በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወላጆቼ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

ከወላጆቼ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 1

ከወላጆቼ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

“ስሜቴን ወላጆቼ በሚገባቸው መንገድ ለመናገር ጥረት ባደርግም እንዳሰብኩት ሐሳቤን በደንብ መግለጽ አልቻልኩም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ገና መናገር ስጀምር አቋረጡኝ። ያነጋገርኳቸው እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ቢሆንም አልተሳካልኝም!”—ሮሳ

ትንሽ ልጅ ሳለህ ብዙውን ጊዜ ምክር ለመጠየቅ መጀመሪያ የምትሮጠው ወደ ወላጆችህ ነበር። * ትልቅ ትንሽ ሳትል ማንኛውንም ነገር ትነግራቸው ነበር። የምታስበውንና የሚሰማህን ነገር ለእነሱ ከመናገር ወደኋላ አትልም፤ ደግሞም በሚሰጡህ ምክር ትተማመን ነበር።

አሁን ግን ወላጆችህ ስሜትህን ፈጽሞ ሊረዱልህ እንደማይችሉ ይሰማህ ይሆናል። ኤዲ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን ራት እየበላን ሳለ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ከዚያም የተሰማኝን ሁሉ ተናገርኩ። ወላጆቼ ቢያዳምጡኝም ስሜቴን የተረዱልኝ አይመስለኝም።” ታዲያ ኤዲ ምን አደረገች? “ወደ መኝታ ክፍሌ ሄጄ ማልቀሴን ቀጠልኩ!” ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ለወላጆችህ ስሜትህን አውጥተህ መናገር የማትፈልግበት ጊዜ ይኖራል። ክሪስቶፈር የሚባል ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ከወላጆቼ ጋር ስለተለያዩ ጉዳዮች አወራለሁ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የማስበውን ነገር ባያውቁ እመርጣለሁ።”

አንዳንድ ነገሮችን ለሌሎች አለመናገርህ ስህተት ነው? ያልተናገርከው ለማታለል ብለህ እስካልሆነ ድረስ ስህተት ላይሆን ይችላል። (ምሳሌ 3:32) ወላጆችህ እንደማይረዱህ ይሰማህ ወይም ደግሞ ሐሳብህን አውጥተህ መናገር አትፈልግ ይሆናል። ያም ቢሆን ልትዘነጋው የማይገባ ነገር አለ፤ አንተ ከወላጆችህ ጋር መነጋገር አለብህ፤ እነሱ ደግሞ ያለህበትን ሁኔታ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

ከማነጋገር ወደኋላ አትበል!

ከወላጆችህ ጋር መነጋገር መኪና ከመንዳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መንገድ ላይ መሰናክል ቢያጋጥምህ ለምሳሌ መንገድ ቢዘጋብህ ጉዞህን አታቋርጥም፤ ከዚህ ይልቅ ሌላ መንገድ ፈልገህ ጉዞህን ትቀጥላለህ። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

መሰናክል 1 ለወላጆችህ መናገር የምትፈልገው ነገር አለ፤ እነሱ ግን የሚያዳምጡህ አይመስሉም። ሊያ የምትባል ወጣት “ከአባቴ ጋር መነጋገር አስቸጋሪ ነው” ብላለች። “አንዳንድ ጊዜ ሳናግረው ቆይቼ መሃል ላይ ‘ይቅርታ፣ ልብ ብዬ አልሰማሁሽም፤ ምን አልሽኝ?’ ይለኛል።”

ጥያቄ፦ ሊያ አባቷን ማነጋገር የፈለገችው አንድ ችግር አጋጥሟት ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለች? ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሏት።

አማራጭ ሀ

በአባቷ ላይ መጮኽ። “ለምን አታዳምጠኝም? ቁም ነገር እኮ ነው የምነግርህ!” በማለት አባቷ ላይ ታንባርቅ ይሆናል።

አማራጭ ለ

አባቷን ላለማናገር መወሰን። ስላጋጠማት ችግር ከአባቷ ጋር ለመነጋገር መሞከሯን እርግፍ አድርጋ ልትተው ትችላለች።

አማራጭ ሐ

አመቺ ጊዜ ፈልጋ ጉዳዩን እንደገና ማንሳት። ስላጋጠማት ችግር ከአባቷ ጋር ሌላ ጊዜ መነጋገር አሊያም ለአባቷ ደብዳቤ መጻፍ ትችላለች።

ሊያ የትኛውን አማራጭ ብትከተል የተሻለ ይመስልሃል? ․․․․․

እስቲ እያንዳንዱ አማራጭ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንመልከት።

የሊያ አባት ትኩረት ሰጥቶ አላዳመጣትም፤ በመሆኑም ያሳሰባት ነገር እንዳለ ልብ አላለም። ስለዚህ ሊያ አማራጭ ሀ ላይ እንደተጠቀሰው በአባቷ ላይ ብትጮኽበት እንዲህ ያደረገችው ለምን እንደሆነ ላይገባው ይችላል። ይህ አማራጭ ሊያ የምትናገረውን ነገር ለማዳመጥ እንዲነሳሳ አያደርገውም፤ ከዚህም በላይ ሊያ ለእሱ አክብሮት እንዳላት የሚያሳይ አይሆንም። (ኤፌሶን 6:2) በመሆኑም ይህ አማራጭ የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም።

አማራጭ ለ ከሁሉ የቀለለው መፍትሔ ሊሆን ቢችልም እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተሉ ብልህነት አይደለም። ለምን? ምክንያቱም “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል።” (ምሳሌ 15:22) ሊያ ችግሯን በተሳካ መንገድ ለመወጣት እንድትችል ከአባቷ ጋር መነጋገር ያስፈልጋታል፤ አባቷም እርዳታ ሊያደርግላት የሚችለው በሕይወቷ ውስጥ ስላጋጠማት ነገር ካወቀ ብቻ ነው። ከእሱ ጋር መነጋገሯን ማቆሟ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።

ሊያ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ ብትከተል ግን በመንገዷ ላይ ያጋጠማት መሰናክል ጉዞዋን እንድታቋርጥ አያደርጋትም። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን ሌላ ጊዜ ለማንሳት ትሞክራለች። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ጉዳዩ ለአባቷ ደብዳቤ ብትጽፍ ብዙም ሳይቆይ ስሜቷ ሊረጋጋ ይችላል። ደብዳቤ መጻፏ መናገር የምትፈልገውን ነገር ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ሊረዳት ይችላል። አባቷም ቢሆን ደብዳቤውን ሲያነብ ሊያ ምን ልትነግረው እንደፈለገች መገንዘብ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ያጋጠማትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችለዋል። ስለዚህ ሊያ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ መከተሏ ለእሷም ሆነ ለአባቷ ጥቅም አለው።

ሊያ ምን ሌሎች አማራጮች ሊኖሯት ይችላሉ? አማራጭ ሊሆን ይችላል ብለህ የምታስበው ነገር ካለ ከዚህ በታች አስፍር። ከዚያም ይህን አማራጭ መከተል ምን ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ጻፍ።

․․․․․

መሰናክል 2 ወላጆችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገዋል፤ አንተ ግን መነጋገር አትፈልግም። ሣራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤት ውዬ ድክም ብሎኝ ስገባ ወላጆቼ በጥያቄ ያጣድፉኛል፤ ይህ ደግሞ ያበሳጨኛል። በዚያ ሰዓት ስለ ትምህርት ቤት እንዲነሳብኝ አልፈልግም፤ ወላጆቼ ግን ገና ሲያገኙኝ ‘ውሎሽ እንዴት ነበር? ያጋጠመሽ ችግር አለ እንዴ?’ እያሉ መጠየቅ ይጀምራሉ።” የሣራ ወላጆች እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የሚያቀርቡላት ሊያበሳጯት አስበው እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ሣራ “በጣም ደክሞኝና አእምሮዬ ውጥር ብሎ ባለበት ወቅት ስለ ትምህርት ቤት ማውራት አልፈልግም” በማለት በምሬት ተናግራለች።

ጥያቄ፦ ሣራ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማት ምን ማድረግ ትችላለች? ቀደም ባለው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሏት።

አማራጭ ሀ

ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆን። “አሁን ማውራት አልፈልግም። በቃ ተዉኝ!” ትል ይሆናል።

አማራጭ ለ

ባትፈልግም ውይይቱን መቀጠል። ውጥረት ስለተሰማት ማውራት ባያሰኛትም ወላጆቿ የሚጠይቋትን ጥያቄዎች በተሰላቸ መንፈስ ትመልስ ይሆናል።

አማራጭ ሐ

ስለ ትምህርት ቤት ከማውራት ይልቅ ለጊዜው የጨዋታውን ርዕስ መቀየር። ስለ ትምህርት ቤት አእምሮዋ ሲረጋጋ ሌላ ጊዜ እንዲወያዩ ሐሳብ ማቅረብ ትችላለች። ከዚያም ከልቧ እንደምታስብላቸው በሚያሳይ መንገድ “እናንተስ ውሏችሁ እንዴት ነበር? ጥሩ ቀን አሳለፋችሁ?” በማለት ልትጠይቃቸው ትችላለች።

ሣራ የትኛውን አማራጭ ብትከተል የተሻለ ይመስልሃል? ․․․․․

አሁንም እያንዳንዱ አማራጭ ምን ውጤት እንደሚያስከትል እስቲ እንመርምር።

ሣራ ውጥረት ስለተሰማት ማውራት አልፈለገችም። ሆኖም አማራጭ ሀ ላይ ያለውን መፍትሔ ብትመርጥ ውጥረቷ ቀለል አይልላትም፤ በዚያ ላይ ደግሞ በወላጆቿ ላይ በመጮዃ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማታል።—ምሳሌ 29:11

የሣራ ወላጆችም ቢሆኑ በቁጣ መመለሷም ሆነ ከዚያ በኋላ ለማውራት ፈቃደኛ አለመሆኗ ቅር ሊያሰኛቸው ይችላል። ሣራ የደበቀችው ነገር እንዳለ ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም ስሜቷን አውጥታ እንድትነግራቸው ከበፊቱ ይበልጥ ይወተውቷት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሣራን የባሰ እንደሚያበሳጫት የታወቀ ነው። በመሆኑም ይህን አማራጭ መከተል መፍትሔ አይሆንም።

አማራጭ ለ ከአማራጭ ሀ የተሻለ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ቢያንስ ቢያንስ ሣራና ወላጆቿ መነጋገር ችለዋል። ይሁን እንጂ ሣራ የምትናገረው ከልቧ ስላልሆነ እሷም ሆነች ወላጆቿ ውይይታቸው እንደሚፈልጉት አይሆንላቸውም፤ በሌላ አባባል፣ ዘና ባለ መንፈስ የውስጣቸውን አውጥተው አይነጋገሩም።

ሣራ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ ብትከተል ግን ቢያንስ በዚያ ወቅት ስለ ትምህርት ቤት ስለማያወሩ ውጥረቷ ቀለል ሊልላት ይችላል። ወላጆቿም ቢሆኑ ጨዋታው እንዲቀጥል ጥረት በማድረጓ ደስ ይላቸዋል። ይህ አማራጭ ከሁሉ የተሻለ ውጤት ያስገኛል፤ ምክንያቱም ሁለቱም ወገኖች በፊልጵስዩስ 2:4 ላይ ያለውን “ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ” የሚለውን መመሪያ በሥራ ላይ አውለዋል።

ወላጆችህ የምትናገረውን ነገር ባላሰብከው መንገድ እንዳይረዱት ምን ማድረግ ትችላለህ?

ወላጆችህ የምትናገረውን ነገር አንዳንድ ጊዜ አንተ ባላሰብከው መንገድ ሊረዱት እንደሚችሉ አስታውስ። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆችህ የከፋህ ለምን እንደሆነ ይጠይቁህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ “ስለዚህ ጉዳይ ማውራት አልፈልግም” ብለህ ብትመልስላቸው ወላጆችህ እንደሚከተለው እንዳልካቸው ሊሰማቸው ይችላል፦ “ሚስጥሬን ለእናንተ መናገር ይከብደኛል። ስለዚህ ጉዳይ ከጓደኞቼ እንጂ ከእናንተ ጋር ማውራት አልፈልግም።” ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፦ አንድ ከባድ ችግር አጋጥሞሃል እንበል፤ ወላጆችህ እርዳታ ያስፈልግህ እንደሆነ ጠየቁህ። ይህን በአእምሮህ በመያዝ ከታች ባሉት ክፍት ቦታዎች ላይ ሐሳብህን ለማስፈር ሞክር።

የአንተ ምላሽ፦ “አይ አታስቡ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ።”

ወላጆችህ ሊረዱ የሚችሉበት መንገድ፦ ․․․․․

የተሻለው ምላሽ፦ ․․․․․

ዋናው ነጥብ? ከመናገርህ በፊት ስለምትጠቀምባቸው ቃላት ቆም ብለህ አስብ። የምትናገርበት መንገድ አክብሮት እንዳለህ የሚያሳይ ይሁን። (ቆላስይስ 4:6) ወላጆችህ አንተን ለመርዳት የሚፈልጉ አጋሮችህ እንጂ ጠላቶችህ እንዳልሆኑ አስታውስ። ደግሞም ልትዘነጋው የማይገባ ሐቅ አለ፦ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ ለመወጣት ከፈለግህ አንተን ለመርዳት የሚሞክሩ አጋሮችህን እርዳታ ሁሉ መቀበል አለብህ።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ከወላጆችህ ጋር መነጋገር ባይከብድህም መነጋገር ስትጀምሩ ሁልጊዜ ጭቅጭቅ የሚፈጠር ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“ከአንደበቴ የሚወጡት ቃላት የልቤን ቅንነት የሚገልጡ ናቸው።”—ኢዮብ 33:3 የ1980 ትርጉም

ጠቃሚ ምክር

ስላጋጠመህ ችግር ከወላጆችህ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር የሚከብድህ ከሆነ በእግራችሁ ስትንሸራሸሩ፣ በመኪና ስትጓዙ ወይም ገበያ ስትወጡ ጉዳዩን አንስተህ ልታወያያቸው ትችላለህ።

ይህን ታውቅ ነበር?

ከበድ ያሉ ጉዳዮችን አንስቶ ከወላጆችህ ጋር መወያየት የሚጨንቅህ አንተ ብቻ አይደለህም፤ ወላጆችህም ቢሆኑ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ማውራት ሊከብዳቸው እንዲሁም ስለ ጉዳዩ በቂ እውቀት እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ከወላጆቼ ጋር ስለ አንድ ጉዳይ ማውራት ባልፈልግ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ስለ አንድ ጉዳይ ማውራት ባያሰኘኝም ወላጆቼ እንዳወራ ቢጎተጉቱኝ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ጥሩ ውይይት ለማድረግ አመቺ ጊዜ መምረጥ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?—ምሳሌ 25:11

● ከወላጆችህ ጋር ለመነጋገር ጥረት ማድረግህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?—ኢዮብ 12:12

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከወላጆችህ ጋር መነጋገር ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም ስሜትህን አውጥተህ ስታወያያቸው ከባድ ሸክም ከላይህ የወረደልህ ያህል ቅልል ይልሃል።”—ዴቨኒ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንገድ ቢዘጋብህ ሌላ አማራጭ ትፈልጋለህ እንጂ ጉዞህን አታቆምም፤ ከወላጆችህ ጋር ለመነጋገር ስትፈልግ እንቅፋት ቢያጋጥምህም ሌላ አማራጭ መጠቀም ትችላለህ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ወጣቶች ስንገልጽ በአብዛኛው የምንጠቀመው በተባዕታይ ፆታ ቢሆንም ትምህርቱ ለሁለቱም ፆታዎች እንደሚሠራ ግልጽ ነው።