በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ነገሮች አስደሳች እንዲሆኑልኝ ምን ላድርግ?

መንፈሳዊ ነገሮች አስደሳች እንዲሆኑልኝ ምን ላድርግ?

ምዕራፍ 38

መንፈሳዊ ነገሮች አስደሳች እንዲሆኑልኝ ምን ላድርግ?

የ16 ዓመቱ ጆሽዋ አልጋው ላይ ጋደም ብሏል። እናቱ መኝታ ቤቱ በር ላይ ቆማ ኮስተር በማለት “ጆሽዋ፣ ተነሳ እንጂ! ዛሬ ስብሰባ እንዳለን ታውቅ የለ እንዴ!” አለችው። የጆሽዋ ቤተሰብ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ቤተሰቡ ካሉት ቋሚ ፕሮግራሞች አንዱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጆሽ ወደ ስብሰባ መሄድ እየሰለቸው መጥቷል።

ጆሽ እየተነጫነጨ “እማዬ! እኔ ባልሄድስ?” አላት።

እናቱ “እንግዲህ መነጫነጩን ተውና ተነስተህ ለባብስ፤ ዛሬም አርፍጄ መድረስ አልፈልግም!” ብላው መሄድ ጀመረች።

ጆሽ እናቱ ከአጠገቡ ብዙም ሳትርቅ “ግን’ኮ አንቺ የይሖዋ ምሥክር ስለሆንሽ እኔም የአንቺን ሃይማኖት መከተል አለብኝ ማለት አይደለም” በማለት ተናገረ። ይህን ሲል እናቱ ቆም ስላለች የተናገረውን እንደሰማች ገብቶታል። ሆኖም ምንም መልስ ሳትሰጠው መንገዷን ቀጠለች።

በዚህ ጊዜ ጆሽዋ የተናገረው ነገር ጸጸተው። እናቱን ማሳዘን አይፈልግም። ይሁን እንጂ ይቅርታ ለመጠየቅም አላሰበም። ማድረግ የሚችለው ነገር አንድ ብቻ ነው።

ጆሽ ደስ ባይለውም ከአልጋው ተነስቶ ልብሱን መለባበስ ጀመረ። “የራሴን ውሳኔ ማድረግ የምችልበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም” በማለት አጉተመተመ። “እኔ በጉባኤያችን እንዳሉት ልጆች አይደለሁም። ክርስቲያን መሆን አልፈልግም!”

አንተስ እንደ ጆሽ ተሰምቶህ ያውቃል? ሌሎች በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በደስታ ሲካፈሉ አንተ ግን እንዲህ የምታደርገው ግዴታ ስለሆነብህ ብቻ እንደሆነ የሚሰማህ ጊዜ አለ? ለምሳሌ ያህል፦

● መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አስተማሪህ የሚሰጥህን የቤት ሥራ ከመሥራት እንደማይለይ ይሰማሃል?

● ከቤት ወደ ቤት እየሄድህ መስበክ አትወድም?

● ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ብዙውን ጊዜ አሰልቺ ይሆኑብሃል?

ከላይ ላሉት ጥያቄዎች መልስህ “አዎ” የሚል ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አንተም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ እስቲ እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ማጥናት የሚባለው ነገር እንደማይሆንልህ ይሰማህ ይሆናል። ለተወሰነ ሰዓት አንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስቸግርህ ይሆናል፤ በሌላ አባባል ሐሳብህን መሰብሰብ ይከብድሃል። በዚያ ላይ ደግሞ ‘ለትምህርት ቤት የማጠናው መቼ አነሰ!’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ።

ማጥናት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ከመሆኑም ሌላ “እውነትን ለማስተማር፥ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፥ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16 የ1980 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልህ አንዳንድ ነገሮችን ቀደም ሲል ባላሰብኸው መንገድ ለመረዳት ያስችልሃል። እውነቱን ለመናገር ማንኛውም ጠቃሚ ነገር ጥረት ሳይደረግ አይገኝም። በአንድ የስፖርት ዓይነት ጥሩ ችሎታ ለማዳበር ከፈለግህ ሕጎቹን ማወቅና ልምምድ ማድረግ አለብህ። ጤናማ መሆን ከፈለግህም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብሃል። በተመሳሳይም ስለ ፈጣሪህ ለማወቅ የአምላክን ቃል ማጥናት ያስፈልግሃል።

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ የሕይወቴን አቅጣጫ በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ። በትምህርት ቤት ያሉት ልጆች የማይፈጽሙት መጥፎ ድርጊት አልነበረም፤ ስለዚህ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ፦ ‘እንደ እነሱ መሆን እፈልጋለሁ? ወላጆቼ የሚያስተምሩኝ ነገር እውነት ነው?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች ራሴ መልስ ማግኘት ነበረብኝ።”—ትሼድዛ

“የተማርኩት ነገር እውነት መሆኑን ተጠራጥሬ አላውቅም፤ ያም ቢሆን ይህንን ራሴ ማረጋገጥ አስፈልጎኝ ነበር። ይህን ሃይማኖት የምከተለው የቤተሰቦቼ ሃይማኖት ስለሆነ ሳይሆን ራሴ ስላመንኩበት ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል።”—ኔሊሳ

ምን ማድረግ ትችላለህ? ለአንተ የሚስማማህ የጥናት ፕሮግራም አውጣ። ምርምር ልታደርግባቸው የምትፈልጋቸውን ርዕሰ ጉዳዮች አንተው ራስህ ምረጥ። ከምን መጀመር ትችላለህ? ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * እንደተሰኘው ያለ መጽሐፍ ተጠቅመህ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት ስለ እምነትህ ምርምር ለምን አታደርግም?

ለምን እንዲህ አታደርግም? ቀጥሎ ከቀረቡት መካከል ጥልቀት ያለው ምርምር ልታደርግባቸው በምትፈልገው ሁለት ወይም ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች ላይ ✔ አድርግ፤ አሊያም ምርምር ልታደርግበት የምትፈልገውን ሌላ ርዕስ መጻፍ ትችላለህ።

በእርግጥ አምላክ አለ?

□ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት መሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?

□ ከዝግመተ ለውጥ ይልቅ በፍጥረት የማምነው ለምንድን ነው?

□ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ይህ መንግሥት መኖሩን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

□ ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ለሌሎች ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

□ ትንሣኤ ይኖራል ብዬ እንዳምን የሚያደርገኝ ምንድን ነው?

□ እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

․․․․․

ተፈታታኝ ሁኔታ 2 በአገልግሎት መካፈል

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ለሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር ወይም ደግሞ በአገልግሎት ላይ ሳለህ የትምህርት ቤት ጓደኛህን ማግኘት ሊያስፈራህ ይችላል።

በአገልግሎት መካፈል የሚኖርብህ ለምንድን ነው? ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ለመስበክ የሚያነሳሱን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ ቦታዎች፣ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች በአምላክም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ያምናሉ። ሆኖም እነዚህ ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚገልጸውን ተስፋ አያውቁም። አንተ ግን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትህ አብዛኞቹ እኩዮችህ እየፈለጉ ያሉትንና የሚያስፈልጋቸውን እውቀት አግኝተሃል! ስለምታምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርህ ለራስህ ጥሩ ግምት እንዲኖርህ ይረዳሃል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛለህ።—ምሳሌ 27:11

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “እኔና ጓደኛዬ ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ጥሩ መግቢያዎችን ተዘጋጀን፤ እንዲሁም ሰዎች ለሚያነሷቸው የተቃውሞ ሐሳቦች እንዴት መልስ መስጠት እንደምንችልና ተመላልሶ መጠየቆችን እንዴት እንደምናደርግ ተለማመድን። ለአገልግሎት ይበልጥ በተዘጋጀሁ መጠን አገልግሎቴ ይበልጥ አስደሳች እየሆነልኝ መጣ።”—ኔሊሳ

“በዕድሜ ስድስት ዓመት የምትበልጠኝ አንዲት እህት በጣም ረድታኛለች! አገልግሎት ይዛኝ ትወጣ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቁርስ ትጋብዘኝ ነበር። አንዳንድ አበረታች ጥቅሶችን ያሳየችኝ ሲሆን ጥቅሶቹ አስተሳሰቤን እንዳስተካክል ረድተውኛል። የእሷ ግሩም ምሳሌነት አሁን ሰዎችን ለመርዳት የበለጠ ጥረት እንዳደርግ አነሳስቶኛል። ትልቅ ውለታ እንደዋለችልኝ ይሰማኛል!”—ሻንቲ

ምን ማድረግ ትችላለህ? ከጉባኤያችሁ አባላት መካከል የአገልግሎት ጓደኛህ ሊሆን የሚችል በዕድሜ የሚበልጥህ ሰው ፈልግ፤ እርግጥ ይህን ስታደርግ የወላጆችህን ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልግህ ይሆናል። (የሐዋርያት ሥራ 16:1-3) መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 27:17) ተሞክሮ ካካበቱ በዕድሜ የሚበልጡህ ሰዎች ጋር መቀራረብ ብዙ ጥቅሞች አሉት። የ19 ዓመቷ አሌክሲስ “እንደ እውነቱ ከሆነ በዕድሜ ከሚበልጡን ጋር መሆን ሁሉን ነገር ቀላል ያደርገዋል” በማለት ተናግራለች።

ለምን እንዲህ አታደርግም? ከወላጆችህ ሌላ በአገልግሎት ሊረዳህ የሚችል ሰው በጉባኤህ ውስጥ አለ? ስሙን ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ተፈታታኝ ሁኔታ 3 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት

ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ቀኑን ሙሉ ትምህርት ቤት ስትማር ትውላለህ፤ ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለማዳመጥ ከአንድ ሰዓት በላይ መቀመጥ ስልችት ሊልህ ይችላል።

መሰብሰብ የሚኖርብህ ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት ይመክራል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።”—ዕብራውያን 10:24, 25

እኩዮችህ ምን ይላሉ? “ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ነው። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ራስን ማስገደድ ያስፈልጋል። ተዘጋጅተህ ከሄድክ ትምህርቱ ስለ ምን እንደሆነ ይገባሃል፤ በዚያ ላይ ደግሞ መሳተፍ ስለምትችል ስብሰባው አስደሳች ይሆንልሃል።”—ኤልዳ

“በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስሰጥ ስብሰባዎቹ ይበልጥ አስደሳች እንደሚሆኑልኝ አስተውያለሁ።”—ጄሲካ

ምን ማድረግ ትችላለህ? በቅድሚያ ጊዜ መድበህ ተዘጋጅ፤ ከቻልክ ደግሞ በስብሰባዎቹ ላይ ሐሳብ ስጥ። እንዲህ ካደረግህ አንተም ለስብሰባው የራስህን ድርሻ እንደምታበረክት ይሰማሃል።

ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፦ ይበልጥ የሚያስደስትህ አንድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በቴሌቪዥን መመልከት ነው ወይስ ራስህ መጫወት? ተመልካች ከመሆን ይልቅ በጨዋታው መሳተፍ ይበልጥ እንደሚያስደስት ግልጽ ነው። ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ።

ለምን እንዲህ አታደርግም? ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት የምትችለው መቼ እንደሆነ ከታች በተሰጠው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ፤ ይህን ለማድረግ በሳምንት 30 ደቂቃ ሊበቃህ ይችላል።

․․․․․

ብዙ ወጣቶች በመዝሙር 34:8 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት በራሳቸው ሕይወት ማየት ችለዋል። ጣት ስለሚያስቆረጥም አንድ ምግብ መስማት ብቻውን ምን ያህል ደስታ ያስገኛል? ምግቡን ራስህ ብታጣጥመው ግን ይበልጥ እንደምትደሰት የታወቀ ነው። አምላክን በማምለክ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ አንተው ራስህ ለምን ቀምሰህ አታየውም? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው “ይህን በማድረጉ ደስተኛ ይሆናል” በማለት ይናገራል።—ያዕቆብ 1:25

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ግቦች ማውጣትና ያወጣሃቸው ግቦች ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ቁልፍ ጥቅስ

“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2

ጠቃሚ ምክር

ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዋና ዋና ነጥቦችን ጻፍ። እንዲህ ስታደርግ ጊዜው ሳይታወቅህ የሚሄድ ሲሆን ስብሰባዎች አስደሳች ይሆኑልሃል!

ይህን ታውቅ ነበር?

ስለምታምንባቸው ነገሮች ምርምር ማድረግህ ስህተት አይደለም። እንዲያውም የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳትህና በእነሱ ላይ ምርምር ማድረግህ ስለ አምላክ የምታምነው ነገር እውነት መሆኑን እንድታረጋግጥ ያስችልሃል።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ․․․․․ ደቂቃ እመድባለሁ፤ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ደግሞ በየሳምንቱ ․․․․․ እመድባለሁ።

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይበልጥ በትኩረት ለማዳመጥ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል አሰልቺ የሚመስላቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

● በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ሦስት የአምልኳችን ገጽታዎች መካከል አንተ ማሻሻያ ማድረግ የሚኖርብህ በየትኛው ላይ ነው?

[በገጽ 278 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ይህን ሃይማኖት የያዝኩት ራሴ ስላመንኩበት እንጂ የወላጆቼ ሃይማኖት ስለሆነ አይደለም። ይሖዋ የእኔም አምላክ ነው፤ ከእሱ ጋር የመሠረትኩትን ዝምድና የሚያበላሽብኝ ምንም ነገር ማድረግ አልፈልግም።”—ሳማንታ

[በገጽ 280 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ግብ አውጥተዋል

መጽሐፍ ቅዱስ “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን . . . አታውቁም” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 4:14) አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው ሊቀጩ ይችላሉ። የካትሪናን እና የካይልን ተሞክሮ ስታነብ እነዚህ ወጣቶች ገና በልጅነታቸው ሕይወታቸው ቢያልፍም አስቀድመው መንፈሳዊ ግቦች ማውጣታቸውና እነዚህ ግቦች ላይ መድረሳቸው በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም ለማትረፍ ያስቻላቸው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።—መክብብ 7:1

ካትሪና ሕይወቷ ያለፈው በ18 ዓመቷ ነው፤ ይሁን እንጂ የ13 ዓመት ልጅ እያለች ልትደርስባቸው የምትፈልጋቸውን ግቦች በጽሑፍ በማስፈር “የሕይወት እቅድ” አውጥታ ነበር። ካወጣቻቸው ግቦች መካከል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል እና ከአባቷ ጋር በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መሳተፍ ይገኙበታል። “ሕይወቴን ለይሖዋ አምላክ ወስኛለሁ!” በማለት የጻፈች ሲሆን ግቧ የአምላክን “መሥፈርቶች በመከተል እሱን በሚያስደስት መንገድ መኖር” ነበር። በቀብር ሥነ ሥርዓቷ ላይ ካትሪና “መላ ሕይወቷ በይሖዋ አገልግሎት ዙሪያ እንዲያጠነጥን የማድረግ ግብ የነበራት ውብ ወጣት” እንደነበረች ተገልጿል።

ካይል ግብ እንዲያወጣ ከትንሽነቱ ጀምሮ ሥልጠና ተሰጥቶት ነበር። በ20 ዓመቱ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ዘመዶቹ ካይል የጻፈውን “የግብ መጽሐፍ” አገኙ፤ ካይል ይህን መጽሐፍ እናቱ እያገዘችው የጻፈው ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ካይል በማስታወሻው ላይ ካሰፈራቸው ግቦች መካከል መጠመቅ፣ በመንግሥት አዳራሽ ንግግር መስጠት እንዲሁም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ገብቶ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ የሚረዱ ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ ሥራ መካፈል ይገኙበታል። የካይል እናት ልጇ ከዓመታት በፊት የጻፈውን ማስታወሻ ካነበበች በኋላ “እያንዳንዱን ግብ አሳክቷል” ብላለች።

አንተስ ምን ግቦችን አውጥተሃል? ነገ ምን ሊያጋጥምህ እንደሚችል አታውቅም። በመሆኑም እያንዳንዱን ቀን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀምበት። እንደ ካትሪና እና ካይል አንተም ሕይወትህን ከምንም በላይ አስደሳች በሆነው መንገድ ተጠቀምበት። “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄያለሁ” በማለት በሕይወቱ መጨረሻ የተናገረውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተከተል። (2 ጢሞቴዎስ 4:7) የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ለማድረግ ይረዳሃል።

[በገጽ 274 እና 275 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጤናማ መሆን ከፈለግህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚኖርብህ ሁሉ በመንፈሳዊ ሁኔታም ጤናማ ለመሆን የአምላክን ቃል ማጥናት ያስፈልግሃል