በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 17

በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

“በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ ለመናገር የሚያስችሉኝ በጣም ጥሩ አጋጣሚዎች አግኝቼ ነበር። የሚያሳዝነው ግን አልተጠቀምኩባቸውም።”—ካሌብ

“መምህራችን በዝግመተ ለውጥ እናምን እንደሆነ ክፍል ውስጥ ጠየቀችን። ይህ ስለ እምነቴ ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ባውቅም በጣም ስለፈራሁ የምናገረው ጠፋኝ። በኋላ ላይ ግን በነገሩ በጣም አዘንኩ።”—ጃዝሚን

አንተም ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ እንደ ካሌብና እንደ ጃዝሚን ተሰምቶህ ያውቅ ይሆናል። እንደ እነዚህ ወጣቶች ሁሉ አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት የምትወድ ከመሆኑም ሌላ የተማርካቸውን ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ትፈልግ ይሆናል። ያም ሆኖ እምነትህን ለሌሎች ስለ ማካፈል ስታስብ በጣም ትፈራ ይሆናል። ይሁን እንጂ በድፍረት የመናገር ችሎታ ማዳበር ትችላለህ። እንዴት? ከዚህ በታች የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

1. የሚያስፈራህ ምን እንደሆነ ለይ። እምነትህን ለሌሎች ስለ መናገር ስታስብ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ሊያጋጥምህ የሚችለው የሚያስፈራ ሁኔታ ይሆናል! ይሁንና የሚያስፈራህ ምን እንደሆነ መናገሩ ወይም መጻፉ ፍርሃትህ እንዲቀንስ ሊረዳህ ይችላል።

ቀጥሎ ያለውን ዓረፍተ ነገር አሟላ፦

● በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ ብናገር ሊፈጠር ይችላል ብዬ የምፈራው ነገር ․․․․․

አንተን የሚያስፈሩህ ነገሮች ሌሎች ክርስቲያን ወጣቶችንም ሊያስፈሯቸው እንደሚችሉ ማወቅህ ሊያበረታታህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የ14 ዓመቱ ክሪስቶፈር “ልጆች እንዳያፌዙብኝና እንዳይጠቋቆሙብኝ እፈራለሁ” በማለት ተናግሯል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ካሌብም “መመለስ የማልችለው ጥያቄ ቢጠይቁኝስ ብዬ እፈራለሁ” ብሏል።

2. የሚያስፈራ ሁኔታ ሊያጋጥምህ እንደሚችል ጠብቅ። ፍርሃትህ ጨርሶ መሠረት የሌለው ነው ሊባል ይችላል? እንደዚያ ማለት አይቻልም። የ20 ዓመቷ አሽሊ ምን አጋጥሟት እንደነበር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ልጆች ስለ እምነቴ ማወቅ የሚፈልጉ መስለው ቀርበውኝ ነበር። በኋላ ግን የተናገርኩትን ነገር በማጣመም በሌሎች ልጆች ፊት አሾፉብኝ።” የ17 ዓመት ወጣት የሆነችው ኒኮልም ያጋጠማትን ሁኔታ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ልጅ፣ የራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅስ አውጥቶ እኔ ከያዝኩት መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲያወዳድር የቃላት ልዩነት እንዳለው ተመለከተ። በዚህ ጊዜ፣ የእኔ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተለወጠ ተናገረ። እኔም ክው ብዬ ቀረሁ! ምን ማለት እንዳለብኝ አላወቅኩም ነበር።” *

እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች በጣም እንደሚያስፈሩ ሊሰማህ ይችላል! ይሁንና በፍርሃት ተሸንፈህ፣ ከመናገር ወደኋላ ከማለት ይልቅ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርብሃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) የ13 ዓመቱ ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ስደት እንደሚደርስባቸው ተናግሯል፤ ስለዚህ ሁሉም ሰው እምነታችንን ይወድልናል ብለን መጠበቅ አንችልም።”—ዮሐንስ 15:20

3. ጥቅሞቹን አስብ። መጥፎ ገጠመኝ እንደሆነ የምታስበው ነገር ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? የ21 ዓመት ወጣት የሆነችው አምበር ይህ ሊሆን እንደሚችል ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ለሌላቸው ሰዎች ስለ እምነታችሁ ማስረዳት ከባድ ነው። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችሁ ስለምታምኑበት ነገር የተሻለ እውቀት እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል።”—ሮም 12:2

በተራ ቁጥር 1 ሥር ባለው ክፍት ቦታ ላይ ያሰፈርከውን ሐሳብ እስቲ መለስ ብለህ ተመልከት። ይህ ሁኔታ ሊያስገኝ የሚችላቸውን ቢያንስ ሁለት ጥቅሞች ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ክፍት ቦታው ላይ ጻፋቸው።

1 ․․․․․

2 ․․․․․

ፍንጭ፦ ስለ እምነትህ መናገርህ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ እንዲቀንስ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? ስለ እምነትህ መናገርህ በራስ የመተማመን ስሜትህ እንዲጎለብት የሚያደርገው እንዴት ነው? ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው? እሱስ ስለ አንተ ምን እንዲሰማው ያደርጋል?—ምሳሌ 23:15

4. አስቀድመህ ተዘጋጅ። ምሳሌ 15:28 “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” ይላል። ስለምታምንባቸው ነገሮች ምን ብለህ እንደምትናገር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሊያነሷቸው የሚችሉ ጥያቄዎችንም ለማሰብ ሞክር። በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም በራስህ አባባል ልትሰጠው የምትችለውን መልስ ተዘጋጅ።—በገጽ 127 ላይ የሚገኘውን “ መልስህን አስቀድመህ አዘጋጅ” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

5. ውይይት ጀምር። ስለ እምነትህ ለመናገር ከተዘጋጀህ በኋላ ውይይቱን የምትጀምረው እንዴት ነው? የተለያዩ አማራጮች አሉህ። ስለ እምነትህ መናገር ከመዋኘት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ አንዳንዶች ወደ ውኃው የሚገቡት ቀስ በቀስ ነው፤ ሌሎች ደግሞ ዘሎ መግባትን ይመርጣሉ። ወደ ውኃው ቀስ በቀስ እንደሚገቡ ሰዎች ሁሉ አንተም ከሃይማኖት ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ጉዳዮች መጀመሪያ ላይ ካነሳህ በኋላ የግለሰቡን ምላሽ እያየህ ውይይቱ በመንፈሳዊ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ትችላለህ። በሌላ በኩል ግን ገና ለገና ሊያጋጥሙህ የሚችሉ ነገሮችን እያሰብክ በጣም የምትጨነቅ ከሆነ የተሻለው አማራጭ ውኃ ውስጥ ዘለው እንደሚገቡ ሰዎች በቀጥታ ስለ እምነትህ መናገር ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 12:11, 12) የ17 ዓመቱ አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “ምንጊዜም ቢሆን ስለ እምነቴ ለሌሎች መናገር እንዲህ ለማድረግ የማሰቡን ያህል አይከብደኝም። አንድ ጊዜ ውይይት ከተጀመረ በኋላ ስለ እምነቴ መናገር ካሰብኩት የበለጠ ቀላል እንደሆነ ተመልክቻለሁ።” *

6. አስተዋይ ሁን። ሰለሞን “አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 13:16 የ1980 ትርጉም) ጥልቀት የሌለው ውኃ ውስጥ ዘለህ እንደማትገባ ሁሉ ለውጥ የማያመጣ ክርክር ውስጥም ላለመግባት ተጠንቀቅ። ለመናገርም ሆነ ለዝምታ ጊዜ እንዳለው አስታውስ። (መክብብ 3:1, 7) ኢየሱስ እንኳ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት የተቆጠበበት ጊዜ ነበር።—ማቴዎስ 26:62, 63

መልስ መስጠት እንዳለብህ ከተሰማህ ደግሞ አጠር ያለና ማስተዋል የሚንጸባረቅበት መልስ ስጥ። ለምሳሌ ያህል፣ ከክፍልህ ተማሪዎች አንዱ ‘ለምን ሲጋራ አታጨስም?’ አለህ እንበል፤ ጥያቄውን ያነሳው ሊያፌዝብህ እንደሆነ ከገባህ ‘ሰውነቴን መበከል አልፈልግም!’ ብለህ መመለስህ በቂ ሊሆን ይችላል። ልጁ የሚሰጥህን መልስ ከሰማህ በኋላ ስለምታምንበት ነገር ይበልጥ ማብራራት ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ትችላለህ።

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተመለከትናቸው ስድስት ነጥቦች ስለ እምነትህ “መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ” እንድትሆን ያስችሉሃል። (1 ጴጥሮስ 3:15) እርግጥ ዝግጅት ስላደረግህ ፈጽሞ አትፈራም ማለት አይደለም። የ18 ዓመቷ አላና እንዲህ ብላለች፦ “ፍርሃት ቢሰማህም እንደምንም ራስህን አደፋፍረህ ስለ እምነትህ ስትናገር አንድ ቁም ነገር እንደሠራህ ይሰማሃል፤ ምክንያቱም ፍርሃትህን ማሸነፍ እንዲሁም ሊሳካም ላይሳካም እንደሚችል እያወቅህም እንኳ በድፍረት መናገር ችለሃል። ከተሳካልህ ደግሞ የበለጠ ደስ ይልሃል! በድፍረት መናገር መቻልህ ጥሩ ስሜት ይፈጥርልሃል።”

በሚቀጥለው ምዕራፍ

የትምህርት ቤት ሕይወትህ ውጥረት ፈጥሮብሃል? ከሆነ ውጥረቱን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንድን ሐሳብ ለመግለጽ የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ትርጉሞች መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሐሳቡ ከተገለጸበት መንገድ ሳይርቁ በተቻለ መጠን ቃል በቃል ለመተርጎም ጥረት ያደርጋሉ።

^ አን.18 ውይይት ለመጀመር . . .” የሚለውን በገጽ 124 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች [ሁኑ]፤ . . . ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።”—1 ጴጥሮስ 3:15

ጠቃሚ ምክር

አብረውህ የሚማሩት ልጆች አንተ የምታምንበትን ነገር እንዲቀበሉ ጫና ከማድረግ ተቆጠብ፤ ከዚህ ይልቅ አንተ ራስህ ስለምታምንበት ነገር በድፍረት መናገርና ለእምነትህ መሠረት የሆነህን ነገር ማስረዳቱ የተሻለ ነው።

ይህን ታውቅ ነበር?

አብረውህ የሚማሩ አንዳንድ ልጆች ስለ እምነትህ ለመጠየቅ ቢፈሩም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በመከተልህ ያደንቁህ ይሆናል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አብረውኝ ከሚማሩ ልጆች መካከል ስለ እምነቴ ልነግረው የምችለው [ቢያንስ የአንድ ልጅ ስም ጻፍ] ․․․․․

ልጁ ሊወደው ይችላል ብዬ የማስበው ርዕስ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አብረውህ የሚማሩት ልጆች በእምነትህ የሚያሾፉት ለምን ይመስልሃል?

● ስለምታምንባቸው ነገሮች በልበ ሙሉነት መናገር ያለብህ ለምንድን ነው?

[በገጽ 126 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ልጅ እያለሁ ከሌሎች ልጆች የተለየሁ ሆኜ መታየት አልፈልግም ነበር። እያደግሁ ስሄድ ግን እምነቴ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረኝ እንደረዳኝ ተገነዘብኩ። ይህም ይበልጥ በራሴ እንድተማመንና በማምንበት ነገር እንድኮራ አድርጎኛል።”—ጄሰን

[በገጽ 124 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ውይይት ለመጀመር . . .

“ትምህርት ቤት ሲዘጋ ምን ለማድረግ አስበሃል?” [መልሱን ከሰማህ በኋላ አንተ ስላወጣሃቸው መንፈሳዊ እቅዶች ለምሳሌ አገልግሎትህን በስፋት ለማከናወን ማሰብህን ልትነግረው ትችላለህ።]

● በዜና ስለሰማኸው አንድ ጉዳይ ከጠቀስክ በኋላ እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ “አንተስ ይህን ዜና ሰምተህ ነበር? ታዲያ ምን ተሰማህ?”

“የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ [ሌላም ችግር ሊሆን ይችላል] መፍትሔ የሚኖረው ይመስልሃል? [እንዲመልስ ዕድል ስጠው።] እንዲህ ያልከው ለምንድን ነው?”

“ሃይማኖትህ ምንድን ነው?”

“ወደፊት ምን ለመሆን ታስባለህ?” [መልሱን ከሰማህ በኋላ አንተ ስላወጣሃቸው መንፈሳዊ ግቦች ንገረው።]

[በገጽ 127 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

 (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የመልመጃ ሣጥን

መልስህን አስቀድመህ አዘጋጅ

ፎቶ ኮፒ አድርገው!

እንዲህ አድርግ፦ ይህን ሠንጠረዥ ከወላጆችህና ክርስቲያን ከሆኑ ሌሎች ወጣቶች ጋር ተወያይበት። ከዚያም ሠንጠረዡን ሙላው። ቀጥሎም አብረውህ የሚማሩ ልጆች ሊያነሷቸው የሚችሉ ሌሎች ጥያቄዎችን አስብና በራስህ አባባል ልትሰጣቸው የምትችለውን መልስ ተዘጋጅ።

ገለልተኝነት

ጥያቄ

ብሔራዊ መዝሙር የማትዘምረው ለምንድን ነው? አገርህን አትወድም?

መልስ

ለምኖርበት አገር አክብሮት አለኝ፤ ብሔራዊ መዝሙር የማልዘምረው አገሪቱን ስለማልወድድ ሳይሆን አምልኮዬን ስለሚነካብኝ ነው።

ሌላ ጥያቄ

ታዲያ ለአገርህ አትዋጋም ማለት ነው?

መልስ

አልዋጋም። በሌሎች አገሮች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን አገር ለመውጋት አይነሱም።

ደም

ጥያቄ

ደም የማትወስደው ለምንድን ነው?

መልስ

መጽሐፍ ቅዱስ ከደም እንድንርቅ ስለሚያዝዝ ነው። ይሁንና ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን እቀበላለሁ። እነዚህ ሕክምናዎች ለኤድስ ወይም ለሄፕታይተስ አያጋልጡም።

ሌላ ጥያቄ

እንዴ፣ ደም ካልወሰድክ ትሞታለህ ብትባልስ? ሕይወትህን ለማትረፍ እስከሆነ ድረስ አምላክ ይቅር አይልህም?

መልስ

․․․․․

የግል ምርጫ

ጥያቄ

የእናንተ አባል የሆነው እንትና እንዲህ ሲያደርግ አይቼዋለሁ። ታዲያ አንተ ምን ታካብዳለህ?

መልስ

ሁላችንም የአምላክን መመሪያዎች ተምረናል፤ ይሁን እንጂ የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው።

ሌላ ጥያቄ

ታዲያ ሁሉም እንደፈለገው ነው የሚሆነው ማለት ነው?

መልስ

․․․․․

ፍጥረት

ጥያቄ

በዝግመተ ለውጥ የማታምነው ለምንድን ነው?

መልስ

አሳማኝ ምክንያት ስላላገኘሁ ነዋ! ተምረዋል የሚባሉት የሳይንስ ሊቃውንት እንኳ በዚህ ጉዳይ እርስ በርስ አይስማሙም!

ሌላ ጥያቄ

․․․․․

መልስ

․․․․․

[በገጽ 125 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ መናገር ከመዋኘት ጋር ይመሳሰላል፤ ቀስ በቀስ አሊያም ዘለህ መግባት ትችላለህ!