በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ ክፍል—ወላጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች

ተጨማሪ ክፍል—ወላጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች

ተጨማሪ ክፍል

ወላጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች

“ልጄ ስሜቱን አውጥቶ እንዲነግረኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?”

“ልጄ የተወሰነለትን ሰዓት ጠብቆ ቤት እንዲገባ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?”

“ልጄ በአመጋገብ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት እንድታዳብር ልረዳት የምችለው እንዴት ነው?”

በዚህ ተጨማሪ ክፍል ውስጥ መልስ ከሚያገኙት 17 ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ እነዚህ ናቸው። ይህ መረጃ ስድስት ክፍሎች አሉት፤ በእነዚህ ክፍሎች ላይ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 እና ጥራዝ 2 ላይ የሚገኙ ከእያንዳንዱ ጥያቄ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ምዕራፎችም ተጠቅሰዋል።

ይህን ክፍል አንብቡት። የሚቻል ከሆነ ደግሞ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩበት። ከዚያም በዚህ ክፍል ውስጥ የቀረበውን ምክር ልጆቻችሁን ለመርዳት ተጠቀሙበት። ምክሮቹ የተመሠረቱት በቀላሉ የሚሳሳቱት የሰው ልጆች በሚሰጡት ሐሳብ ላይ ሳይሆን የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። በመሆኑም እምነት ልትጥሉባቸው ትችላለችሁ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

290  መነጋገር

297  መመሪያ

302  ነፃነት

307  የፆታ ግንኙነት እና የፍቅር ጓደኝነት

311  ስሜት

315  መንፈሳዊነት

 መነጋገር

ከትዳር ጓደኛዬ ወይም ከልጆቼ ጋር መጨቃጨቅ ምን ያህል ጉዳት አለው?

በትዳር ውስጥ አለመግባባቶች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። አለመግባባት ሲፈጠር የምትወስዱት እርምጃ ግን በእናንተ ላይ የተመካ ነው። በወላጆች መካከል የሚፈጠረው ጭቅጭቅ በልጆች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ይህም ሊያሳስባችሁ የሚገባ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ልጆቻችሁ ወደፊት ትዳር ቢመሠርቱ የእናንተን ምሳሌ መከተላቸው አይቀርም። (ምሳሌ 22:6) በመካከላችሁ አለመግባባት ሲፈጠር ይህን አጋጣሚ ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ግጭቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። እስቲ የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦

አዳምጡ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንን እንዲሁም ለመናገርና ለቁጣ የዘገየን’ እንድንሆን ይመክረናል። (ያዕቆብ 1:19) ‘በክፉ ፋንታ ክፉ በመመለስ’ በእሳት ላይ ጭድ አትጨምሩ። (ሮሜ 12:17) የትዳር ጓደኛችሁ ሊያዳምጣችሁ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በሚሰማችሁ ጊዜም እንኳ እናንተ ማዳመጣችሁ ጠቃሚ ነው።

የትዳር ጓደኛችሁን ሳትነቅፉ የተሰማችሁን ለመግለጽ ሞክሩ። የትዳር ጓደኛችሁ ያደረገው ነገር እንዴት እንደጎዳችሁ በሰከነ መንፈስ ግለጹ። (ለምሳሌ፣ “እንዲህ ስታደርግ ይከፋኛል።”) የትዳር ጓደኛችሁን ከመውቀስ ወይም ከመንቀፍ ተቆጠቡ። (ለምሳሌ፣ “ድሮም አንተ የእኔ ነገር አያሳስብህም።” “በጭራሽ አታዳምጠኝም።”)

ጉዳዩን ለጊዜው ተወት አድርጉት። አንዳንድ ጊዜ ውይይቱን ለጊዜው ማቆምና ንዴታችሁ በረድ ሲል መቀጠሉ በጣም የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 17:14

አንዳችሁ ሌላውን አስፈላጊ ከሆነም ልጆቻችሁን ይቅርታ ጠይቁ። ብሪያን የተባለች የ14 ዓመት ልጅ “አንዳንድ ጊዜ ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ፣ ሁኔታው እኔንና ታላቅ ወንድሜን ምን ያህል እንደሚያስጨንቀን ስለሚገባቸው በኋላ ላይ ይቅርታ ይጠይቁናል” ብላለች። ለልጆቻችሁ ከምታስተምሯቸው በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች አንዱ በትሕትና ይቅርታ መጠየቅ ነው።

ይሁንና ጭቅጭቁ የተፈጠረው በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ቢሆንስ? ሳታስቡት ሁኔታውን የሚያባብስ ነገር እያደረጋችሁ እንዳይሆን ቆም ብላችሁ አስቡ። ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራፍ 2 ገጽ 15 ላይ የተገለጸውን ሁኔታ ተመልከቱ። የሬቸል እናት ለጭቅጭቁ መፈጠር አስተዋጽኦ ያደረገችባቸውን አንዳንድ መንገዶች መጥቀስ ትችላላችሁ? እናንተስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦

● “አንተ ሁልጊዜ . . .” ወይም “አንተ ፈጽሞ . . .” እንደሚሉት ያሉ የተጋነኑ አነጋገሮችን ከመጠቀም ተቆጠቡ። እንደዚህ ያሉት አነጋገሮች ልጃችሁ ራሱን ለመከላከል ሲል እንዲከራከራችሁ ከማድረግ ውጪ የሚፈይዱት ነገር የለም። ደግሞም እንዲህ ያሉ ንግግሮች የተጋነኑ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ልጃችሁም ቢሆን ይህን ያውቃል። እንዲህ የተናገራችሁት እናንተ በጣም ስለተናደዳችሁ እንጂ ያን ያህል የሚያስቆጣ ስህተት ስለሠራ እንዳልሆነም መገንዘቡ አይቀርም።

● ወቀሳው እሱ ላይ እንዲያነጣጥር ከማድረግ (ለምሳሌ፣ “አንተ . . .” ከማለት) ይልቅ የልጃችሁ ባሕርይ እናንተን ምን ያህል እንዳሳዘናችሁ ለመግለጽ ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ “እንዲህ ስታደርግ . . . ይሰማኛል” ማለት ትችላላችሁ። ለእናንተ ባይመስላችሁም እንኳ ልጃችሁ ስሜታችሁን መጉዳት አይፈልግም። በመሆኑም ምን ያህል እንዳሳዘናችሁ ለልጃችሁ መግለጻችሁ እናንተን እንዲሰማ ሊያነሳሳው ይችላል። *

● ቁጣችሁ እስኪበርድ መታገስ ከባድ ሊሆን ቢችልም እንደተቆጣችሁ ከመናገር ተቆጠቡ። (ምሳሌ 29:22) የጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆነው የቤት ውስጥ ሥራ ከሆነ ጉዳዩን ከልጃችሁ ጋር ተወያዩበት። ከእሱ የሚጠበቀው ምን እንደሆነ በጽሑፍ አስፍሩ፤ ልጁ የሚጠበቅበትን ነገር ካልፈጸመ የሚከተለውን ቅጣት በግልጽ መናገርም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። የልጃችሁ አመለካከት ስህተት መስሎ ቢሰማችሁም እንኳ ሲናገር በትዕግሥት አዳምጡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ መመሪያ ከምታዥጎደጉዱባቸው ይልቅ በትኩረት ብታዳምጧቸው ለምትሰጧቸው ምክር የተሻለ ምላሽ ይሰጣሉ።

● በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ ዓመፀኛ እንደሆነ ለመደምደም ከመቸኮል ይልቅ በልጃችሁ ላይ የምትመለከቱት አብዛኛው ነገር የእድገቱ ክፍል መሆኑን ለመረዳት ሞክሩ። ልጃችሁ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚከራከራችሁ ማደጉን ለማሳየት ሲል ብቻ ሊሆን ይችላል። እናንተም ከእሱ ጋር ለመጨቃጨቅ ብትፈተኑም ይህን ከማድረግ ተቆጠቡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ልጃችሁ፣ እናንተ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥማችሁ መልስ የምትሰጡበትን መንገድ በመመልከት ትምህርት ሊወስድ እንደሚችል አትዘንጉ። ታጋሽ እና ሆደ ሰፊ በመሆን ረገድ ምሳሌ ከሆናችሁ ልጃችሁም እነዚህን ባሕርያት ያዳብራል።—ገላትያ 5:22, 23

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 2⁠ን እና ጥራዝ 2 ምዕራፍ 24⁠ን ተመልከት

ስለ ቀድሞ ሕይወቴ ለልጆቼ ምን ያህል መንገር አለብኝ?

ከባለቤትሽ፣ ከሴት ልጅሽና ከወዳጆቻችሁ ጋር ራት እየበላችሁ ነው እንበል። እየተጨዋወታችሁ እያለ ጓደኛሽ፣ ከባለቤትሽ ጋር ከመተዋወቃችሁ በፊት የፍቅር ጓደኛሽ ስለነበረ ሰው አነሳች። በዚህ ጊዜ ልጅሽ በጣም ተገርማ “ከአባዬ በፊት ከሌላ ሰው ጋር ትጠናኚ ነበር ማለት ነው?” አለችሽ። ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ለልጅሽ አውርተሽላት አታውቂም። በመሆኑም ልጅሽ ስለ ታሪኩ ለማወቅ ፈለገች። ታዲያ ምን ታደርጊያለሽ?

አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ መስጠቱ የተሻለ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው ጥያቄ መልስ መስጠታቸው ከልጆቻቸው ጋር የልባቸውን አውጥተው ለመነጋገር አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ብዙ ወላጆች የሚፈልጉት ነገር ነው።

ታዲያ ለልጆቻችሁ በወጣትነታችሁ ስላሳለፋችሁት ሕይወት ምን ያህል መንገር ይኖርባችኋል? በእርግጥ፣ የሚያሳፍሩ ነገሮችን መናገር እንደማትፈልጉ የታወቀ ነው። ሆኖም ያጋጠሟችሁን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መናገራችሁ ልጆቹን ሊጠቅማቸው ይችላል። እንዴት?

አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው። . . . እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” ብሏል። (ሮም 7:21-24) ይሖዋ አምላክ ይህ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብና እስከ ዛሬ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። ደግሞም ጳውሎስ በግልጽ የተናገረውን ይህን ሐሳብ የማይጋራ ሰው ስለሌለ ሁላችንም ጥቅም እናገኝበታለን።

በተመሳሳይም ልጆቻችሁ ስላደረጋችኋቸው ጥሩ ምርጫዎች ብቻ ሳይሆን ስለሠራችኋቸው ስህተቶችም ጭምር ማወቃቸው እናንተም በወጣትነታችሁ እንደ እነሱ እንደነበራችሁ እንዲረዱ ያስችላቸዋል። እርግጥ ነው፣ እናንተ ያደጋችሁበት ዘመን ከአሁኑ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ ዘመኑ ቢለወጥም የሰው ተፈጥሮም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አይለወጡም። (መዝሙር 119:144) ስላጋጠሟችሁ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና እንዴት እንደተወጣችኋቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻችሁ ጋር መወያየታችሁ እነሱም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመወጣት ሊረዳቸው ይችላል። ካመረን የተባለ ወጣት “ወላጆችህም እንደ አንተው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው እንደነበር ማወቅህ እነሱም እንደ አንተው ዓይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ እንድትገነዘብ ያደርግሃል” ሲል ተናግሯል። አክሎም “የሆነ ችግር ሲያጋጥምህ ‘ወላጆቼም እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሟቸው ይሆን?’ ብለህ ታስባለህ” ብሏል።

ይሁንና ስላሳለፋችሁት ሕይወት በነገራችኋቸው ቁጥር ምክር ልታክሉበት ይገባል ማለት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋችኋል። እውነት ነው፣ ‘በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችን የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ’ ወይም ‘እነሱም ተመሳሳይ ስህተት ቢፈጽሙ ምንም ማለት እንዳልሆነ አድርገው ያስባሉ’ ብላችሁ ትሰጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ ከታሪኩ እንዲያገኙ የምትፈልጉትን ትምህርት ለመጠቆም ከመሞከር ይልቅ (ለምሳሌ፣ “አንተም ፈጽሞ እንዲህ ማድረግ የሌለብህ ለዚህ ነው”) ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማችሁ ብቻ በአጭሩ ተናገሩ (ለምሳሌ፣ “አሁን ሳስበው ያኔ እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምክንያቱም . . .”)። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ ምክር እየተሰጣቸው እንደሆነ ሳይሰማቸው ከእናንተ ተሞክሮ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።—ኤፌሶን 6:4

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 1⁠ን ተመልከት

ልጄ ስሜቱን አውጥቶ እንዲነግረኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ልጆቻችሁ ትንሽ እያሉ ምንም የሚደብቋችሁ ነገር አልነበረም። አንድ ነገር ስትጠይቋቸው መልስ የሚሰጡት በደስታ ነበር። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ገና ሳትጠይቋቸው ሁሉን ነገር ዝክዝክ አድርገው ይነግሯችሁ ነበር፤ በምሳሌያዊ አነጋገር በራሱ ቡልቅ እያለ እንደሚወጣ ፍልውኃ ነበሩ። ልጆቻችሁ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲገቡ ግን ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማድረግ እየደረቀ ካለ ጉድጓድ ውኃ ስቦ የማውጣት ያህል ከባድ ሊሆን ይችላል። ‘ከጓደኞቻቸው ጋር እንደ ልብ ያወራሉ፤ ታዲያ ለእኔ ስሜታቸውን መግለጽ የማይፈልጉት ለምንድን ነው?’ ትሉ ይሆናል።

ልጆቻችሁ እንደ ድሮው ለማውራት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ብቻ በሕይወታቸው ውስጥ እንድትገቡ እንደማይፈልጉ ሊሰማችሁ አይገባም። እውነቱን ለመናገር የእናንተ እርዳታ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው አሁን ነው። ደስ የሚለው ደግሞ፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ አብዛኞቹ ልጆች ከእኩዮቻቸው ወይም ከመገናኛ ብዙኃን ከሚያገኙት ምክር እንኳ ይበልጥ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ምክር ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ።

ታዲያ ልጆቻችሁ ስሜታቸውን አውጥተው ለእናንተ ከመናገር ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ የሰጡትን ሐሳብ ተመልከቱ። ከዚያም በቀረቡት ጥያቄዎች አማካኝነት ራሳችሁን ፈትሹ፤ እንዲሁም ጥቅሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥታችሁ አንብቡ።

“አባቴ በሥራ ቦታም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ብዙ የሚያከናውናቸው ነገሮች ስላሉት እሱን ቀርቤ ማነጋገር ይከብደኛል። ከእኔ ጋር ለመነጋገር ምንም ጊዜ ያለው አይመስልም።”—አንድሩ

‘እኔ ባይታወቀኝም ልጆቼ ጊዜ እንደሌለኝ ሆኖ እንዲሰማቸው እያደረግሁ ይሆን? ከሆነ በቀላሉ እንዲቀርቡኝ ምን ማድረግ እችላለሁ? ከልጆቼ ጋር የማወራበት ቋሚ ጊዜ ለመመደብ ምን ማድረግ እችላለሁ?’—ዘዳግም 6:7

“በትምህርት ቤት ከልጆች ጋር ስለተጨቃጨቅንበት ጉዳይ ለእናቴ የነገርኳት እንባ እየተናነቀኝ ነበር። ታጽናናኛለች ብዬ ሳስብ እሷ ግን ተቆጣችኝ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ ስለሚያሳስበኝ ነገር ምንም ነግሬያት አላውቅም።”—ኬንጂ

‘ልጆቼ ችግራቸውን ሲያዋዩኝ መልስ የምሰጣቸው እንዴት ነው? ምክር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ በሚሰማኝ ጊዜም እንኳ ይህን ከማድረጌ በፊት ስሜታቸውን እንደተረዳሁላቸው በሚያሳይ መንገድ አዳምጣቸዋለሁ?’—ያዕቆብ 1:19

“ወላጆች፣ ልጆቻቸው ስሜታቸውን አውጥተው ቢነግሯቸው ሳይቆጡ እንደሚያዳምጧቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፤ ልጆቹ ሐሳባቸውን ሲናገሩ ግን ወላጆቻቸው ብዙውን ጊዜ ይበሳጫሉ። በዚህ ጊዜ ልጆቹ እንደተታለሉ ይሰማቸዋል።”—ሬቸል

‘ልጆቼ አንድ የሚያናድድ ነገር ቢነግሩኝ ቶሎ ላለመበሳጨት ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?’—ምሳሌ 10:19

“ብዙውን ጊዜ ለእናቴ ሚስጥሬን አውጥቼ ስነግራት ወዲያውኑ ለጓደኞቿ ትነግራቸዋለች። ለረጅም ጊዜ በእሷ ላይ እምነት መጣል አቅቶኝ ነበር።”—ቻንቴል

‘ልጆቼ የነገሩኝን ሚስጥር ለሌሎች ባለመናገር ለስሜታቸው እንደምጠነቀቅ አሳያለሁ?’—ምሳሌ 25:9

“ከወላጆቼ ጋር መነጋገር የምፈልገው ብዙ ነገር አለኝ። ይሁንና ውይይቱን እነሱ ቢጀምሩት ደስ ይለኛል።”—ኮርትኒ

‘በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጄ ጋር ጭውውት ለመጀመር ቅድሚያውን መውሰድ እችላለሁ? ለመነጋገር ይበልጥ አመቺ የሚሆነው ጊዜስ መቼ ነው?’—መክብብ 3:7

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሁልጊዜ ለመነጋገር ጥረት ማድረጋቸው ብዙ ጥቅሞች አሉት። በጃፓን የምትኖረው የ17 ዓመቷ ጁንኮ ምን እንዳጋጠማት ልብ በሉ። እንዲህ ብላለች፦ “ከክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የበለጠ የምቀርበው አብረውኝ የሚማሩትን ልጆች እንደሆነ በአንድ ወቅት ለእናቴ በግልጽ ነገርኳት። በቀጣዩ ቀን እናቴ ደብዳቤ ጽፋ ጠረጴዛዬ ላይ አስቀመጠችልኝ። በደብዳቤው ላይ እሷም ከክርስቲያኖች መካከል ጓደኛ የሚሆናት አጥታ የተቸገረችበት ወቅት እንደነበረ የሚገልጽ ሐሳብ ጽፋ ነበር። ከዚያም አብሯቸው ሆኖ የሚያበረታታቸው ሰው ሳይኖር አምላክን ያገለገሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ሰዎችን ጠቀሰችልኝ። በተጨማሪም ጥሩ ጓደኞች ለማግኘት ስላደረግሁት ጥረት አመሰገነችኝ። እንዲህ ያለ ችግር ያጋጠመኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩና እናቴም ተመሳሳይ ነገር ገጥሟት እንደነበር ሳውቅ ተገረምኩ። እንዲያውም በጣም ከመደሰቴ የተነሳ አለቀስኩ። እናቴ በነገረችኝ ነገር በጣም ተበረታታሁ፤ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥንካሬ አገኘሁ።”

ከጁንኮ ተሞክሮ ማየት እንደሚቻለው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች የልባቸውን ሲናገሩ ወላጆቻቸው እንደማይቀልዱባቸው ወይም እንደማይተቿቸው ካወቁ ስሜታቸውን አውጥተው መግለጽ አይከብዳቸውም። ይሁን እንጂ ከልጆቻችሁ ጋር ስትነጋገሩ ቁጣ ቁጣ እንደሚላቸው ወይም እንደሚበሳጩ ካስተዋላችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በዚህ ጊዜ እናንተም ተመሳሳይ ምላሽ ለመስጠት ብትፈተኑም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ተቆጠቡ። (ሮም 12:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:23) ከዚህ ይልቅ ከልጆቻችሁ የምትጠብቁትን አነጋገር እና ባሕርይ በማሳየት ምሳሌ ሁኑ።

የጉርምስና ዕድሜ ልጆቻችሁ ወደ አዋቂነት የሚሸጋገሩበት ጊዜ እንደሆነ አትርሱ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ባሕርያቸው ሊለዋወጥ ይኸውም አንዳንድ ጊዜ እንደ አዋቂ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ልጅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ በሚታይበት በተለይ ደግሞ ለዕድሜው የማይመጥን የልጅ ዓይነት ባሕርይ በሚያሳይበት ጊዜ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ትችት ከመሰንዘር ወይም አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ። ልጃችሁን እንደ ትልቅ ሰው እንደምትመለከቱት በሚያሳይ መንገድ አነጋግሩት። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ለምሳሌ ያህል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ልጃችሁ “ምን ትጨቀጭቁኛላችሁ?” ብሎ ብስለት የሌለው ነገር ቢናገር በቁጣ ለመመለስ ትፈተኑ ይሆናል። እንዲህ ብታደርጉ ግን የውይይቱ አቅጣጫ ሊቀየርና ሌላ ርዕስ ውስጥ ልትገቡ ብሎም ወደ ጭቅጭቅ ልታመሩ ትችላላችሁ። ከዚህ ይልቅ “አሁን በጣም የተናደድክ ይመስለኛል፤ በኋላ ላይ ስትረጋጋ ብንነጋገርስ?” ልትሉት ትችላላችሁ። በዚህ መንገድ ውይይቱ ዓላማውን እንዳይስት ታደርጋላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ደግሞ ጭቅጭቅ ሳይፈጠር መነጋገር የምትችሉበትን አጋጣሚ ታመቻቻላችሁ።

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 1 እና 2⁠ን ተመልከት

 መመሪያ

ልጄ የተወሰነለትን ሰዓት ጠብቆ ቤት እንዲገባ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንዲረዳችሁ እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናችሁ ለመሳል ሞክሩ፦ በሩ በቀስታ ሲከፈት ሰዓታችሁን ተመለከታችሁ፤ ልጃችሁ ቤት መግባት ከነበረበት ሰዓት 30 ደቂቃ አሳልፏል። ‘ይሄን ጊዜ የተኛን መስሎታል’ ብላችሁ አሰባችሁ። እናንተ ግን ልጃችሁ ቤት የሚገባበት ሰዓት ማለፉን ስታዩ በር በሩን እያያችሁ ቁጭ ብላችኋል። ልጃችሁ በሩን ከፍቶ ሲገባ ፊት ለፊት ተገጣጠማችሁ። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? ልጃችሁንስ ምን ትሉታላችሁ?

የተለያዩ አማራጮች አሏችሁ። ‘ያው የልጅ ነገር ስለሆነ ነው’ በማለት ነገሩን ቀለል አድርጋችሁ ልታልፉት ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ ወደ ሌላው ጽንፍ በመሄድ “ከአሁን በኋላ ከዚህች ቤት አትወጣትም!” ልትሉት ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ልጃችሁ ዘግይቶ የመጣበት በቂ ምክንያት ሊኖረው ስለሚችል በስሜት ገንፍላችሁ ከመናገራችሁ በፊት አዳምጡት። ከዚያም በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ለልጃችሁ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ልትሰጡት ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ስለ ጉዳዩ በማግስቱ እንደምትነጋገሩ ለልጃችሁ ግለጹለት። ከዚያም አመቺ ጊዜ ምረጡና ስለተፈጠረው ሁኔታ ምን ልታደርጉ እንዳሰባችሁ አወያዩት። ለምሳሌ አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ቤት መግባት ካለበት ሰዓት ዘግይቶ ከመጣ በሚቀጥለው ጊዜ ከወትሮው 30 ደቂቃ ቀደም ብሎ መመለስ እንዳለበት ይነግሩታል። በሌላ በኩል ደግሞ ልጃችሁ ሁልጊዜ ሰዓቱን በማክበር እምነት የሚጣልበት መሆኑን ካሳየ በአንዳንድ ወቅቶች ተጨማሪ ነፃነት ልትሰጡት ምናልባትም ቤት እንዲገባ የሚጠበቅበትን ሰዓት ገፋ ልታደርጉለት ታስቡ ይሆናል። ልጃችሁ በስንት ሰዓት ቤት መግባት እንዳለበት እንዲሁም ይህንን ካላደረገ ምን ቅጣት እንደሚጠብቀው በግልጽ ማሳወቃችሁ አስፈላጊ ነው። ከዚያም መመሪያውን ከጣሰ ያላችሁትን ከመፈጸም ወደኋላ አትበሉ።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” እንደሚል አስታውሱ። (ፊልጵስዩስ 4:5) ልጃችሁ ቤት እንዲገባ የምትፈልጉበትን ሰዓት ከመወሰናችሁ በፊት ከእሱ ጋር መወያየታችሁ የተሻለ ነው፤ የትኛውን ሰዓት እንደሚመርጥና ይህንን ሰዓት የመረጠበትን ምክንያት ጠይቁት። ልጁ የሚያቀርበውን ሐሳብ ከግምት ለማስገባት ሞክሩ። ከዚህ ቀደም እምነት የሚጣልበት መሆኑን ካስመሠከረና የጠየቀው ነገር ምክንያታዊ ከሆነ እሱ የፈለገው እንዲሆን ልትስማሙ ትችሉ ይሆናል።

ሰዓት ማክበር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። በመሆኑም ልጃችሁ ቤት እንዲገባ የምትፈልጉበትን ሰዓት የምትወስኑት አደጋ እንዳያጋጥመው ለማድረግ ብቻ አይደለም። እንዲህ ስታደርጉ፣ ልጁ ወደፊት ራሱን ችሎ መኖር ሲጀምርም የሚጠቅመው ጥሩ ልማድ እንዲያዳብር እያሠለጠናችሁት ነው።—ምሳሌ 22:6

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 3⁠ን እና ጥራዝ 2 ምዕራፍ 22⁠ን ተመልከት

በአለባበስ ረገድ ከልጆቼ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር መፍታት የምችለው እንዴት ነው?

እስቲ በገጽ 77 ላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ መለስ ብላችሁ ተመልከቱ። ሄዘር የእናንተ ልጅ ነች እንበል። የለበሰችው ልብስ ብጣቂ ነገር እንደሆነ ስለተሰማችሁ እንዳላየ ሆናችሁ ማለፍ አልቻላችሁም። በመሆኑም “በይ የኔ እመቤት፣ ሂጂና ሌላ ልብስ ቀይሪ። አለዚያ እንደዚህ ለብሰሽ ከዚህ ንቅንቅ አትያትም!” አላችኋት። እንዲህ በማለት ልጃችሁ ልብሷን እንድትለውጥ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ደግሞስ ልጃችሁ የተባለችውን ከመፈጸም ሌላ ምን ምርጫ አላት? ይሁን እንጂ ልጃችሁ ልብሷን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቧንም እንድትቀይር ልታሠለጥኗት የምትችሉት እንዴት ነው?

● በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሥርዓታማ ያልሆነ ልብስ መልበስ የሚያስከትለው መዘዝ የእናንተን ያህል ምናልባትም ከዚያ በበለጠ ልጃችሁን እንደሚያስጨንቃት አስታውሱ። እሷም ብትሆን በአለባበሷ የተነሳ የሌሎች መሳቂያ መሆን ወይም አላስፈላጊ ትኩረት መሳብ አትፈልግም። ስለዚህ ልከኛ ያልሆነ ልብስ መልበሷ አምራ እንድትታይ እንደማያደርጋት ግለጹላት፤ እንዲሁም ይህንን ያላችሁበትን ምክንያት ረጋ ብላችሁ አስረዷት። * አማራጭ ሐሳቦችንም አቅርቡላት።

● ሁለተኛ፣ ምክንያታዊ ሁኑ። ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልብሱን ያልወደድኩት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ነው? ወይስ የእኔ ምርጫ ስላልሆነ?’ (2 ቆሮንቶስ 1:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ታዲያ የምርጫ ጉዳይ ከሆነ ልጃችሁ ልብሱን እንድትለብስ ልትፈቅዱላት ትችላላችሁ?

● ሦስተኛ፣ አንዳንድ ልብሶች ተገቢ እንዳልሆኑ በመናገር ብቻ ከመወሰን ይልቅ ተስማሚ የሆኑ ልብሶችን እንድታገኝም እርዷት። ከልጃችሁ ጋር በአለባበስ ረገድ ስትወያዩ በገጽ 82 እና 83 ላይ የሚገኘውን መልመጃ መጠቀም ትችላላችሁ። ጊዜ ወስዳችሁ ይህን ለማድረግ መጣራችሁ ይክሳችኋል።

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 11⁠ን ተመልከት

ልጄ የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን እንዲጫወት ልፈቅድለት ይገባል?

በዛሬው ጊዜ ያሉት የኤሌክትሮኒክ ጌሞች እናንተ ወጣት በነበራችሁበት ወቅት ከምታውቋቸው ጌሞች በጣም የተለዩ ናቸው። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁ የኤሌክትሮኒክ ጌሞች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ እንዲያውቅና ከእነዚህ አደጋዎች እንዲጠበቅ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በጥቅሉ ማውገዝ ወይም እንዲህ ያሉ ጌሞች ጊዜ ከማባከን ሌላ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው መግለጽ የሚፈይደው ነገር የለም። መጥፎ የሆኑት ሁሉም ጌሞች እንዳልሆኑ አስታውሱ። ይሁን እንጂ ጌሞች ሱስ ሊያስይዙ ይችላሉ። በመሆኑም ልጃችሁ ጌም በመጫወት ምን ያህል ጊዜ እንደሚያሳልፍ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በተጨማሪም ልጃችሁ የሚወደው የትኞቹን ጌሞች እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። ልጃችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ልትጠይቁትም ትችላላችሁ፦

● አብረውህ የሚማሩት ልጆች በጣም የሚወዱት ጌም የትኛው ነው?

● ጌሙ ምን ዓይነት ነው?

● ጌሙ ይህን ያህል ተወዳጅ የሆነው ለምን ይመስልሃል?

ልጃችሁ እናንተ ከጠበቃችሁት በላይ ስለ ኤሌክትሮኒክ ጌሞች እንደሚያውቅ ታስተውሉ ይሆናል! ምናልባትም ጥሩ እንዳልሆኑ የምታስቧቸውን ጌሞች ተጫውቶ ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ ስሜታዊ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ። እንዲያውም ይህን አጋጣሚ ልጃችሁ የማስተዋል ችሎታውን እንዲያዳብር ለመርዳት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ።—ዕብራውያን 5:14

ልጃችሁ ተገቢ ያልሆኑ የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን መጫወት የሚያስደስተው ለምን እንደሆነ እንዲያስተውል አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቁት። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ፦

● ይህን ጌም እንድትጫወት ስላልተፈቀደልህ ከጓደኞችህ የተለየህ እንደሆንህ ይሰማሃል?

አንዳንድ ወጣቶች አንድን ጌም የሚጫወቱት ከእኩዮቻቸው ጋር የሚያወሩት ነገር ለማግኘት ብለው ሊሆን ይችላል። ልጃችሁ ጌሙን የተጫወተበት ምክንያት ይህ እንደሆነ ማወቃችሁ ጉዳዩን በምትይዙበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል፤ ምክንያቱም ልጁ ዘግናኝ ዓመፅና የፆታ ብልግና ያለበትን ጌም የሚወድ ከሆነ ምላሽ የምትሰጡበት መንገድ የተለየ እንደሚሆን የታወቀ ነው።—ቈላስይስ 4:6

ይሁን እንጂ ልጃችሁን የሚስቡት በጌሙ ውስጥ ያሉት መጥፎ ነገሮች ቢሆኑስ? አንዳንድ ወጣቶች በጌሙ ላይ የሚታየው አሰቃቂ ነገር እውነተኛ ስላልሆነ ምንም ተጽዕኖ እንደማያሳድርባቸው ለማሳመን ይጥሩ ይሆናል። ‘ጌሙ ላይ አደረግሁት ማለት የእውነት አደርገዋለሁ ማለት አይደለም’ ይላሉ። የእናንተም ልጅ እንዲህ የሚሰማው ከሆነ መዝሙር 11:5 ላይ ያለውን ሐሳብ አሳዩት። በጥቅሱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ እንዲያጣ የሚያደርገው ዓመፀኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓመፅን መውደዱም ጭምር ነው። የፆታ ብልግናን ወይም በአምላክ ቃል ውስጥ የተወገዘን ሌላ መጥፎ ምግባር በተመለከተም ይኸው መመሪያ ይሠራል።—መዝሙር 97:10

ልጃችሁ ከኤሌክትሮኒክ ጌሞች ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለበት ከተሰማችሁ እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦

● የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን ሌሎች በማያዩት ቦታ ለምሳሌ በመኝታ ክፍሉ ሆኖ እንዲጫወት አትፍቀዱ።

● ደንብ አውጡ፤ ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ ጌም ከመጫወቱ በፊት የቤት ሥራውን መጨረስ ወይም ራት መብላት አሊያም ደግሞ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ንገሩት።

● አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግን የሚጠይቁ ሌሎች ጨዋታዎች ያላቸውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጋችሁ ግለጹለት።

● ልጃችሁ የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን ሲጫወት ተመልከቱት፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አብራችሁት ብትጫወቱ ጥሩ ነው።

እርግጥ ነው፣ መዝናኛን በተመለከተ ልጆቻችሁን በነፃነት መምከር እንድትችሉ እናንተ ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባችሁ። በመሆኑም ‘የምመለከታቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ምን ዓይነት ናቸው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። እናንተ የምታደርጉት ነገር ከልጆቻችሁ ከምትጠብቁት የሚለይ ከሆነ ልጆቻችሁ ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም!

ጥራዝ 2 ምዕራፍ 30⁠ን ተመልከት

ልጄ ሞባይል፣ ኮምፒውተር ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱስ ከሆኑበት ምን ማድረግ እችላለሁ?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ኢንተርኔት በመጠቀም ወይም የጽሑፍ መልእክት በመላላክ ብዙ ሰዓት ያጠፋል? አሊያም ደግሞ ከእናንተ ጋር ጊዜ ከማሳለፍ ይልቅ ኤምፒ3 ማጫወቻውን ተጠቅሞ መዝናናት ይመርጣል? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ቀላሉ መንገድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያውን ከልጃችሁ መንጠቅ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። ሁሉም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጥፎ እንደሆኑ ማሰቡ ግን ተገቢ አይደለም። እናንተም ብትሆኑ በወላጆቻችሁ ዘመን ያልነበሩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን እንደምትጠቀሙ ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው የልጃችሁን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ከመንጠቅ ይልቅ (እንዲህ ለማድረግ የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት እስከሌላችሁ ድረስ) ይህን አጋጣሚ ልጃችሁ መሣሪያውን ሚዛናዊነትና ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚችል ለማሠልጠን ለምን አትጠቀሙበትም? ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ከልጃችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት። አንደኛ፣ ጉዳዩ ያሳሰባችሁ ለምን እንደሆነ ግለጹለት። ሁለተኛ፣ ሐሳቡን ሲገልጽ አዳምጡት። (ምሳሌ 18:13) ሦስተኛ፣ ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ እንደሚቻል ተወያዩበት። ተገቢ መስሎ ከታያችሁ ጥብቅ የሆነ ገደብ ከመጣል ወደኋላ አትበሉ፤ ይሁንና ምክንያታዊ ሁኑ። ኤለን የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ የጽሑፍ መልእክት መላላክ እንዳበዛሁ በተሰማቸው ወቅት ሞባይሌን አልቀሙኝም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንድ ደንቦችን አወጡልኝ። ወላጆቼ እንዲህ ማድረጋቸው እነሱ አጠገቤ በማይኖሩበት ጊዜም እንኳ በሞባይል አጠቃቀሜ ረገድ ሚዛናዊ እንድሆን ረድቶኛል።”

ልጃችሁ ምክራችሁን ለመቀበል ቢያንገራግርስ? ያደረጋችሁት ጥረት ድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ እንደሆነ አይሰማችሁ። ከዚህ ይልቅ ትዕግሥተኞች በመሆን ልጃችሁ በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጊዜ ስጡት። ምናልባትም በሐሳባችሁ ተስማምቶ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ ያደርግ ይሆናል። የበርካታ ወጣቶች ሁኔታ ሄሊ ከተባለች ወጣት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፤ ሄሊ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ኮምፒውተር መጠቀም ሱስ እንደሆነብኝ ሲነግሩኝ መጀመሪያ ላይ ቅር ብሎኝ ነበር፤ በኋላ ግን በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ባሰብኩበት ቁጥር እነሱ ትክክል እንደሆኑ እየገባኝ መጣ።”

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 36⁠ን ተመልከት

 ነፃነት

ለልጄ ምን ያህል ነፃነት ልሰጠው ይገባል?

ጉዳዩ ‘በልጄ የግል ሕይወት መግባት አለብኝ ወይስ የለብኝም?’ የሚል በሚሆንበት ጊዜ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ያን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ልጃችሁ መኝታ ክፍሉ ውስጥ በሩን ዘግቶ ተቀምጧል። ሳታንኳኩ ዘው ብላችሁ ብትገቡ ትክክል ይሆናል? ወይም ደግሞ ልጃችሁ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስትጣደፍ ሞባይሏን ረስታ ወጥታለች እንበል። ስልኳን አንስታችሁ ከሌሎች ጋር የተጻጻፈቻቸውን መልእክቶች ብታነብቡ ተገቢ ይሆናል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ቀላል አይደለም። በአንድ በኩል፣ ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙት ልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ምን እየተፈጸመ እንዳለ የማወቅ መብትም ሆነ ልጆቻችሁን ከጉዳት የመጠበቅ ግዴታ አለባችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱን የልጆቻችሁን እንቅስቃሴ ለማወቅ መሞከር ወይም ሁልጊዜ መግቢያ መውጪያቸውን መቆጣጠር አትችሉም። ታዲያ በዚህ ረገድ ሚዛናችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

አንደኛ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ስለ ግል ሕይወቱ ሌሎች እንዳያውቁ የሚፈልገው መጥፎ ነገር ስለሚሠራ ብቻ ላይሆን እንደሚችል መረዳት ይኖርባችኋል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ፍላጎት ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነገር ነው። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በዚህ ረገድ የተወሰነ ነፃነት ማግኘታቸው፣ በራሳቸው ጓደኝነት መመሥረት እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ ተጠቅመው መፍትሔ መፈለግ እንደሚችሉ ራሳቸውን ለመፈተን ይረዳቸዋል። (ሮም 12:1, 2) በተጨማሪም የማመዛዘን ችሎታ እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ሲሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህም ሌላ ብቻቸውን የሚሆኑበት ጊዜ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ውሳኔ ከማድረጋቸው ወይም አስቸጋሪ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠታቸው በፊት ለማሰላሰል አጋጣሚ ይኖራቸዋል።—ምሳሌ 15:28

ሁለተኛ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን በጥቃቅኗ ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጠር መሞከር እንዲማረርና እንዲያምፅ ሊያደርገው እንደሚችል አስታውሱ። (ኤፌሶን 6:4፤ ቆላስይስ 3:21) ታዲያ ይህ ሲባል ልጃችሁን መቆጣጠሩን እርግፍ አድርጋችሁ መተው አለባችሁ ማለት ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም ልጃችሁ ቢጎረምስም አሁንም ወላጆቹ ናችሁ። ይሁን እንጂ ግባችሁ፣ ልጃችሁ ሕሊናውን እንዲያሠለጥን መርዳት ሊሆን ይገባል። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ምሳሌ 22:6) ደግሞም እያንዳንዱን የልጃችሁን እንቅስቃሴ እንደ ፖሊስ ከመከታተል ይልቅ አስፈላጊውን ሥልጠና መስጠት የበለጠ ውጤታማ ነው።

ሦስተኛ፣ ጉዳዩን በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጃችሁ ጋር ተወያዩበት። በዚህ ረገድ የሚሰማውን ሲናገር አዳምጡት። አንዳንድ ጊዜ የእሱን ሐሳብ ማስተናገድ ትችሉ ይሆን? ልጃችሁ እምነት የሚጣልበት መሆኑን እስካስመሠከረ ድረስ በግል ሕይወቱ ጣልቃ ባለመግባት በተወሰነ መጠን ነፃነት እንደምትሰጡት እንዲገነዘብ አድርጉ። አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውጤት ግለጹለት፤ መመሪያችሁን ከጣሰ ደግሞ ተገቢውን ቅጣት ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ። በአንድ ነገር እርግጠኞች ሁኑ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ችግር ውስጥ እንዳይገባ የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን ችላ ሳትሉ በተወሰነ መጠን ነፃነቱን ልታከብሩለት ትችላላችሁ።

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 3 እና 15⁠ን ተመልከት

ልጄ እስከ ስንተኛ ክፍል መማር ይኖርበታል?

“አስተማሪዎቼ አሰልቺ ናቸው!” “የቤት ሥራ በጣም ይበዛብኛል!” “የማለፊያ ውጤት እንኳ የማገኘው በስንት መከራ ነው፤ ታዲያ ምን አለፋኝ?” አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ ስለሚሰማቸውና ተስፋ ስለሚቆርጡ ገቢ ለማግኘት የሚያስችላቸውን እውቀት ከመቅሰማቸው በፊት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ያስባሉ። የእናንተም ልጅ ትምህርት ማቋረጥ ቢፈልግ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦

እናንተ ራሳችሁ ለትምህርት ያላችሁን አመለካከት መርምሩ። በትምህርት ቤት ያሳለፋችሁት ጊዜ እንደባከነ ይሰማችሁ ነበር? ከትምህርት ዓለም የምትገላገሉበትንና ይበልጥ አስፈላጊ ብላችሁ የምታስቡት ግብ ላይ የምትደርሱበትን ጊዜ ትናፍቁ ነበር? ከሆነ እናንተ ስለ ትምህርት ያላችሁ አመለካከት በልጃችሁ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። ይሁንና አንድ ነገር ማስተዋል ይኖርባችኋል፤ ልጆቻችሁ ሁለገብ የሆነ ትምህርት ማግኘታቸው ወደፊት ትልቅ ሰው ሲሆኑ ግቦቻቸው ላይ ለመድረስ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይኸውም “ጥበብንና አርቆ ማስተዋልን” እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 3:21 የ1980 ትርጉም

የሚያስፈልጉትን ነገሮች አቅርቡለት። አንዳንድ ልጆች ውጤታቸው ዝቅተኛ የሚሆነው፣ እንዴት ማጥናት እንዳለባቸው ስለማያውቁ ወይም ደግሞ ለማጥናት አመቺ የሆነ ሁኔታ ስለማያገኙ ብቻ ሊሆን ይችላል። የልጃችሁን የጥናት ቦታ ምቹ ለማድረግ በክፍሉ ውስጥ በቂ ብርሃን እንዲኖርና ለምርምር የሚሆኑ መሣሪያዎች እንዲሟሉ እንዲሁም ጠረጴዛው ያልተዝረከረከ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ልጃችሁ አእምሮውን ለማሠራት እንዲሁም አዳዲስ ሐሳቦችን ለማመንጨት የሚያስችለው ምቹ ቦታ በማዘጋጀት በቀለም ትምህርቱም ሆነ በመንፈሳዊነቱ ረገድ እድገት እንዲያደርግ መርዳት ትችላላችሁ።—ከ1 ጢሞቴዎስ 4:15 ጋር አወዳድር።

የበኩላችሁን አስተዋጽኦ አድርጉ። የልጃችሁን አስተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ ያሉ አማካሪዎችን እንደ ጠላት ሳይሆን አንደ አጋሮቻችሁ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው። ሄዳችሁ አነጋግሯቸው። ስማቸውን እወቁ። ልጃችሁ ስላሉት ግቦችና ስለሚያጋጥሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አነጋግሯቸው። ልጃችሁ ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጣ ከሆነ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ቢያመጣ ጉልበተኞች እንዳያስቸግሩት ይፈራል? ከአስተማሪው ጋር አይስማማ ይሆን? ወይስ የመረጠው የትምህርት ዓይነት ከብዶታል? ሥርዓተ ትምህርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ የሚሄደው የልጆቻችሁን ችሎታ ለማሻሻል እንጂ ከልክ በላይ እንዲጨነቁ ለማድረግ እንዳልሆነ አስታውሱ። ሌላም ልታስቡበት የሚገባ ነገር አለ፦ ልጃችሁ አንድ ያላወቃችሁት እክል ለምሳሌ የማየት ችግር ወይም ትምህርት የመቀበል ችግር ይኖርበት ይሆን?

ልጃችሁን ለማሠልጠን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ባደረጋችሁ መጠን በቀለም ትምህርትም ሆነ በመንፈሳዊ ነገሮች ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን ትረዱታላችሁ።—መዝሙር 127:4, 5

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 19⁠ን ተመልከት

ልጄ ራሱን ችሎ ለመኖር መድረሱን ማወቅ የምችለው እንዴት ነው?

በምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሰችው ሴሪና ከቤት ወጥታ ራሷን ችላ መኖር ትፈራለች። ለምን? አንደኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ምንም ነገር በራሴ ገንዘብ እንድገዛ አይፈቅድልኝም። ይህ የእሱ ኃላፊነት እንደሆነ ይነግረኛል። በመሆኑም በራሴ ወጪዎቼን ሸፍኜ መኖር የሚለው ሐሳብ ያስፈራኛል።” የሴሪና አባት እንደዚህ የሚያደርገው ለእሷ መልካም አስቦ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ይሁንና ልጁ ራሷን ችላ መኖር እንድትችል እያሠለጠናት ያለ ይመስላችኋል?—ምሳሌ 31:10, 18, 27

እናንተስ ለልጆቻችሁ ከመጠን በላይ በመሳሳት የምታደርጉት ነገር ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ለሚኖሩበት ጊዜ እንዳይዘጋጁ እያደረጋቸው ይሆን? ይህን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? እስቲ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን አራት ነጥቦች ተመልከቱ፤ እነዚህ ነጥቦች በምዕራፍ 7 ላይ “ዝግጁ ነኝ?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ተጠቅሰው ነበር፤ አሁን ደግሞ ነጥቦቹን ከወላጅ አንጻር እንያቸው።

የገንዘብ አያያዝ፦ በዕድሜ ከፍ ያሉት ልጆቻችሁ ከግብር ጋር የተያያዙ ሕጎችን ለመታዘዝ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ? (ሮም 13:7) በዱቤ ከመግዛት ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሥልጠና አግኝተዋል? (ምሳሌ 22:7) በጀት በማውጣት ገቢያቸውን አመጣጥነው መኖር ይችላሉ? (ሉቃስ 14:28-30) ሠርተው ባገኙት ገንዘብ አንድ ነገር መግዛት የሚያስገኘውን ደስታ ቀምሰው ያውቃሉ? ጊዜያቸውንና ጥሪታቸውን ተጠቅመው ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን የላቀ ደስታስ አጣጥመው ያውቃሉ?—ሐዋርያት ሥራ 20:35

የቤት አያያዝ፦ ሴቶች እና ወንዶች ልጆቻችሁ ምግብ መሥራት ይችላሉ? ልብስ ማጠብና መተኮስ አስተምራችኋቸዋል? ልጆቻችሁ መኪና የሚነዱ ከሆነ ፊዩዝ፣ ዘይት ወይም ጎማ እንደ መቀየር ያሉ ቀላል ሥራዎችን ማከናወን ይችላሉ?

ማኅበራዊ ሕይወት፦ በዕድሜ ከፍ ባሉ ልጆቻችሁ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ሁልጊዜ ጣልቃ ገብታችሁ ትዳኟቸዋላችሁ? ወይስ ልጆቻችሁ ራሳቸው ተነጋግረው ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱትና የደረሱበትን ውሳኔ እንዲነግሯችሁ አሠልጥናችኋቸዋል?—ማቴዎስ 5:23-25

መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች፦ ለልጆቻችሁ ምን ማመን እንዳለባቸው ትነግሯቸዋላችሁ? ወይስ ማስረጃ በማቅረብ ራሳቸው እንዲያምኑበት ታደርጋላችሁ? (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ልጆቹ ለሚያነሷቸው ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጥያቄዎች ሁልጊዜ እናንተ መልስ ከመስጠት ይልቅ “ልባም” እንዲሆኑ ወይም የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ እያሠለጠናችኋቸው ነው? (ምሳሌ 1:4) በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ረገድ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ እንደምትሆኑ ይሰማችኋል? ካልሆነ በዚህ ረገድ ከእናንተ የተሻለ ልማድ እንዲያዳብሩ ታበረታቷቸዋላችሁ? *

ከላይ በተዘረዘሩት ነጥቦች ረገድ ልጆቻችሁን ማሠልጠን ጊዜና ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ ወግ ደርሷቸው ራሳቸውን ችለው ለመኖር ከእናንተ የሚለዩበት ጊዜ ሲመጣ፣ እነሱን ለማሠልጠን ያደረጋችሁት ጥረት ከንቱ እንዳልሆነ ትመለከታላችሁ።

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት

 የፆታ ግንኙነት እና የፍቅር ጓደኝነት

ከልጄ ጋር ስለ ፆታ ጉዳዮች ማውራት ይኖርብኛል?

በዛሬው ጊዜ ልጆች ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰሙት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ” እና ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” እንዲሁም “አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” እንደሚሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3, 4) ብዙዎች የፍቅር ስሜት ወይም ግንኙነት ሳይኖራቸው ካገኙት ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆኑ የዚህን ትንቢት እውነተኝነት ከሚያረጋግጡት በርካታ ምልክቶች አንዱ ነው።

ዛሬ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እናንተ ወጣት እያላችሁ ከነበረው በጣም የተለየ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያሉት ችግሮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን በእናንተ ዘመን ከነበሩት ጋር ይመሳሰላሉ። ስለዚህ ልጆቻችሁ የሚደርሱባቸውን መጥፎ ተጽዕኖዎች በማሰብ ልትሸበሩ ወይም ከመጠን በላይ ልትሰጉ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ከዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች የሰጠውን ማሳሰቢያ እንዲከተሉ ልጆቻችሁን ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ፤ ጳውሎስ “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ” ብሎ ነበር። (ኤፌሶን 6:11) በአሁኑ ጊዜ መጥፎ ተጽዕኖዎች ቢኖሩም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚጥሩ ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች አሉ፤ እነዚህ ወጣቶች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። እናንተስ ልጆቻችሁ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ፣ በዚህ መጽሐፍ ክፍል 4 እንዲሁም በጥራዝ 2 ክፍል 1 እና 7 ላይ ከሚገኙት ምዕራፎች የተወሰኑትን መርጣችሁ ከልጆቻችሁ ጋር መወያየት ነው። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ልጃችሁ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርጉ ጥቅሶች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ጥቅሶች፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ በመቁረጣቸው ምክንያት በረከት ስላገኙ ሰዎች የሚገልጹ ወይም የአምላክን ሕግጋት ቸል በማለታቸው የተነሳ አስከፊ ነገሮች ስለደረሱባቸው ሰዎች የሚናገሩ እውነተኛ ታሪኮችን የያዙ ናቸው። ሌሎቹ ጥቅሶች ደግሞ እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ከአምላክ ሕግጋት ጋር ተስማምታችሁ መኖራችሁ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ የሚያስችሏቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዘዋል። ታዲያ በእነዚህ ምዕራፎች ላይ በቅርቡ ለመወያየት ለምን ፕሮግራም አታወጡም?

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 23, 25, 26 እና 32⁠ን እንዲሁም ጥራዝ 2 ምዕራፍ 4-6, 28 እና 29⁠ን ተመልከት

ልጄ የፍቅር ጓደኝነት እንዲጀምር ልፍቀድለት?

ይዋል ይደር እንጂ ልጆቻችሁ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርቱ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ፊሊፕ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ሴቶቹ መጥተው የሚጠይቁኝ ምንም የተለየ ነገር አድርጌ አይደለም! እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲያቀርቡልኝ ‘እሺ አሁን ምንድን ነው የምላቸው?’ ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ቆንጆዎች ስለሆኑ እምቢ ማለት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ!”

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልትወስዱት የምትችሉት ከሁሉ የተሻለው እርምጃ የፍቅር ጓደኛ መያዝን በተመለከተ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገር ነው፤ በጥራዝ 2 ምዕራፍ 1 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ለምን አትወያዩም? ልጆቻችሁ በትምህርት ቤትም ሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ጣሩ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ውይይት ‘ቤታችሁ ተቀምጣችሁ ወይም በመንገድ ስትሄዱ’ አሊያም በሌላ አጋጣሚ ልታደርጉት ትችላላችሁ። (ዘዳግም 6:6, 7) ጉዳዩን ያነሳችሁት የትም ይሁን የት ‘ለመስማት የፈጠናችሁና ለመናገር የዘገያችሁ’ መሆን እንዳለባችሁ አትዘንጉ።—ያዕቆብ 1:19

ልጃችሁ ፍቅር እንደያዘው ቢነግራችሁ አትደናገጡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት “አባቴ የወንድ ጓደኛ እንዳለኝ ሲያውቅ በጣም ተበሳጨ!” ስትል ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ለማግባት ዝግጁ መሆኔን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንድፈራ ለማድረግ ሞከረ፤ እንዲህ ዓይነቱ ምላሽ ግን ወጣቶች ወላጆቻቸው እንደተሳሳቱ ለማሳየት ሲሉ ግንኙነታቸውን እንዲገፉበት ያነሳሳቸዋል!”

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ የፍቅር ጓደኝነት ስለ መመሥረት ጨርሶ እንዲነሳ እንደማትፈልጉ ከተሰማቸው የከፋ እርምጃ ሊወስዱ ይኸውም በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ሊጀምሩ ይችላሉ። አንዲት ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የወላጆች መቆጣት የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ልጆቹ ስለ ግንኙነታቸው ይበልጥ ድብቅ እንዲሆኑ ማድረግ ብቻ ነው። ግንኙነታቸውን አያቆሙም። እንዲያውም ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ይጀምራሉ።”

የተሻለ ውጤት ማግኘት የምትችሉት በግልጽ በመነጋገር ነው። ብሪታኒ የተባለች የ20 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የፍቅር ጓደኝነት መመሥረትን በተመለከተ ከወላጆቼ ጋር ሁልጊዜ በግልጽ እንነጋገራለን። የወደድኩት ሰው ካለ ማወቅ ይፈልጋሉ፤ ይህም ጥሩ እንደሆነ ይሰማኛል! አባቴ የወደድኩትን ልጅ ያናግረዋል። ከዚያም ወላጆቼ ያሳሰባቸው ነገር ካለ ያሳውቁኛል። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንኳ ሳያስፈልገኝ ያ ሰው ቢቀርብኝ እንደሚሻል እወስናለሁ።”

ወላጆች በጥራዝ 2 ምዕራፍ 2 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ካነበቡ በኋላ ግን ‘ልጄ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምሮ ይሆን?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። አንዳንዶች ከተቃራኒ ፆታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ለመመሥረት የሚፈተኑት ለምን እንደሆነ በርካታ ወጣቶች የሰጡት ሐሳብ ከዚህ በታች ቀርቧል፤ አስተያየታቸውን ካነበባችሁ በኋላ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ቆም ብላችሁ አስቡ።

“አንዳንድ ልጆች ቤት ውስጥ ስሜታቸውን የሚረዳላቸውና የሚደግፋቸው ሰው እንደሌለ ስለሚሰማቸው ይህን ለማግኘት ሲሉ የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ይወስናሉ።”—ዌንዲ

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን የልጆቻችሁን ስሜት መረዳትና በሚፈልጓችሁ ጊዜ ከጎናቸው መሆን የምትችሉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ልታደርጉት የምትችሉት ማሻሻያ አለ? ካለስ ምን?

“የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከሌላ አገር የመጣ አንድ ተማሪ የሴት ጓደኛው እንድሆን ጠየቀኝ። እኔም ተስማማሁ። እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል የሚያደርግ ጓደኛ ማግኘቱ ደስ የሚል ነገር እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።”—ዳያን

ዳያን የእናንተ ልጅ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርጉ ነበር?

“ሞባይል ስልክ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ወላጆች ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቁት ነገር አይኖርም!”—አኔት

ልጆቻችሁ ሞባይል ስልካቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳይጠቀሙበት ምን ጥንቃቄ ማድረግ ትችላላችሁ?

“ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከማን ጋር ምን እያደረጉ እንደሆነ በቅርበት ካልተከታተሉ ልጆቹ በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት ቀላል ይሆንላቸዋል።”—ቶማስ

የልጃችሁን ነፃነት ሳትጋፉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በቅርበት መከታተል የምትችሉባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?

“ልጆች ብዙውን ጊዜ ቤት ውስጥ ብቻቸውን ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የፈለጉበት እንዲሄዱ ወላጆቻቸው ይፈቅዱላቸዋል።”—ኒኮላስ

እስቲ ስለ ልጃችሁ የቅርብ ጓደኛ አስቡ። አብረው ሲሆኑ ምን እንደሚሠሩ ታውቃላችሁ?

“ወላጆች ከልክ በላይ ጥብቅ ከሆኑ ልጆች በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ሊመሠርቱ ይችላሉ።”—ፖል

የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ “ምክንያታዊ” ለመሆን ጥረት ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?—ፊልጵስዩስ 4:5

“በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለሁ ለራሴ ጥሩ ግምት ስላልነበረኝ የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት እጓጓ ነበር። ስለዚህ ጎረቤት ጉባኤ ከሚገኝ አንድ ወጣት ጋር ኢ-ሜይል መጻጻፍ ጀመርኩና ከእሱ ጋር ፍቅር ያዘኝ። ልጁ የተለየሁ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኝ ነበር።”—ሊንዳ

የሊንዳ ወላጆች ልጃቸው ስለ ራሷ ጥሩ እንዲሰማት ለመርዳት ምን የተሻሉ ዘዴዎችን መጠቀም የሚችሉ ይመስላችኋል?

በዚህ ክፍል ውስጥም ሆነ በጥራዝ 2 ምዕራፍ 2 ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ከልጃችሁ ጋር ለመወያየት ለምን አትጠቀሙባቸውም? የልብን አውጥቶ በግልጽ መነጋገር ልጆቻችሁ የሚደብቋችሁ ነገር እንዳይኖር የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ነው።—ምሳሌ 20:5

ጥራዝ 2 ምዕራፍ 1-3⁠ን ተመልከት

 ስሜት

ልጄ ሕይወቱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ባውቅ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ወጣቶች ሕይወታቸውን ማጥፋታቸው በጣም የተለመደ መሆኑ የሚያሳዝን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከ15 እስከ 25 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሞት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ሦስተኛውን ደረጃ የያዘው የራስን ሕይወት ማጥፋት ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ከ10 እስከ 14 ዓመት ከሆናቸው ወጣቶች መካከል ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ራሳቸውን ያጠፉት ወጣቶች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። በተለይ ደግሞ በአእምሮ ሕመም የሚሠቃዩ፣ ሕይወቱን ያጠፋ የቤተሰብ አባል ያላቸው እንዲሁም ራሳቸውን የመግደል ሙከራ አድርገው የሚያውቁ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት እርምጃ የመውሰድ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው። አንድ ወጣት ሕይወቱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

● ከቤተሰቡም ሆነ ከጓደኞቹ መራቅ

● በአመጋገብና በእንቅልፍ ልማዱ ረገድ ለውጥ ማሳየት

● በአንድ ወቅት ይወዳቸው በነበሩት ነገሮች አለመደሰት

● ጉልህ የሆነ የባሕርይ ለውጥ ማሳየት

● ዕፅ መውሰድ ወይም የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት

● በጣም የሚወዳቸውን ንብረቶች ለሌሎች መስጠት

● ስለ ሞት ማውራት ወይም ከዚያ ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ

ወላጆች እነዚህን ምልክቶች ችላ ማለታቸው ትልቅ ስህተት ነው። የሚያሰጋ ሁኔታ እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች በሙሉ በቁም ነገር መታየት ይኖርባቸዋል። ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች ቢታዩበት ‘ዕድሜው ነው’ ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ልጃችሁ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ወይም በሌላ ዓይነት የአእምሮ ሕመም የሚሠቃይ ከሆነ እርዳታ መጠየቅ ሊያሳፍራችሁ አይገባም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጃችሁ ራሱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ከጠረጠራችሁ ስለ ጉዳዩ አነጋግሩት። ራስን ስለ ማጥፋት ማውራት ልጁ ድርጊቱን እንዲፈጽም ያነሳሳዋል የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው። እንዲያውም ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሱ በርካታ ወጣቶች የሚሰማቸውን መናገር ቀላል ይሆንላቸዋል። ስለዚህ ልጃችሁ ራሱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ከገለጸላችሁ ይህን ስለሚያደርግበት መንገድ ያሰበው ነገር ካለ ጠይቁት፤ ጉዳዩን ምን ያህል በዝርዝር እንዳሰበበት ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ራሱን ማጥፋት ስለሚችልበት መንገድ ዝርዝር ጉዳዮችን ጭምር በደንብ እንዳሰበባቸው ከተገነዘባችሁ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባችሁ።

ልጃችሁ ያጋጠመው የመንፈስ ጭንቀት ያለምንም እርዳታ ከጊዜ በኋላ እንደሚለቀው በማሰብ አትዘናጉ። ጭንቀቱ እየለቀቀው እንደሆነ ቢሰማችሁ እንኳ ችግሩ ለዘለቄታው መፍትሔ አግኝቷል ብላችሁ አታስቡ። እንዲያውም በልጁ ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ መታየቱ በጣም የሚያሰጋ ሊሆን ይችላል። ለምን? እንዲህ ያለ ችግር ያለበት ልጅ በከፍተኛ ጭንቀት በተዋጠበት ወቅት ኃይሉ በጣም ስለሚሟጠጥ ራሱን የማጥፋት ሐሳብ ቢኖረውም ድርጊቱን ለመፈጸም አቅም ያጣ ይሆናል። ጭንቀቱ ቀለል ሲልለትና ኃይሉ ሲታደስ ግን ራሱን ለማጥፋት አቅም ሊያገኝ ይችላል።

አንዳንድ ወጣቶች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ መሆኑ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ወላጆችም ሆኑ ሌሎች አዋቂዎች በልጆቹ ላይ የሚታዩትን ምልክቶች በንቃት በመከታተልና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ማጽናናት’ እንዲሁም ለወጣቶች እንደ መሸሸጊያ መሆን ይችላሉ።—1 ተሰሎንቄ 5:14

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 13 እና 14⁠ን እንዲሁም ጥራዝ 2 ምዕራፍ 26⁠ን ተመልከት

ሐዘኔን ከልጆቼ መደበቅ ይኖርብኛል?

የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት መሪር ሐዘን ያስከትላል። ይህ ሁኔታ የገጠማችሁ ደግሞ ልጃችሁ የእናንተን እርዳታ በሚፈልግበት ጊዜ ይኸውም በጉርምስና ዕድሜ ላይ እያለ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የራሳችሁን ስሜት ችላ ሳትሉ ልጃችሁ ሐዘኑን እንዲቋቋም ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦

ስሜታችሁን ለመደበቅ አትሞክሩ። ልጃችሁ እናንተን በመመልከት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ነገር ተምሯል። ሐዘኑን እንዴት መቋቋም እንደሚችል የሚማረውም እናንተን በማየት ነው። በመሆኑም ለልጃችሁ ስትሉ ጠንካራ መሆን እንዳለባችሁ በማሰብ ሐዘናችሁን ለመደበቅ አትሞክሩ። ስሜታችሁን ለመደበቅ የምትሞክሩ ከሆነ ልጃችሁም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ እያስተማራችሁት ነው። ከዚህ በተቃራኒ ሐዘናችሁን አውጥታችሁ የምትገልጹ ከሆነ ልጃችሁም ስሜቱን አፍኖ ከመያዝ ይልቅ ማውጣቱ የተሻለ መሆኑን እንዲሁም ማዘኑ አንዳንድ ጊዜም መበሳጨቱ የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ይገነዘባል።

ልጃችሁ በውስጡ ያለውን አውጥቶ እንዲናገር አበረታቱት። በጉርምስና ዕድሜ የሚገኘው ልጃችሁ እንደጎተጎታችሁት ሳይሰማው የልቡን አውጥቶ እንዲያወራ ለማበረታታት ሞክሩ። ለማውራት ፈቃደኛ ካልሆነ ደግሞ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ላይ ልትወያዩ ትችላላችሁ። በተጨማሪም በሞት ከተለያችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስላሳለፋችሁት አስደሳች ጊዜ ንገሩት። እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁን አጥታችሁ መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንባችሁ በግልጽ ንገሩት። ስሜታችሁን አውጥታችሁ ስትገልጹ መስማቱ እሱም እንዲህ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲማር ይረዳዋል።

እናንተ ራሳችሁ እርዳታ እንደሚያስፈልጋችሁ አትዘንጉ። በሐዘን በተደቆሳችሁበት በዚህ ወቅት ለልጃችሁ ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠት እንደምትፈልጉ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እናንተም የምትወዱትን የትዳር ጓደኛችሁን በሞት በማጣታችሁ በጣም እንደተጎዳችሁ አትዘንጉ። በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ስሜታዊና አካላዊ ጥንካሬ ላይኖራችሁ እንዲሁም አእምሯችሁ ሊዝል ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ስለሆነም አዋቂ የሆኑ የቤተሰባችሁ አባላት ወይም የጎለመሱ ጓደኞቻችሁ እንዲረዷችሁ መጠየቅ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። እርዳታ መጠየቅ የብስለት ምልክት ነው። ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል።

ከሁሉ የተሻለ እርዳታ ማግኘት የምትችሉት ከይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ‘እኔ ይሖዋ አምላክህ “አትፍራ፤ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ’ በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ኢሳይያስ 41:13

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 16⁠ን ተመልከት

ልጄ በአመጋገብ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት እንድታዳብር ልረዳት የምችለው እንዴት ነው?

ልጃችሁ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ካለባት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? * በመጀመሪያ፣ ልጃችሁ ለዚህ ችግር የተጋለጠችው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርጉ።

ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነና ከራሳቸው ፍጽምናን ይኸውም ጨርሶ ሊደርሱበት የማይችሉትን ነገር እንደሚጠብቁ ተስተውሏል። እናንተም ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራት ላለማድረግ ተጠንቀቁ። ከዚህ ይልቅ ልጃችሁ ለራሷ ጥሩ ግምት እንዲኖራት እርዷት።—1 ተሰሎንቄ 5:11

ከዚህም በላይ እናንተ ራሳችሁ ስለ አመጋገብና ስለ ውፍረት ያላችሁን አመለካከት በሚገባ መርምሩ። እነዚህ ነገሮች በጣም እንደሚያሳስቧችሁ የሚጠቁም ነገር ሳይታወቃችሁ ተናግራችሁ ወይም አድርጋችሁ ይሆን? ወጣቶች የቁመናቸው ነገር በጣም እንደሚያሳስባቸው አትዘንጉ። ልጃችሁ ወፍራም መሆኗን ወይም የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትሆን ቁመቷና ክብደቷ በአንድ ጊዜ መጨመሩን በተመለከተ በቀልድ መልክም እንኳ የምትሰነዝሩት ሐሳብ በልጃችሁ አእምሮ ላይ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርና ስለ ራሷ መጥፎ እንዲሰማት ሊያደርግ ይችላል።

በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰባችሁበት በኋላ ከልጃችሁ ጋር በግልጽ ተነጋገሩ። ይህን ለማድረግ እንዲረዳችሁ የሚከተሉትን ነጥቦች በተግባር ለማዋል ሞክሩ፦

● ምን እንደምትሉና መቼ መናገር እንደሚኖርባችሁ በጥንቃቄ አስቡ።

● ያሳሰባችሁ ጉዳይ ምን እንደሆነና እሷን ለመርዳት እንደምትፈልጉ በግልጽ ንገሯት።

● መጀመሪያ ላይ ችግር እንዳለባት ለመቀበል ብታንገራግር አይግረማችሁ።

● በትዕግሥት አዳምጧት።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጃችሁ ያለባትን የአመጋገብ ችግር ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት አግዟት። ችግሯን እንደ ቤተሰቡ ችግር አድርጋችሁ በመቁጠር በጋራ ተባብራችሁ ሥሩ!

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 10⁠ን እንዲሁም ጥራዝ 2 ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት

  መንፈሳዊነት

ልጆቼ ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲገቡም ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ላስተምራቸው የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጢሞቴዎስ ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ መንፈሳዊ ሥልጠና እንደተሰጠው ይናገራል፤ እናንተም ብትሆኑ ልጆቻችሁን በዚሁ መንገድ አሠልጥናችኋቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ልጆቻችሁ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ግን የምታስተምሩበትን መንገድ ከሚያጋጥሟችሁ አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ማስማማት ያስፈልጋችኋል። ልጆቻችሁ እያደጉ ሲመጡ ትንሽ እያሉ ሊረዷቸው የማይችሉ ከበድ ያሉና ማመዛዘን የሚጠይቁ ነገሮችን መረዳት ይጀምራሉ። በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዚህ ወቅት ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ እንዲጠቀሙ ልታግዟቸው ይገባል።—ሮም 12:1

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጢሞቴዎስ ‘ስለተማራቸውና ሰዎች አሳምነውት ስለተቀበላቸው’ ነገሮች ጠቅሷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14) በተመሳሳይም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የሚያውቋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ‘አምነው እንዲቀበሉ’ መርዳት ያስፈልጋችሁ ይሆናል። የልጆቻችሁን ልብ ለመንካት ከፈለጋችሁ ሊያደርጓቸው ወይም ሊያምኑባቸው ስለሚገቡ ነገሮች በመግለጽ ብቻ መወሰን የለባችሁም። ልጆቻችሁ እነዚህን ነገሮች ራሳቸው መርምረው ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። እንዲህ እንዲያደርጉ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? እንደሚከተሉት ስላሉት ጥያቄዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ እንዲሁም አመለካከታቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው።

● አምላክ እንዳለ የማምነው ለምንድን ነው?—ሮም 1:20

● ወላጆቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያስተምሩኝ ነገር እውነት መሆኑን እንዴት አውቃለሁ?—የሐዋርያት ሥራ 17:11

● የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተሌ እንደሚጠቅመኝ እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?—ኢሳይያስ 48:17, 18

● የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ እንዴት አውቃለሁ?—ኢያሱ 23:14

● ዓለም የሚያቀርበው ማንኛውም ነገር “ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት” ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር እንደማይችል የማምነው ለምንድን ነው?—ፊልጵስዩስ 3:8

● የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሕይወቴ ምን እንዳደርግ ሊያነሳሳኝ ይገባል?—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15፤ ገላትያ 2:20

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ላያውቁት እንደሚችሉ በመፍራት በጥያቄዎቹ ላይ እንዲያስቡባቸው ከማድረግ ወደኋላ ትሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ በመኪና ውስጥ ያለው የነዳጅ መጠን ጠቋሚ መሣሪያ ነዳጁ ባዶ መሆኑን እያመለከተ እንዳይሆን በመፍራት መሣሪያውን ከማየት ወደኋላ እንደ ማለት ይቆጠራል። መኪናው ነዳጅ ከሌለው መሙላት እንድትችሉ የነዳጁን መጠን አስቀድማችሁ ማወቃችሁ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም ልጆቻችሁ ከእምነታቸው ጋር ስለተያያዙ ጥያቄዎች ምርምር እንዲያደርጉና እነዚህን ነገሮች ‘አምነው እንዲቀበሉ’ ለመርዳት የተሻለው ጊዜ ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ከቤት ከመውጣታቸው በፊት ነው። *

ልጆቻችሁ “በዚህ ነገር የማምነው ለምንድን ነው?” ብለው መጠየቃቸው ስህተት እንዳልሆነ አስታውሱ። የ22 ዓመት ወጣት የሆነችው ዳያን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለች እንዲህ አድርጋ እንደነበር ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስለማምንባቸው ነገሮች መልስ መስጠት እንደማልችል እንዲሰማኝ አልፈለግሁም። የማምንባቸውን ነገሮች በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች ግልጽ እና በማስረጃ የተደገፈ መልስ ማግኘቴ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ እንድደሰት አድርጎኛል! አንድ ነገር የማላደርገው ለምን እንደሆነ ስጠየቅ ‘ሃይማኖቴ ስለማይፈቅድ ነው’ ከማለት ይልቅ ‘ትክክል እንዳልሆነ ስለሚሰማኝ ነው’ ብዬ እመልሳለሁ። በሌላ አባባል ሕይወቴን በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሠረት የምመራው ስላመንኩበት ነው።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ አንድ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ የማሰብ ችሎታቸውን ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካሉት መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነገር እንዲያደርጉ ለመርዳት፣ እንደ ወላጅ ሆነው እንዲያስቡ ጠይቋቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ በአንድ ፓርቲ ላይ ለመገኘት ፈቃድ ጠየቀቻችሁ እንበል። በዚህ ፓርቲ ላይ መገኘቷ ተገቢ እንደማይሆን ታውቃላችሁ፤ እሷም ብትሆን ይህን ሳትገነዘብ አትቀርም። ለልጃችሁ ወደ ፓርቲው መሄድ እንደማይፈቀድላት ብቻ ከመግለጽ ይልቅ እንዲህ ልትሏት ትችላላችሁ፦ ‘እስቲ ራስሽን በእኛ ቦታ አስቀምጪና ስለ ፓርቲው አስቢ። ከዚያም ስለ ጉዳዩ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርጊና (ምናልባትም የዚህን መጽሐፍ ምዕራፍ 37 እና ጥራዝ 2 ምዕራፍ 32 ማየት ይቻላል) ነገ እንነጋገርበታለን። ነገ፣ እኔ በአንቺ ቦታ ሆኜ ፓርቲ መሄድ እንደምፈልግ እነግርሻለሁ፤ አንቺ ደግሞ እንደ ወላጅ ሆነሽ በዝግጅቱ ላይ መገኘቴ ጥሩ መሆን አለመሆኑን ታስረጂኛለሽ።’

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 38⁠ን እንዲሁም ጥራዝ 2 ምዕራፍ 34-36⁠ን ተመልከት

ልጃችን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንደ ድሮው አያስደስተውም። ምን ብናደርግ ይሻላል?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልጃችሁ እንዲህ መሆኑ የእናንተን እምነት መከተል እንደማይፈልግ የሚያሳይ እንደሆነ ለመደምደም አትቸኩሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ፍላጎት እንዲያጣ ያደረገው ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ፦

● እኩዮቹ ተጽዕኖ ያደርጉበት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በመከተሉ ከሌሎች የተለየ መሆን ያስፈራው ይሆናል

● ሌሎች ወጣቶች (ምናልባትም ወንድሞቹና እህቶቹ) ከእሱ የበለጠ መንፈሳዊ ሰዎች እንደሆኑና እሱ ግን ፈጽሞ እዚያ ደረጃ መድረስ እንደማይችል ሊሰማው ይችላል

● ጓደኞች ስለሌሉት ብቸኝነት ይሰማው ይሆናል፤ ወይም ከእምነት ባልንጀሮቹ መካከል ጓደኛ ማግኘት አልቻለም

● ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ወጣቶች ሁለት ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩ ተመልክቶ ይሆናል

● የራሱ ማንነት ያለው ሰው መሆን እንዳለበት ስለሚያስብ እናንተ ከፍ አድርጋችሁ የምታዩዋቸው ነገሮች ትክክል ስለ መሆናቸው ጥያቄ ማንሳት እንዳለበት ይሰማው ይሆናል

● አብረውት የሚማሩ ልጆች መጥፎ ነገሮችን ቢፈጽሙም ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ሊሰማው ይችላል

● አማኝ ያልሆነ ወላጁን ለማስደሰት እየጣረ ሊሆን ይችላል

እንደነዚህ ያሉት ጉዳዮች ልጃችሁ እምነታችሁ ትክክለኛ መሆኑን እንደተጠራጠረ የሚያሳዩ እንዳልሆኑ ልብ ልትሉ ይገባል። ከዚህ ይልቅ ልጃችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ያጣው ይህን እምነት መከተል ተፈታታኝ እንዲሆንበት የሚያደርጉ ሁኔታዎች ስለገጠሙት ነው። ታዲያ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

አቋማችሁን ሳታላሉ ማስተካከያዎች አድርጉ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዲያጣ ያደረገው ምን እንደሆነ ለመረዳት ሞክሩ፤ እንዲሁም በመንፈሳዊ እያደገ እንዲሄድ የሚረዳው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርጉ። (ምሳሌ 16:20) ለምሳሌ ያህል፣ በጥራዝ 2 ገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለውን ሣጥን በመጠቀም ልጃችሁ አብረውት ለሚማሩት ልጆች አቋሙን መግለጽ እንዳይፈራ ልትረዱት ትችላላችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ልጃችሁ ብቸኝነት የሚሰማው ከሆነ ጥሩ ጓደኞች እንዲያገኝ ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባችሁ ይሆናል።

ምሳሌ ከሚሆን አዋቂ ሰው ጋር እንዲቀራረብ አድርጉ። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች የቤተሰባቸው አባል ካልሆነ አዋቂ ሰው ማበረታቻ ማግኘታቸው ይጠቅማቸዋል። መንፈሳዊ አመለካከት ያለውና በጉርምስና ዕድሜ ላይ ላለው ልጃችሁ ጥሩ ወዳጅ ሊሆን የሚችል የምታውቁት ሰው አለ? ይህ ሰው ከልጃችሁ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ ለምን አታደርጉም? እንዲህ የምታደርጉት ኃላፊነታችሁን በሌላ ሰው ላይ ለመጫን አይደለም። የጢሞቴዎስን ምሳሌ አስታውሱ። ጢሞቴዎስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው አርዓያ ብዙ ነገር ተምሯል፤ ጳውሎስም ጢሞቴዎስ አብሮት በመሆኑ በጣም ተጠቅሟል።—ፊልጵስዩስ 2:20, 22

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ከእናንተ ጋር እስከኖረ ድረስ በምታደርጓቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈል የመጠየቅ መብት አላችሁ። ይሁን እንጂ ግባችሁ፣ ልጃችሁ ለአምላክ ፍቅር እንዲያዳብር መርዳት እንጂ እንዲሁ በዘልማድ ነገሮችን እንዲያከናውን ማድረግ አይደለም። ልጃችሁ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዲከተል ለመርዳት እናንተ ራሳችሁ ጥሩ አርዓያ ልትሆኑለት ይገባል። ከእሱ በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ። ምሳሌ ከሚሆን አዋቂ ሰው እንዲሁም ጥሩ ጓደኛ ሊሆኑት ከሚችሉ ሰዎች ጋር እንዲቀራረብ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ልክ እንደ መዝሙራዊው ይሖዋ ለእሱም ‘ዐለቱ፣ መጠጊያውና ታዳጊው’ እንደሆነ እንዲሰማው ልትረዱት ትችላላችሁ።—መዝሙር 18:2

ጥራዝ 1 ምዕራፍ 39⁠ን እንዲሁም ጥራዝ 2 ምዕራፍ 37 እና 38⁠ን ተመልከት

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.23 በሌላ በኩል ደግሞ ልጃችሁ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት አንድ ነገር እንዲያደርግ ለማነሳሳት አትሞክሩ።

^ አን.64 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች የመልክና የቁመናቸው ነገር በጣም ስለሚያሳስባቸው የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚጠቁም ሐሳብ ላለመሰንዘር ተጠንቀቁ።

^ አን.113  ከገጽ 315-318 ተመልከቱ።

^ አን.168 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በአንስታይ ፆታ ተጠቅመናል። ይሁንና የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.188 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች አምላክ መኖሩን ራሳቸው መርምረው ማረጋገጥ እንዲችሉ ለመርዳት በጥራዝ 2 ምዕራፍ 36 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች መጠቀም ትችላላችሁ።