በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱስ ሆነውብኛል?

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱስ ሆነውብኛል?

ምዕራፍ 36

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱስ ሆነውብኛል?

“የጽሑፍ መልእክት መላላክ በጣም በጣም እወዳለሁ! ከምንም በላይ ደስ የሚል ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። መላ ሕይወቴን ተቆጣጥሮታል ማለት ይቻላል።”—አለን

ወላጆችህ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳሉ በስፋት የሚታወቁት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ነበሩ። በዘመኑ የነበሩት ስልኮች የድምፅ መልእክት ከማስተላለፍ ያለፈ አገልግሎት አልነበራቸውም፤ እነዚህ ስልኮች የሚሠሩት ግድግዳ ላይ ከተሰካ መሥመር ጋር ተገናኝተው በመሆኑ አሁን እንዳሉት ስልኮች ተንቀሳቃሽ አልነበሩም። እንዲህ ያለው ስልክ ኋላቀር እንደሆነ ይሰማሃል? አና የተባለች አንዲት ወጣት እንደዚህ ይሰማታል። “ወላጆቼ ያደጉት በቴክኖሎጂ ረገድ በጨለማ ዘመን ውስጥ ነው” ብላለች። “ሞባይል ስልካቸው ላይ ያሉትን አንዳንድ ነገሮች እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው መረዳት እስካሁን ይከብዳቸዋል!”

ዛሬ ግን በኪስህ በምትይዛት አንዲት ትንሽ ስልክ አማካኝነት መደወል፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ፊልም ማየት፣ ጌም መጫወት፣ ለጓደኞችህ ኢ-ሜይል መላክ፣ ፎቶ ማንሳትና ኢንተርኔት መጠቀም ትችላለህ። ከልጅነትህ ጀምሮ ኮምፒውተር፣ ሞባይል፣ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት ማግኘት ትችል ስለነበር በእነዚህ ነገሮች በመጠቀም ረጅም ሰዓት ማሳለፍ ስህተት እንደሆነ አይሰማህ ይሆናል። ወላጆችህ ግን የእነዚህ ነገሮች ሱሰኛ እንደሆንክ ሊሰማቸው ይችላል። እነዚህን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በመጠቀም የምታሳልፈው ጊዜ እንዳሳሰባቸው ቢነግሩህ ትክክል እንዳልሆኑ ተሰምቶህ አስተያየታቸውን ችላ አትበል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “መልስ ከመስጠትህ በፊት አዳምጥ፤ አለበለዚያ ሞኝ . . . መሆንህን ታሳያለህ” ብሏል።—ምሳሌ 18:13 የ1980 ትርጉም

ወላጆችህ ጉዳዩ ይህን ያህል ያሳሰባቸው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አንድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሱስ ሆኖብህ እንደሆነ ራስህን ለመገምገም ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት።

ራስህን ገምግም—ሱስ ሆኖብሃል?

አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው ሱስ የሚለው ቃል “አንድ ሰው፣ ጉዳት የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ማቆም ያቃተውን ወይም ለማቆም የማይፈልገውን ከልክ ያለፈና ሥር የሰደደ ልማድ” ያመለክታል። እስቲ በዚህ ፍቺ ውስጥ ያሉትን ሐረጎች ከፋፍለን እንመልከታቸው። አንዳንድ ወጣቶች የሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፤ አንተስ እንደ እነሱ አድርገህ ታውቃለህ? በክፍት ቦታው ላይ መልስህን ጻፍ።

ከልክ ያለፈ ልማድ። “የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በመጫወት ብዙ ሰዓት አጠፋ ነበር። ጌም መጫወት የእንቅልፍ ሰዓቴን የሚሻማብኝ ከመሆኑም ሌላ ወሬዬ ሁሉ እሱ ነበር። በምጫወታቸው ጌሞች ውስጥ ባለው ምናባዊ ዓለም በጣም ስለምመሰጥ ሌላ ዓለም ውስጥ ያለሁ ያህል ነበር፤ ከቤተሰቦቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ አልነበረኝም።”—አንድሩ

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም በየቀኑ ምን ያህል ሰዓት ብታሳልፍ ተገቢ ይመስልሃል? ․․․․․

ወላጆችህስ ምን ያህል ሰዓት ብታሳልፍ ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸዋል? ․․․․․

የጽሑፍ መልእክት በመላላክ፣ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ፎቶዎችንና አንዳንድ ሐሳቦችን ድረ ገጽ ላይ በማስቀመጥ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በመጫወትና በመሳሰሉት ነገሮች በየቀኑ በአጠቃላይ ምን ያህል ሰዓት ታሳልፋለህ? ․․․․․

ለጥያቄዎቹ ከሰጠኸው መልስ አንጻር የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም የምታሳልፈው ጊዜ ከልክ ያለፈ እንደሆነ ይሰማሃል?

□ አዎ □ አይ

ማቆም አለመቻል ወይም አለመፈለግ። “ወላጆቼ ሁልጊዜ የጽሑፍ መልእክት ስላላክ ስለሚመለከቱኝ በጣም እንዳበዛሁት ይነግሩኛል። ከእኩዮቼ አንጻር ግን እኔ እንዳውም ያን ያህል አልላላክም። እርግጥ ከወላጆቼ አንጻር ከታየ የእኔ ይበልጣል። ግን’ኮ እኔንና ወላጆቼን ማወዳደር ፖምን ከብርቱካን ጋር እንደ ማወዳደር ነው፤ እነሱ 40 እኔ ግን ገና 15 ዓመቴ ነው።”—አለን

ወላጆችህ ወይም ጓደኞችህ አንዳንድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ብዙ ጊዜ እንደምታሳልፍ ነግረውህ ያውቃሉ?

□ አዎ □ አይ

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በመጠቀም የምታሳልፈውን ጊዜ መቀነስ አቅቶሃል? ወይም እንዲህ ማድረግ አትፈልግም?

□ አዎ □ አይ

ጉዳት የሚያስከትል። “ጓደኞቼ ሁልጊዜ ሌላው ቀርቶ መኪና እየነዱ እንኳ የጽሑፍ መልእክት ይላላካሉ። ይህ በጣም አደገኛ ነው!”—ጁሊ

“ሞባይል መያዝ የጀመርኩ ሰሞን ለሰው ሁሉ እደውል ነበር፤ የጽሑፍ መልእክትም ቢሆን የማልክለት ሰው አልነበረም። ሌላ ሥራ አልነበረኝም ማለት እችላለሁ። ይህም ከቤተሰቤ ሌላው ቀርቶ ከአንዳንድ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት እንኳ አበላሽቶብኛል። አሁን ግን ከጓደኞቼ ጋር እያወራሁ እያለ መሃል ላይ እያቋረጡ ‘ቆይ አንድ ጊዜ፣ ለዚህ መልእክት መልስ መስጠት አለብኝ’ ሲሉኝ አንድ ነገር አስተዋልኩ። ከእነዚህ ጓደኞቼ ጋር እንዳልቀራረብ እንቅፋት የሆነብኝ አንዱ ምክንያት ይህ ነው።”—ሸርሊ

መኪና እየነዳህ፣ ክፍል ውስጥ ሆነህ ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እያለህ የጽሑፍ መልእክት ታነብባለህ ወይም ትልካለህ?

□ አዎ □ አይ

ከቤተሰብህ ወይም ከጓደኞችህ ጋር እያወራህ እያለ ለተላከልህ የኢ-ሜይል ወይም የሞባይል መልእክት መልስ ለመስጠት አሊያም ስልክ ለማንሳት ስትል በተደጋጋሚ ወሬውን ታቋርጣለህ?

□ አዎ □ አይ

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የእንቅልፍ ጊዜህን ይሻሙብሃል ወይም ከጥናትህ ያዘናጉሃል?

□ አዎ □ አይ

እስካሁን ካየናቸው ነጥቦች አንጻር አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ይሰማሃል? ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ልብ በል።

ሚዛናዊ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

ኮምፒውተር፣ ሞባይል ወይም ሌላ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ የምትጠቀም ከሆነ ከዚህ በታች ያሉትን አራት ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱትን ምክሮች መከተልህ እንዲሁም ልታደርጋቸው ስለሚገቡና ስለማይገቡ ነገሮች ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ በተግባር ማዋልህ ከአደጋ የሚጠብቅህ ከመሆኑም በላይ በአጠቃቀምህ ረገድ ገደብ እንድታበጅ ይረዳሃል።

ይዘቱ ምን ይመስላል? “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8

✔ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ከጓደኞችህና ከቤተሰብህ አባላት ጋር ለመገናኘት እንዲሁም የሚያንጹ ነገሮችን ለመለዋወጥ ተጠቀምባቸው።—ምሳሌ 25:25፤ ኤፌሶን 4:29

X ሐሜት አታሰራጭ፣ የብልግና መልእክቶችንም ሆነ ምስሎችን አትላክ፤ እንዲሁም ወራዳ የሆኑ ፕሮግራሞችን ወይም የቪዲዮ ክሊፖችን አትመልከት።—ቆላስይስ 3:5፤ 1 ጴጥሮስ 4:15

የምጠቀመው መቼ ነው? “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1

✔ ስልክ በመደዋወል፣ መልእክት በመላላክ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት ወይም ጌም በመጫወት ምን ያህል ጊዜ ብታሳልፍ ተገቢ እንደሚሆን ወስን።

X የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን የምትጠቀምበት መንገድ ከጓደኞችህና ከቤተሰብህ ጋር ለማሳለፍ እንዲሁም ለማጥናትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የመደብከውን ጊዜ እንዲነካብህ አትፍቀድ።—ኤፌሶን 5:15-17፤ ፊልጵስዩስ 2:4

የምቀራረበው ከእነማን ጋር ነው? “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮንቶስ 15:33

✔ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን፣ ጥሩ ልማድ እንድታዳብር ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ለማጠናከር ተጠቀምባቸው።—ምሳሌ 22:17

X ራስህን አታታልል፤ በኢ-ሜይል፣ በሞባይል፣ በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የምታገኛቸው ሰዎች የሚመሩባቸው መሥፈርቶች፣ አነጋገራቸውና አስተሳሰባቸው ወደ አንተ መጋባቱ አይቀርም።—ምሳሌ 13:20

ምን ያህል ጊዜ እያጠፋሁ ነው? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

✔ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፍ መዝግብ።

X ጓደኞችህ ወይም ወላጆችህ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ብዙ ጊዜ እንደምታባክን ከነገሩህ አስተያየታቸውን ችላ አትበል።—ምሳሌ 26:12

ቀደም ሲል የተጠቀሰው አንድሩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለ መጠቀም የሰጠው ሐሳብ ነገሩን ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል። እንዲህ ብሏል፦ “የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በጣም አስደሳች እንደሆኑ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ጊዜያችንን እንዳናባክን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ቴክኖሎጂ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ እንዲያርቀኝ መፍቀድ እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ።”

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 30 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ወጣ ብለህ ለመዝናናት እንዲፈቅዱልህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“በራስህ አመለካከት ጥበበኛ አትሁን። ይሖዋን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።”—ምሳሌ 3:7 NW

ጠቃሚ ምክር

የስልክ አጠቃቀምህን ለመቆጣጠር እንድትችል፣ በሞባይል ወይም በኢ-ሜይል ለሚላኩልህ መልእክቶች አሊያም ለስልክ ጥሪዎች ወዲያውኑ ምላሽ የማትሰጥባቸው ጊዜያት እንዳሉ ለጓደኞችህ ንገራቸው።

ይህን ታውቅ ነበር?

በኢንተርኔት ድረ ገጾች ላይ የምታስቀምጣቸውን ፎቶ ግራፎችና ስላደረግሃቸው ነገሮች የምታሰፍራቸውን ሐሳቦች ከበርካታ ዓመታት በኋላም ማየት ይቻላል፤ ሥራ ሊቀጥሩህ የሚያስቡ ወይም ሌሎች ሰዎች እነዚህን መረጃዎች የማግኘት አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የ ․․․․․ አጠቃቀሜን መቆጣጠር ካስቸገረኝ በሳምንት ውስጥ በዚህ መሣሪያ ․․․․․ ሰዓት ብቻ ለመጠቀም እወስናለሁ።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መጠቀም ሱስ እንደሆነብህ ማስተዋል ሊከብድህ የሚችለው ለምን ይመስልሃል?

● በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አጠቃቀምህ ረገድ ገደብ ማበጀት ካልቻልህ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 262 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ቴሌቪዥን የማየት ሱሴን ለማሸነፍ የረዱኝ በርካታ ነገሮች አሉ። ቴሌቪዥን በማየት በማሳልፈው ጊዜ ረገድ ገደብ ለማበጀት ከፍተኛ ጥረት አደረግሁ። ይህን ችግሬን በተመለከተ ከእናቴ ጋር ሁልጊዜ እናወራለን። እንዲሁም ደጋግሜ መጸለዬ ረድቶኛል።”—ካትሊን

[በገጽ 263 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችህን ትቆጣጠራቸዋለህ ወይስ እነሱ ይቆጣጠሩሃል?