በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁልጊዜ የምንጨቃጨቀው ለምንድን ነው?

ሁልጊዜ የምንጨቃጨቀው ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 2

ሁልጊዜ የምንጨቃጨቀው ለምንድን ነው?

በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ውስጥ ሬቸል ጭቅጭቅ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደረገችባቸውን ሦስት መንገዶች መጥቀስ ትችላለህ? መልስህን ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ፤ ከዚያም በገጽ 20 ላይ ባለው “ መልስ” በሚለው ሣጥን ውስጥ ከተሰጠው ሐሳብ ጋር መልስህን አወዳድር።

․․․․․

ቀኑ ረቡዕ ሲሆን አመሻሹ ላይ ነው። የ17 ዓመቷ ሬቸል የቤት ውስጥ ሥራዋን ስለጨራረሰች ትንሽ ዘና ለማለት አስባለች። ቴሌቪዥኑን ከፈተችና በምትወደው ሶፋ ላይ ተመቻችታ ቁጭ አለች።

ሬቸል ገና ከመቀመጧ እናቷ ብቅ አለች፤ በሬቸል እንዳልተደሰተች ፊቷ ላይ ይነበባል። “ሬቸል! እህትሽን የቤት ሥራ ማሠራት ትተሽ ቁጭ ብለሽ ቴሌቪዥን ታያለሽ? አንቺ በቃ የምትባዪውን ፈጽሞ አትሰሚም ማለት ነው?” አለቻት።

ሬቸል ለእናቷ በሚሰማ ድምፅ “ጀመራት ደግሞ” በማለት አጉተመተመች።

እናቷም “ምናልሽ?” በማለት ጠየቀቻት።

ሬቸል በረጅሙ ተንፍሳ እናቷን በጎሪጥ እያየች “ምንም” ብላ መለሰችላት።

በዚህ ጊዜ እናቷ በጣም ተናድዳ “በዚህ መንገድ ነው የምትመልሺልኝ?” በማለት አፈጠጠችባት።

ሬቸልም “አንቺስ ብትሆኚ እንዴት ነው ያናገርሽኝ?” በማለት መለሰች።

ሬቸል ዘና ማለቷ ቀረና ሌላ ጭቅጭቅ ተጀመረ።

አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥምሃል? ከወላጆችህ ጋር ነጋ ጠባ ትጨቃጨቃላችሁ? ከሆነ እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የሚያጨቃጭቋችሁ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ከታች ከተዘረዘሩት መካከል እናንተን በሚያጨቃጭቋችሁ ጉዳዮች ላይ ✔ አድርግ፤ አሊያም “ሌላ” በሚለው ቦታ ላይ የራስህን ሐሳብ ጻፍ።

□ የአመለካከት ልዩነት

□ የቤት ውስጥ ሥራዎች

□ አለባበስ

□ ቤት መግቢያ ሰዓት

□ መዝናኛ

□ ጓደኞች

□ ተቃራኒ ፆታ

□ ሌላ ․․․․․

የሚያጨቃጭቃችሁ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፣ በኋላ ላይ አንተም ሆንክ ወላጆችህ በተፈጠረው ሁኔታ ደስ እንደማይላችሁ የታወቀ ነው። እርግጥ ነው፣ ለወላጆችህ ምንም መልስ ባለመስጠት በሚናገሩት ሁሉ እንደተስማማህ ማስመሰል ትችላለህ። ይሁንና እንዲህ ማድረግህ አምላክን ያስደስተዋል? አያስደስተውም። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “አባትህንና እናትህን አክብር” በማለት ያዝዛል። (ኤፌሶን 6:2, 3) በሌላ በኩል ግን ‘ልባም’ እንድትሆን ማለትም የማመዛዘን ችሎታህን እንድታዳብር እንዲሁም ‘የማሰብ ችሎታህን’ እንድትጠቀምበት ያበረታታል። (ምሳሌ 1:1-4፤ ሮም 12:1) እንዲህ ስታደርግ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ከወላጆችህ የተለየ አመለካከት ሊኖርህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ በሚያደርጉ ቤተሰቦች ውስጥ ወላጆችና ልጆች የአመለካከት ልዩነት በሚኖራቸው ጊዜም እንኳ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መወያየት ይችላሉ።—ቆላስይስ 3:13

ታዲያ ከወላጆችህ ጋር የምታደርጉት ውይይት ወደ ቃላት ጦርነት ሳይለወጥ ስሜትህን መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው? “ጥፋቱ እኮ የወላጆቼ ነው፤ ስወጣ ስገባ ይጨቀጭቁኛል” ብሎ መናገር ቀላል ነው። ይሁን እንጂ እስቲ አስበው፤ ወላጆችህን ወይም ሌሎች ሰዎችን መለወጥ ትችላለህ? መለወጥ የምትችለው ራስህን ብቻ ነው። ደስ የሚለው ነገር ደግሞ አንተ ውጥረቱን ለማርገብ የበኩልህን የምታደርግ ከሆነ ሐሳብህን በምትገልጽበት ጊዜ ወላጆችህም ጆሮ ሰጥተው በተረጋጋ መንፈስ ሊያዳምጡህ ይችላሉ።

ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር አንተ በበኩልህ ምን ማድረግ እንደምትችል እስቲ እንመልከት። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ከሌሎች ጋር የመነጋገር ችሎታህን ለማሻሻል ሞክር፤ እንዲህ ስታደርግ በሚኖርህ ለውጥ አንተም ሆንክ ወላጆችህ መደነቃችሁ አይቀርም።

መልስ ከመስጠትህ በፊት አስብ። ወላጆችህ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደተናገሩህ ሲሰማህ አፍህ ላይ የመጣውን ነገር ከመናገር ተቆጠብ። ለምሳሌ ያህል፣ እናትህ “ዕቃውን ያላጠብከው ለምንድን ነው? ሰው የሚልህን ፈጽሞ አትሰማም ማለት ነው?” አለችህ እንበል። በዚህ ቅጽበት “እስቲ አትጨቅጭቂኝ!” ብለህ መመለስ ይቃጣህ ይሆናል። ይሁንና እስቲ ቆም ብለህ ጉዳዩን ለማመዛዘን ሞክር። እናትህ እንዲህ እንዲሰማት ያደረገው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት ጣር። “ሁልጊዜ” ወይም “ፈጽሞ” እንደሚሉት ያሉትን አነጋገሮች አብዛኛውን ጊዜ ቃል በቃል መረዳት የለብህም። እነዚህ ቃላት፣ ተናጋሪው በወቅቱ ያለውን ስሜት የሚጠቁሙ ናቸው። ታዲያ እናትህ እንዲህ ያለችው ምን ተሰምቷት ሊሆን ይችላል?

ምናልባት እናትህ የቤቱ ሥራ ሁሉ በእሷ ላይ እንደተከመረ ስለተሰማት ተበሳጭታ ይሆናል። በዚህ ወቅት የምትፈልገው እሷን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆንክ ማወቅ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ “እስቲ አትጨቅጭቂኝ!” ብለህ መልስ መስጠትህ ነገሩን ከማባባስ ውጭ ምንም አይፈይድም። ታዲያ እናትህን ሊያረጋጋት የሚችል ሐሳብ ለምን አትናገርም? ለምሳሌ “ይቅርታ እማዬ። ዕቃውን አሁኑኑ አጥበዋለሁ” ልትል ትችላለህ። ይሁንና አነጋገርህ የሽሙጥ እንዳይመስልብህ ተጠንቀቅ። ስሜቷን እንደተረዳህላት በሚያሳይ መንገድ መናገርህ እናትህ እንድትረጋጋና ያበሳጫት ነገር ምን እንደሆነ እንድትነግርህ ሊያነሳሳት ይችላል። *

አባትህ ወይም እናትህ ምን ቢሉህ እንደምትበሳጭ ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

ወላጆችህ እንዲህ የተናገሩት ምን ተሰምቷቸው እንደሆነ መረዳትህን የሚያሳይ ምን መልስ መስጠት ትችላለህ?

․․․․․

በአክብሮት ተናገር። ሚሼል የተባለችው ወጣት እናቷን የምታነጋግርበት መንገድ ለውጥ እንደሚያመጣ ከተሞክሮ ተምራለች። ሚሼል “ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣ ሁሌም እናቴን የሚያበሳጫት የምናገርበት መንገድ ነው” ብላለች። አንተም ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚፈጠር ካስተዋልክ ሳትጮኽ ረጋ ብለህ ተናገር፤ እንዲሁም ዓይንህን በማጉረጥረጥም ይሁን ሌላ አካላዊ መግለጫ በመጠቀም ብስጭትህን ከመግለጽ ተቆጠብ። (ምሳሌ 30:17) በቁጣ ልትገነፍል እንደሆነ ከተሰማህ በልብህ ወደ አምላክ አጭር ጸሎት አቅርብ። (ነህምያ 2:4) እርግጥ ነው፣ ወደ አምላክ የምትጸልየው ‘ከወላጆችህ ጭቅጭቅ እንዲገላግልህ’ ሳይሆን በመካከላችሁ ያለውን ውጥረት የሚያባብስ ነገር እንዳታደርግ ራስህን ለመግዛት እንዲረዳህ መሆን ይኖርበታል።—ያዕቆብ 1:26

ልታስወግዳቸው የሚገቡ አንዳንድ አነጋገሮችንና አካላዊ መግለጫዎችን ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

አነጋገር (የምትናገራቸው ቃላት)፦

․․․․․

አካላዊ መግለጫዎች (በፊትህና በሌሎች የሰውነትህ ክፍሎች የምታሳያቸው ነገሮች)፦

․․․․․

አዳምጥ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከብዙ ንግግር ውስጥ ስሕተት አይጠፋም” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 10:19 የ1980 ትርጉም) እናትህ ወይም አባትህ እንዲናገሩ ዕድል ስጣቸው፤ እንዲሁም ወላጆችህ ሲናገሩ በትኩረት አዳምጥ። የሚናገሩትን ነገር ለማስተባበል ስትል ጣልቃ ገብተህ አታቋርጣቸው። ሲናገሩ ዝም ብለህ አዳምጥ። ወላጆችህ ተናግረው ሲጨርሱ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ወይም ሐሳብህን ለመግለጽ አጋጣሚ ይኖርሃል። በሌላ በኩል ግን ‘ያሰብኩትን አሁኑኑ ካልተናገርኩ ሞቼ እገኛለሁ’ የምትል ከሆነ ሁኔታውን ከማባባስ ውጭ የምታተርፈው ነገር የለም። መናገር የምትፈልገው ነገር ቢኖርም እንኳ ‘ለዝምታ ጊዜ እንዳለው’ ማስታወስህ ጥሩ ነው።—መክብብ 3:7

ይቅርታ ለመጠየቅ አታመንታ። ለጭቅጭቁ መፈጠር አንተም ተጠያቂ ልትሆን ስለምትችል “ይቅርታ” ማለትህ ምንጊዜም ቢሆን ተገቢ ነው። (ሮም 14:19) ሌላው ቢቀር ጭቅጭቅ በመፈጠሩ እንዳዘንክ መናገር ትችላለህ። ፊት ለፊት ይቅርታ መጠየቅ ከባድ ከሆነብህ ስሜትህን በጽሑፍ ለመግለጽ ሞክር። ከዚህም ሌላ ለጭቅጭቅ መንስኤ ሊሆን የሚችል ማንኛውንም ባሕርይ በማስወገድ ‘ተጨማሪ ኪሎ ሜትር’ መሄድ ማለትም ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ ትችላለህ። (ማቴዎስ 5:41) ለምሳሌ ያህል፣ ለጭቅጭቅ መንስኤ የሆነው መሥራት ያለብህን የቤት ውስጥ ሥራ ሳትሠራ መቅረትህ ከሆነ ሥራውን በመሥራት ወላጆችህን ለምን አታስደስታቸውም? ሥራውን አትወደው ይሆናል፤ ያም ቢሆን ወላጆችህ ተነግሮህም አለመሥራትህን ሲያዩ ከሚፈጠረው ጭቅጭቅ ይልቅ ሠርቶ መገላገሉ አይሻልም? (ማቴዎስ 21:28-31) በአንተና በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረውን ውጥረት የሰፈነበት ሁኔታ በማርገብ ረገድ የበኩልህን ድርሻ ማበርከትህ ምን ጥቅሞች እንደሚያስገኝልህ አስብ።

ጥሩ ግንኙነት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥም አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል፤ ሆኖም እነዚህ ቤተሰቦች የተፈጠረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ያውቃሉ። በዚህ ምዕራፍ ላይ የቀረቡትን ምክሮች ተግባራዊ ካደረግህ ከበድ ያሉ ጉዳዮችንም ከወላጆችህ ጋር ሳትጨቃጨቁ መወያየት ትችላላችሁ!

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡህ እንደሚገባ ይሰማሃል? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.26 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 21 ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ደጋግ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ።”—ምሳሌ 15:28 የ1980 ትርጉም

ጠቃሚ ምክር

ወላጆችህ ሲያናግሩህ ሙዚቃ ተከፍቶ ከነበረ አጥፋው፤ እንዲሁም የምታነበውን መጽሐፍ ወይም መጽሔት ዘግተህ ዓይን ዓይናቸውን እያየህ አዳምጣቸው።

ይህን ታውቅ ነበር

በአንተና በወላጆችህ መካከል የተፈጠረውን ጭቅጭቅ ለመፍታት መሞከርህ አሊያም ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር መጣርህ ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖርህ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስም “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 11:17

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል ይበልጥ ልሠራበት የምፈልገው ነጥብ ․․․․․

ከዚህ ቀን ጀምሮ ይህን ነጥብ ልሠራበት ወስኛለሁ፤ ቀኑን አስፍር ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በአንተ ዕድሜ ያሉ አንዳንድ ወጣቶች፣ ተጨቃጭቆ መርታት ትልቅ ችሎታ እንደሆነ የሚያስቡት ለምንድን ነው?

● ይሖዋ ተጨቃጫቂ የሆነን ሰው እንደ ተላላ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 20:3

● በአንተና በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረውን ውጥረት የሰፈነበት ሁኔታ ለማርገብ የበኩልህን ድርሻ ማበርከትህ ምን ጥቅሞች ያስገኝልሃል?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንዳንድ ጊዜ እናቴ እቅፍ አድርጋ ይቅርታ ትጠይቀኛለች፤ እንዲህ ስታደርግ ደስ ይለኛል። ከዚያም የተፈጠረውን ነገር እንረሳዋለን። እኔም እንደ እናቴ ለማድረግ እሞክራለሁ። ኩራቴን ዋጥ አድርጌ ከልቤ ይቅርታ መጠየቅ ቀላል ባይሆንም ይህን ማድረጌ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ተረድቻለሁ።”—ሎረን

 [በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መልስ

1. በሽሙጥ መናገሯ (“ጀመራት ደግሞ”) የእናቷን ንዴት ከማባባስ ውጭ የፈየደው ነገር የለም።

2. ሬቸል ፊቷ ላይ ያሳየችው ነገር (እናቷን በጎሪጥ ማየቷ) የበለጠ ችግር ፈጥሯል።

3. እኩል መመላለስ (“አንቺስ ብትሆኚ እንዴት ነው ያናገርሽኝ?”) አብዛኛውን ጊዜ የባሰ ጣጣ ውስጥ ያስገባል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከወላጆችህ ጋር መጨቃጨቅ በመሮጫ ማሽን ላይ ከመሮጥ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ባለ በሌለ ኃይልህ ብትሮጥም የትም አትደርስም