ ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚተርፍህ ስታይ መገረምህ አይቀርም!—ፊልጵስዩስ 1:10

ልታደርጋቸው የሚገቡ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

․․․․․

አሁን ደግሞ የጻፍካቸውን ነገሮች ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው ከሚገባው ጀምረህ በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው። አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በቅድሚያ የምታከናውን ከሆነ ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችል ብዙ ጊዜ ታተርፋለህ።

ምን ማድረግ ትችላለህ? የቀን መቁጠሪያ ያለው በኪስ የሚያዝ ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅተህ ማከናወን ያለብህን ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጠው ከሚገባው ጀምረህ በቅደም ተከተል ጻፋቸው። የቀን መቁጠሪያ ባለው ማስታወሻ ደብተር ፋንታ ከዚህ ቀጥሎ ከቀረቡት አማራጮች መካከል አንዱን መጠቀምም ትችላለህ።

□ የሞባይል ስልክ የቀን መቁጠሪያ

□ አነስ ያለ ማስታወሻ ደብተር

□ የኮምፒውተር የቀን መቁጠሪያ

□ ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጥ የቀን መቁጠሪያ

ተፈታታኝ ሁኔታ #2፦ ፕሮግራምህን በጥብቅ መከተል

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። ከትምህርት ቤት እንደተመለስክ ቴሌቪዥን እያየህ ትንሽ ዘና ማለት ትፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ ፈተና ኖሮህ ለማጥናት አቅደህ ሳለ ጓደኞችህ ‘ሲኒማ እንግባ’ የሚል መልእክት ላኩልህ እንበል። ‘ፊልሙ የሚታይበት ሰዓት ሊለወጥ አይችልም፤ ጥናቴን ግን ማታ ስመለስ ልደርስበት እችላለሁ። በዚያ ላይ ደግሞ ፈተና ላይ በደንብ የምሠራው ባለቀ ሰዓት ሳጠና ነው’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? አእምሮህ የበለጠ ንቁ እያለ ብታጠና የተሻለ ውጤት ልታመጣ ትችላለህ። ደግሞስ ያለብህ ውጥረት ሳያንስ ሌሊቱን በችኮላ ለማጥናት በመሞከር በራስህ ላይ ለምን ሌላ ውጥረት ትጨምራለህ? በዚያ ላይ በማግስቱ ጠዋት ምን ሊከሰት እንደሚችል እስቲ አስብ። ከእንቅልፍህ አርፍደህ ብትነቃ የበለጠ ትወጣጠራለህ፤ ከዚህም ሌላ ከቤት ተጣድፈህ ልትወጣ ወይም ትምህርት ቤት ዘግይተህ ልትደርስ ትችላለህ።—ምሳሌ 6:10, 11

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “ቴሌቪዥን ማየት፣ ጊታር መጫወትና ከጓደኞቼ ጋር መሆን በጣም ያስደስተኛል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ በራሱ ስህተት ባይሆንም ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ጊዜ ስለሚያሳጡኝ በኋላ ላይ ነገሮችን በጥድፊያ ለማከናወን እገደዳለሁ።”—ጁልያን

ምን ሊረዳህ ይችላል? የግድ ማድረግ ያለብህን ነገሮች ብቻ ሳይሆን ዘና የምትልባቸውን አንዳንድ እንቅስቃሴዎችም በፕሮግራምህ ውስጥ አካትት። ጁልያን “በኋላ ላይ አንድ የሚያስደስተኝ ነገር እንደማደርግ ካሰብኩ ከዚያ በፊት መሥራት የሚገባኝን ነገር ማከናወን ቀላል ይሆንልኛል” በማለት ተናግሯል። ሌላ አማራጭ፦ ልትደርስበት የምትፈልገው ግብ አውጣ፤ ከዚያም እዚያ ላይ ለመድረስ የሚረዱህ ሌሎች የአጭር ጊዜ ግቦች በማውጣት በፕሮግራምህ መሠረት እየሄድህ መሆንህን ተከታተል።

ምን ማድረግ ትችላለህ? በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን አንድ ወይም ሁለት ግቦች ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ልትደርስበት የምትፈልገውን ግብ ጻፍ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከአሁን ጀምሮ ምን ማድረግ ትችላለህ? *

․․․․․

ተፈታታኝ ሁኔታ #3፦ ንጹሕና የተደራጀህ መሆን

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። ‘ንጹሕና የተደራጁ መሆን ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ‘በዚያ ላይ ሁሉን ነገር በሥርዓት ማስቀመጥ ቀላል አይደለም። ክፍሌን ነገም ላስተካክለው እችላለሁ፤ ደግሞም ባይስተካከልስ! እኔ እንደሆን መዝረክረኩ ያን ያህል አይደብረኝም!’ ትል ይሆናል። በመሆኑም ክፍልህን ማስተካከል ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና ይህ ትክክለኛ አመለካከት ነው?

ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ሁሉንም ነገር በሥርዓት ማስቀመጥህና የተደራጀህ መሆንህ የምትፈልገውን ነገር በቀላሉ ለማግኘት ስለሚያስችልህ ጊዜ ይቆጥብልሃል። በተጨማሪም የተረጋጋህ እንድትሆን ስለሚረዳህ በጣም ይጠቅምሃል።—1 ቆሮንቶስ 14:40

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “ልብሶቼ ከተዝረከረኩ የምፈልጋቸውን ነገሮች ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንብኛል።”—ማንዲ

“በአንድ ወቅት የኪስ ቦርሳዬን የት እንዳደረግሁት አጥቼው ነበር። ሳምንቱን በሙሉ ብፈልገውም ላገኘው ስላልቻልኩ በጣም ተጨነቅኩ። በመጨረሻ ግን ክፍሌን ሳስተካክል አገኘሁት።”—ፍራንክ

ምን ሊረዳህ ይችላል? በተቻለህ መጠን ዕቃዎችህን ወዲያውኑ በየቦታቸው ለመመለስ ጥረት አድርግ። ክፍልህ ተዝረክርኮ ለማጽዳት አስቸጋሪ እስኪሆን ከመጠበቅ ይልቅ ከሥር ከሥሩ አስተካክለው።

ማድረግ የምትችለው ነገር። ምንጊዜም ንጹሕና የተደራጀህ ለመሆን ጥረት አድርግ። ሁሉንም ነገር በሥርዓት ለማስቀመጥ ስትጥር ውጥረትህ ይቀንስልሃል።

ጊዜ ሁሉም ሰው በእኩል መጠን የተሰጠው ንብረት ነው ማለት ይችላል። ይህን ንብረት ካባከንከው ችግር ውስጥ ትገባለህ። በአግባቡ ከተጠቀምክበት ግን ጥሩ ውጤት ታገኛለህ። ምርጫው የአንተ ነው።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ የምትኖርበት አገር ተወላጆች ናቸው? ካልሆኑ በትምህርት ቤት ከሌሎች የተለየህ እንደሆንክ፣ ቤት ውስጥ ደግሞ ከወላጆችህ ጋር መግጠም እንዳልቻልክ ይሰማሃል? ታዲያ ካለህበት ሁኔታ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.32 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 39⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

ጠቃሚ ምክር

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች በሙሉ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ አትሞክር። ከዚህ ይልቅ በአንድ ወር ውስጥ አንዱን ሐሳብ ብቻ በተግባር ለማዋል ጥረት አድርግ። ይሄኛው ከተሳካልህ በኋላ በቀጣዩ ወር በሌላው ነጥብ ላይ ሥራ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በአንድ ቀን ብዙ ነገሮችን ለማከናወን ማቀድ ውጥረት ይፈጥራል። ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለብህ መወሰንህ ግን ጊዜ ካልበቃህ የምትተዋቸውን ሥራዎች ለመለየት ይረዳሃል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ․․․․․ የማጠፋውን ጊዜ እቀንሳለሁ።

በዚህ መንገድ የማገኘውን ጊዜ እንዲህ ለማድረግ እጠቀምበታለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በፕሮግራም መመራትን መልመድህ ወደፊት ራስህን ችለህ መኖር ስትጀምር የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

● ጊዜን አብቃቅቶ በመጠቀም ረገድ ከወላጆችህ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

● በፕሮግራም የምትመራ ከሆነ በጊዜ አጠቃቀምህ ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 154 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በአሥር ሰዓት እንዲመጣልህ የምትፈልግ ከሆነ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ቅጠረው’ በማለት አንድ ሰው ስለ እኔ በቀልድ መልክ ሲናገር ሰማሁ። ጊዜዬን በምጠቀምበት መንገድ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብኝ የተገነዘብኩት በዚህ ወቅት ነበር።”—ሪኪ

[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጊዜዬን ምን ወሰደው?

ከ8 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ወጣቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን በማከናወን ያሳለፉት ሰዓት በአማካይ፦

17

ከወላጆቻቸው ጋር

30

ትምህርት ቤት

44

ቴሌቪዥን በማየት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት፣ የጽሑፍ መልእክት በመላላክና ሙዚቃ በማዳመጥ

በየሳምንቱ ከታች ባሉት ነገሮች ላይ የምታጠፋውን ጊዜ ጻፍ

ቴሌቪዥን በማየት ․․․․․

የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ․․․․․

ኢንተርኔት በመጠቀም ․․․․․

ሙዚቃ በማዳመጥ ․․․․․

ድምር ․․․․․

ከዚህ ላይ ቀንሼ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ላውለው የምችለው ሰዓት ․․․․․

[በገጽ 153 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊዜ በፍጥነት እንደሚጋልብ ፈረስ ነው፤ እንዴት እንደምትቆጣጠረው ማወቅ አለብህ