በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታዲያ ምን ልልበስ?

ታዲያ ምን ልልበስ?

ምዕራፍ 11

ታዲያ ምን ልልበስ?

ሄዘር ከቤት ወጣ ለማለት ተዘጋጅታለች፤ ወላጆቿ ምን እንደለበሰች ሲመለከቱ ዓይናቸውን ማመን አቃታቸው።

አባቷ በድንጋጤ “እንዴ! እንዲህ ለብሰሽ ነው የምትሄጂው?” አላት።

ሄዘር በጥያቄው በመገረም “ምናለበት? የምሄደው’ኮ ከጓደኞቼ ጋር ዘና ለማለት ነው” ብላ መለሰች።

እናቷ “እንዲህ ለብሰሽማ አትሄጂም!” አለቻት።

“እንዴ እማዬ! ልጆቹ ሁሉ እኮ እንዲህ ነው የሚለብሱት” በማለት ሄዘር ተነጫነጨች። “ደግሞም ልብሱ ‘ይናገራል!’”

“እኛ ግን ልብሱ ‘የሚናገረውን’ ነገር አልወደድነውም!” አለ አባቷ ኮስተር ብሎ። ከዚያም “በይ የኔ እመቤት፣ ሂጂና ሌላ ልብስ ቀይሪ። አለዚያ እንደዚህ ለብሰሽ ከዚህ ንቅንቅ አትያትም!” አላት።

ከልብስ ጋር በተያያዘ በወላጆችና በልጆች መካከል ጭቅጭቅ መፈጠሩ ያለ ነገር ነው። ወላጆችሽ በአንቺ ዕድሜ እያሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወላጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ተጋጭተው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በወቅቱ አንቺ ዛሬ እንደሚሰማሽ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል! አሁን ግን እነሱ በተራቸው ወላጅ ሲሆኑ የአለባበስ ጉዳይ በመካከላችሁ በተደጋጋሚ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ልጅ፦ ይመቻል።

ወላጅ፦ የተዝረከረከ ነው።

ልጅ፦ በጣም ያምራል!

ወላጅ፦ ሰውነት ያጋልጣል።

ልጅ፦ ዋጋው ርካሽ ነው።

ወላጅ፦ ታዲያ ቢረክስ ምን ይገርማል? ብጣቂ ጨርቅ እኮ ነው!

እንዲህ ዓይነቱን ንትርክ ማርገብ ይቻል ይሆን? አዎ፣ ይቻላል! የ23 ዓመቷ ሜጋን ቁልፉ ምን እንደሆነ ስትናገር “መጨቃጨቅ ሳያስፈልግ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል” ብላለች። ‘ስምምነት?’ ትዪ ይሆናል። ከወላጆችሽ ጋር ለመስማማት ስትዪ እንደ እናቶች መልበስ አለብሽ ማለት ነው? እንደ እሱ ማለት አይደለም! መስማማት ሲባል አንቺና ወላጆችሽ የሚሰማችሁን ተነጋግራችሁ ሁላችሁንም ሊያግባቡ የሚችሉ ሌሎች አማራጮች ትፈልጋላችሁ ማለት ነው። እንዲህ ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል?

1. እኩዮችሽም እንኳ የሚወዱት ዓይነት ጥሩ አለባበስ ይኖርሻል።

2. አለባበስሽ ወላጆችሽን የሚያስከፋ አይሆንም።

3. ወላጆችሽ በዚህ ረገድ እምነት የሚጣልብሽ እንደሆንሽ ሲያዩ በሌሎች ጉዳዮችም ነፃነት ሊሰጡሽ ይችላሉ።

እስቲ ምን ማድረግ እንዳለብሽ እንመልከት። ሱቅ ውስጥ ወይም ኢንተርኔት ላይ አይተሽው በጣም የወደድሽውን አንድ ልብስ ለማሰብ ሞክሪ። መጀመሪያ ልታደርጊው የሚገባው ነገር . . .

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል

የሚገርመው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አለባበስ ብዙ አይናገርም። እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ በቀጥታ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን በሙሉ ለማንበብ ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ አይወስድብሽም! ምክሮቹ ብዙ ባይሆኑም እንኳ አስተማማኝና ጠቃሚ መመሪያዎች ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፦

● መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሴቶች ራሳቸውን “በልከኝነትና በማስተዋል” እንዲያስውቡ ይመክራል። *1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10

“ልከኝነት” የሚለውን ቃል ስትሰሚ ‘ታዲያ መዘነጥ አልችልም ማለት ነው?’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። እንደዚያ ማለት አይደለም። ልከኛ መሆን ሲባል አለባበስሽ ለራስሽ አክብሮት እንዳለሽና ለሌሎች ስሜት እንደምትጠነቀቂ የሚያሳይ ይሆናል ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:3) ይህን መሥፈርት የሚያሟሉ ብዙ ልብሶች ማግኘት ይቻላል። የ23 ዓመቷ ዳንዬል እንዲህ ትላለች፦ “መምረጡ ተፈታታኝ ቢሆንም ወጣ ያሉ ፋሽኖችን ሳትከተሉ ዘመናዊ አለባበስ ሊኖራችሁ ይችላል።”

● ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ትኩረት መስጠት ያለብሽ ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ ወይም እንደ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ‘ለውስጥ ሰውነት ውበት’ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 3:4

ልከኛ ያልሆነ ልብስ ለጊዜው የሰዎችን ትኩረት ይስብ ይሆናል፤ በአዋቂዎችም ሆነ በእኩዮችሽ ዘንድ ምንጊዜም አክብሮት የሚያተርፍልሽ ግን ውስጣዊ ውበትሽ ነው። ‘ልከኛ አለባበስ በእኩዮቼም ዘንድ ያስከብረኛል?’ ትዪ ይሆናል። አዎ ያስከብርሻል፤ እነሱም እንኳ ቅጥ ያጣ ልብስ ለሚለብስ ሰው ጥሩ ግምት ላይኖራቸው ይችላል። “ሴቶች የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ እርቃን ቀረሽ የሆነ ፋሽን ሲከተሉ ማየት በጣም ይዘገንናል!” በማለት የ16 ዓመቷ ብሪትኒ ተናግራለች። ኬይም በዚህ ትስማማለች። ኬይ፣ ስለ ቀድሞ ጓደኛዋ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የምትለብሳቸው ልብሶች በሙሉ ‘እዩኝ’ የሚል ጽሑፍ የተጻፈባቸው ያህል ነበሩ። የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ስትል ምንም ነገር ከመልበስ ወደኋላ አትልም።”

የወላጆችን ሐሳብ መቀበል

ወላጆችሽ የማይፈቅዱልሽን ልብስ በቦርሳሽ ደብቀሽ ትምህርት ቤት ስትደርሺ መቀየር ምንም አይጠቅምሽም። ከወላጆችሽ መደበቅ እንደምትችዪ በሚሰማሽ ነገሮች ረገድም እንኳ ግልጽና ሐቀኛ መሆንሽ የእነሱን አመኔታ ይበልጥ እንድታተርፊ ይረዳሻል። እንዲያውም አንድን ልብስ ለመልበስ ወይም ለመግዛት ስታስቢ የወላጆችሽን አስተያየት ብትጠይቂ መልካም ነው። (ምሳሌ 15:22)—በገጽ 82 እና 83 ላይ የሚገኘውን “ልብስ ለመምረጥ የሚረዳ መልመጃ” መሥራቱ ጠቃሚ ይሆናል።

ይሁን እንጂ ‘የወላጆቼን ምክር የምጠይቀው ለምንድን ነው? እነሱ እንደሆነ ፋሽን የሆነ ነገር እንድለብስ አይፈልጉም’ ትዪ ይሆናል። እንደዚህ ብለሽ ለመደምደም አትቸኩዪ። እውነት ነው፣ ወላጆችሽ ነገሮችን የሚያዩት ከአንቺ በተለየ መንገድ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ሁልጊዜ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። የ17 ዓመቷ ናታሌን እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ምክር ሲሰጡኝ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም የሚያሳፍረኝ ወይም የአላፊ አግዳሚው መጠቋቆሚያ የሚያደርገኝ ነገር ለብሼ መታየት አልፈልግም።”

ደግሞም ልትቀበዪው የሚገባ አንድ ሐቅ አለ፦ በወላጆችሽ ሥር እስከኖርሽ ድረስ የእነሱን ሥልጣን ማክበር አለብሽ። (ቆላስይስ 3:20) እንደዚያም ቢሆን ግን አንዳችሁ የሌላውን ስሜት መረዳት ከቻላችሁ በመካከላችሁ የሚፈጠረው ጭቅጭቅ በጣም ይቀንሳል። እንዲያውም ውሎ አድሮ በልብስ ጉዳይ መነታረኩ ከናካቴው ሊቀር ይችላል!

ጠቃሚ ምክር፦ አንድን ልብስ ለመልበስ ስታስቢ ልብሱ ልከኛ መሆኑን በደንብ አረጋግጪ። ልከኛ መስሎ የታየሽ ልብስ፣ ስትቀመጪ ወይም አንድ ነገር ለማንሳት ጎንበስ ስትዪ ሰውነትሽን ሊያጋልጥ ይችላል። ከተቻለ ወላጆችሽን አሊያም ሌላ ብስለት ያለው ሰው አማክሪ።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ለራስህ ጥሩ አመለካከት የለህም? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.23 እንዲህ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በቀጥታ የተሰጡት ለሴቶች ቢሆንም መመሪያው ለወንዶችም ይሠራል።

ቁልፍ ጥቅስ

“ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም . . . በልብስ አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ . . . የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።” —1 ጴጥሮስ 3:3, 4

ጠቃሚ ምክር

የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ልብሶች አትልበሺ። እንዲህ ዓይነቱ አለባበስ ትኩረት ለማግኘት በጣም የምትጓጊ እንዲሁም ለሌሎች ስሜት ግድ የሌለሽ ሊያስመስልሽ ይችላል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩን ስለ እኛ የሚኖራቸው አመለካከት ብዙውን ጊዜ በአለባበሳችን ላይ የተመካ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ልብስ መግዛት ስፈልግ ከቤተሰቤ አባላት ወይም ብስለት ካላቸው ጓደኞቼ መካከል የማማክረው ․․․․․

ልብስ ስገዛ የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት አስገባለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ወላጆችና ወጣቶች በአለባበስ ጉዳይ ብዙውን ጊዜ የሚጋጩት ለምንድን ነው?

● ወጣቶች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ከወላጆቻቸው ጋር መወያየታቸው ምን ዓይነት ችሎታ ለማዳበር ይረዳቸዋል?

[በገጽ 81 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የተገላለጠ ነገር የለበሱ ወጣት ሴቶች ሳይ ለእነሱ ያለኝ አክብሮት ይቀንሳል። ልከኛና የሚያምር ልብስ የለበሱ ሴቶች ሳይ ግን ‘እኔም እንዲህ ነው መልበስ የምፈልገው’ ብዬ አስባለሁ።”—ናታሌን

[በገጽ 82 እና 83 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የመልመጃ ሣጥን

ልብስ ለመምረጥ የሚረዳ መልመጃ

መመሪያ፦ ገጽ 82⁠ን እና 83⁠ን ፎቶ ኮፒ አድርጊ። ከዚያም አንቺ በስተግራ በኩል ያለውን መልመጃ ሥሪ፤ ወላጆችሽ ደግሞ በስተቀኝ ያለውን መልመጃ እንዲሠሩ ጠይቂያቸው። ከዚያም ወረቀታችሁን ተለዋወጡና በመልሶቻችሁ ላይ ተወያዩ። ያልጠበቃችሁትን መልስ አገኛችሁ? አንዳችሁ ስለ ሌላው አመለካከት ምን አዲስ ነገር አስተዋላችሁ?

አንቺ የምትሠሪው ልትለብሺው ወይም ልትገዢው ስለፈለግሽው አንድ ልብስ አስቢ።

ይህን ልብስ የወደድሽው ለምንድን ነው? ዋነኛ ከምትዪው ምክንያት ጀምረሽ ከታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች እንደ ቅደም ተከተላቸው ደረጃ ስጫቸው።

․․․․․ ታዋቂ ዲዛይነር ስለሠራው

․․․․․ ወንዶች ስለሚወዱት

․․․․․ ጓደኞቼ የሚለብሱት እንደዚህ ስለሆነ

․․․․․ ስለሚመች

․․․․․ ርካሽ ስለሆነ

․․․․․ ሌላ ․․․․․

ወላጆቼ ልብሱን ሲያዩት ምን ይላሉ?

□ “በጭራሽ አይሆንም”

□ “ምንም አይል”

□ “ጥሩ ነው”

ወላጆቼ ልብሱን ካልወደዱት ሊሰጡ የሚችሉት ምክንያት

□ “ሰውነትን ያጋልጣል”

□ “የተዝረከረከ ነው”

□ “ዘመን አመጣሽ ነው”

□ “እኛን ያስነቅፈናል”

□ “በጣም ውድ ነው”

□ ሌላ ․․․․․

በዚህ ጉዳይ ለመስማማት ምን ማድረግ እንችላለን?

ወላጆቼ የሰጡት አስተያየት ትክክል የሚሆነው ከምን አንጻር ነው?

․․․․․

ወላጆቼ ልብሱን እንዲቀበሉት ምን ዓይነት ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል?

․․․․․

ወላጆችሽ የሚሞሉት ልጃችሁ ልትለብሰው ወይም ልትገዛው ስለፈለገችው አንድ ልብስ አስቡ።

ልጃችሁ ይህን ልብስ የወደደችው ለምን ይመስላችኋል? ዋነኛ ምክንያቷ እንደሆነ ከምታስቡት ጀምራችሁ ከታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች እንደ ቅደም ተከተላቸው ደረጃ ስጧቸው።

․․․․․ ታዋቂ ዲዛይነር ስለሠራው

․․․․․ ወንዶች ስለሚወዱት

․․․․․ ጓደኞቿ የሚለብሱት እንደዚህ ስለሆነ

․․․․․ ስለሚመች

․․․․․ ርካሽ ስለሆነ

․․․․․ ሌላ ․․․․․

ልብሱን ስናየው የምንሰጠው ምላሽ

□ “በጭራሽ አይሆንም”

□ “ምንም አይል”

□ “ጥሩ ነው”

ልብሱን ያልወደድንበት ምክንያት

□ “ሰውነትን ያጋልጣል”

□ “የተዝረከረከ ነው”

□ “ዘመን አመጣሽ ነው”

□ “እኛን ያስነቅፈናል”

□ “በጣም ውድ ነው”

□ ሌላ ․․․․․

በዚህ ጉዳይ ለመስማማት ምን ማድረግ እንችላለን?

ይህን ልብስ ያልወደድነው እኛ የምንመርጠው ዓይነት ስላልሆነ ብቻ ነው?

□ አዎ □ ሊሆን ይችላል □ አይደለም

ወላጆቼ ልብሱን እንዲቀበሉት ምን ዓይነት ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል?

․․․․․

ውሳኔ ․․․․․

[በገጽ 84 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ወንዶችስ ምን ማለት ይቻላል?

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተወያየንባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለወንዶችም ይሠራሉ። በአለባበስ ረገድ ልከኛ ሁን። አለባበስህ፣ የተሰወረውን የልብ ሰው ማለትም ውስጣዊ ማንነትህን የሚያሳይ ይሁን። አንድን ልብስ ለመልበስ ወይም ለመግዛት ስታስብ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ልብስ ስለ እኔ ምን ይናገራል? ልብሱ “የሚናገረው ነገር” እውነተኛ ማንነቴን ያንጸባርቃል?’ አለባበሳችን ስለ ማንነታችን የሚያስተላልፈው መልእክት እንዳለ አስታውስ። ልብሶችህ የማታምንባቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቁ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ አድርግ!

[በገጽ 80 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለባበስ ስለ አንድ ሰው ማንነት በግልጽ ይናገራል። ታዲያ ልብሳችሁ ስለ እናንተ ምን ይላል?