በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 9

‘የእግዚአብሔር ኃይል የሆነው ክርስቶስ’

‘የእግዚአብሔር ኃይል የሆነው ክርስቶስ’

1-3. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ባሕር ላይ ምን አስፈሪ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? ኢየሱስስ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ ‘የእግዚአብሔር ኃይል የሆነው ክርስቶስ’ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት ተውጠዋል። በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳለ ድንገት ማዕበል ተነሳ። በዚህ ሐይቅ ላይ ማዕበል ሲያጋጥማቸው ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ የታወቀ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በዓሣ አጥማጅነት ሥራ ረጅም ዓመታት ያሳለፉ ናቸው። * (ማቴዎስ 4:18, 19) ሆኖም በዚህ ጊዜ ያጋጠማቸው “ብርቱ ዐውሎ ነፋስ” በመሆኑ ባሕሩን ክፉኛ አናወጠው። ባለ በሌለ ኃይላቸው ለመቅዘፍ ቢሞክሩም ማዕበሉን ሊቋቋሙት አልቻሉም። ማዕበሉ “ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ” ያናውጣት ጀመር። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢየሱስ ሕዝቡን ሲያስተምር ውሎ ስለደከመው በታንኳይቱ የኋለኛ ክፍል ውስጥ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እንዳይሰምጡ ስለፈሩ ኢየሱስን ቀስቅሰው “ጌታ ሆይ፣ አድነን፣ ጠፋን” ብለው ተማጸኑት።—ማርቆስ 4:35-38፤ ማቴዎስ 8:23-25

2 ኢየሱስ በሁኔታው ምንም አልተረበሸም። ከዚህ ይልቅ ነፋሱንና ባሕሩን “ዝም በል፣ ፀጥ በል” ሲል ገሠጸ። ወዲያውኑም ነፋሱና ማዕበሉ ቆመ፤ “ታላቅ ፀጥታም ሆነ።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ፈርተው እርስ በርሳቸው “ይህ ማን ነው?” ተባባሉ። በእርግጥም ነፋስንና ባሕርን እንደ ትንሽ ልጅ ሊገሥጽ የቻለው ምን ዓይነት ሰው ቢሆን ነው?—ማርቆስ 4:39-41፤ ማቴዎስ 8:26, 27

አዎን፣ ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። የይሖዋ ኃይል በኢየሱስ አማካኝነት አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስ  በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ኢየሱስን ‘የእግዚአብሔር ኃይል የሆነው ክርስቶስ’ ሲል መጥራቱ የተገባ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:24) የአምላክ ኃይል በኢየሱስ አማካኝነት የተገለጸባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ በእኛ ሕይወት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

የአምላክ አንድያ ልጅ ያለው ኃይል

4, 5. (ሀ) ይሖዋ ለአንድያ ልጁ ምን ኃይልና ሥልጣን ሰጥቶታል? (ለ) ኢየሱስ አባቱ የሰጠውን የፍጥረት ሥራ ማከናወን የቻለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረውን ኃይል እስቲ እንመልከት። ይሖዋ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የተጠራውን አንድያ ልጁን ሲፈጥር ‘የዘላለም ኃይሉን’ ተጠቅሟል። (ሮሜ 1:20፤ ቆላስይስ 1:15) ከዚያም ይሖዋ ልጁ በፍጥረት ሥራዎቹ እንዲካፈል በማድረግ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን ሰጥቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ልጅ አስመልክቶ ሲናገር “ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ይላል።—ዮሐንስ 1:3

5 ይህ ሥራ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ሙሉ በሙሉ መረዳት አዳጋች ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኃያላን መላእክትን፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጋላክሲዎችን ያቀፈውን ግዙፍ ጽንፈ ዓለምና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ዝርያዎች የያዘችውን ምድር መፍጠር ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንደሚጠይቅ እስቲ አስብ። የአምላክ አንድያ ልጅ እነዚህን ሥራዎች ማከናወን እንዲችል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው ኃይል ማለትም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተሰጥቶት ነበር። ይህ ልጅ ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር ዋና ሠራተኛ አድርጎ ስለተጠቀመበት ከፍተኛ ደስታ አግኝቷል።—ምሳሌ 8:22-31

6. ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ምን ኃይልና ሥልጣን ተሰጥቶታል?

6 የአምላክ አንድያ ልጅ ከዚህ የላቀ ኃይልና ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል? ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:18) አዎን፣ ኢየሱስ በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ላይ የመግዛት ችሎታና መብት ተሰጥቶታል። “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” እንደመሆኑ መጠን የአባቱን ሥልጣን የሚቀናቀንን የሚታይም ሆነ የማይታይ ‘ኃይል፣ ሥልጣንና አለቅነት ሁሉ የመሻር’  ኃላፊነት ተሰጥቶታል። (ራእይ 19:16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:24-26) ይሖዋ ከራሱ በስተቀር ‘ሁሉን ለኢየሱስ አስገዝቶለታል።’—ዕብራውያን 2:8፤ 1 ቆሮንቶስ 15:27

7. ኢየሱስ ይሖዋ የሰጠውን ኃይል አላግባብ እንደማይጠቀምበት እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ኃይሉን አላግባብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? በፍጹም! አባቱን እጅግ ስለሚወደው እሱን የሚያሳዝን ነገር አያደርግም። (ዮሐንስ 8:29፤ 14:31) ኢየሱስ አባቱ ሁሉን ማድረግ የሚያስችለውን ኃይሉን አላግባብ እንደማይጠቀምበት ጠንቅቆ ያውቃል። ከዚህ ይልቅ ‘በፍጹም ልባቸው በእርሱ የሚታመኑትን ለማበርታት’ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንደሚጠቀም ተመልክቷል። (2 ዜና መዋዕል 16:9 አ.መ.ት) እንደ አባቱ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ፍቅር ስላለው ምንጊዜም ቢሆን ኃይሉን በጎ ለሆነ ዓላማ እንደሚጠቀምበት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 13:1) በዚህ ረገድ ያስመዘገበው ታሪክ እንከን የማይወጣለት ነው። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምን ያህል ኃይል እንደነበረውና ይህን ኃይሉን እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት።

“በቃል ብርቱ”

8. ኢየሱስ ከተቀባ በኋላ ምን እንዲያደርግ ኃይል ተሰጠው? ይህን ኃይልስ የተጠቀመበት እንዴት ነው?

8 ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ በልጅነቱ ናዝሬት ውስጥ በነበረበት ወቅት ምንም ተአምር አልፈጸመም። ይሁን እንጂ በ30 ዓመቱ ሲጠመቅ ይህ ሁኔታ ተለወጠ። (ሉቃስ 3:21-23) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፣ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ” በማለት ይነግረናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:38) “መልካም እያደረገ” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ኃይሉን በአግባቡ እንደተጠቀመበት የሚያመለክት አይደለምን? በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ “በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ” ሆነ።—ሉቃስ 24:19

9-11. (ሀ) ኢየሱስ በአብዛኛው ያስተምር የነበረው በየትኞቹ ቦታዎች ነው? ትምህርቱንስ በምን መንገድ ማቅረብ ነበረበት? (ለ) ሕዝቡ በትምህርቱ የተገረሙት ለምን ነበር?

9 ኢየሱስ በቃል ብርቱ የሆነው እንዴት ነው? በአብዛኛው ያስተምር  የነበረው በሐይቅ ዳርቻዎችና በተራራ አጠገብ እንዲሁም በጎዳናዎችና በገበያ ቦታዎች ነበር። (ማርቆስ 6:53-56፤ ሉቃስ 5:1-3፤ 13:26) ትምህርቱ የአድማጮቹን ትኩረት የማይስብ ቢሆን ኖሮ ጥለውት ይሄዱ እንደነበር የታወቀ ነው። መጻሕፍት ይታተሙ ባልነበረበት በዚያ ዘመን አድማጮች ትምህርቱን በጥሞና አዳምጠው በአእምሯቸውና በልባቸው መቅረጽ ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም የኢየሱስ ትምህርት አድማጮችን የሚመስጥ፣ ግልጽና በቀላሉ ሊታወስ የሚችል መሆን ነበረበት። ይህን ማድረግ ለኢየሱስ አስቸጋሪ አልነበረም። የተራራ ስብከቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

10 በ31 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንድ ቀን ጠዋት በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ኮረብታ ላይ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። አንዳንዶቹ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ከ100 እስከ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው የመጡ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በስተ ሰሜን ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና የባሕር ዳርቻዎች የመጡ ናቸው። ኢየሱስ ቀርበው ሊዳስሱት ይሞክሩ የነበሩትን የታመሙ ሰዎች በሙሉ ፈወሳቸው። ሁሉንም ከፈወሰ በኋላ ማስተማር ጀመረ። (ሉቃስ 6:17-19) አስተምሮ ሲጨርስ ሰዎቹ በትምህርቱ እጅግ ተገረሙ። ለምን?

11 በተራራው ስብከት ላይ ተገኝቶ የነበረ አንድ ሰው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ . . . እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።” (ማቴዎስ 7:28, 29) አድማጮቹ ኢየሱስ እንደ ባለ ሥልጣን ይናገር እንደነበር ማስተዋል ችለዋል። አምላክን ወክሎ ይናገር የነበረ ሲሆን ትምህርቱም በአምላክ ቃል የተደገፈ ነበር። (ዮሐንስ 7:16) ትምህርቶቹ ግልጽ፣ ምክሮቹ አሳማኝ እንዲሁም የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች ሊታበሉ የማይችሉ ናቸው። ትምህርቱ ወሳኝ በሆኑ ቁምነገሮች ላይ ያተኮረ ከመሆኑም በላይ የአድማጮቹን ልብ የሚነካ ነበር። ደስታ ማግኘት፣ መጸለይ፣ የአምላክን መንግሥት መፈለግና ሕይወታቸውን አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ መገንባት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:3–7:27) ያስተማረው ትምህርት እውነትንና ጽድቅን የተጠሙ ሰዎችን ልብ ለተግባር አነሳስቷል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ‘ለመካድና’ ሁሉን ትተው እሱን  ለመከተል ፈቃደኞች ሆነዋል። (ማቴዎስ 16:24፤ ሉቃስ 5:10, 11) ኢየሱስ በቃል ብርቱ ነው መባሉ ምንኛ ተገቢ ነው!

‘በሥራ ብርቱ’

12, 13. ኢየሱስ ‘በሥራ ብርቱ’ የነበረው በምን መንገድ ነው? የፈጸማቸው ተአምራት ብዙ ዓይነት ናቸው እንድንል የሚያደርገንስ ምንድን ነው?

12 ኢየሱስ ‘በሥራም ብርቱ’ ነበር። (ሉቃስ 24:19) ኢየሱስ “[በይሖዋ] ኃይል” የፈጸማቸው ከ30 የሚበልጡ ተአምራት በወንጌሎች ውስጥ በቀጥታ ተጠቅሰው እናገኛለን። * (ሉቃስ 5:17) ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥተዋል። ‘ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር’ በአንድ ወቅት 5,000 ወንዶችን በሌላ ወቅት ደግሞ 4,000 ወንዶችን በተአምር መግቧል። በእነዚህ ጊዜያት ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ወደ 20,000 እንደሚጠጋ ይገመታል።—ማቴዎስ 14:13-21፤ 15:32-38

‘ኢየሱስ በባሕር ላይ ሲሄድ አዩ’

13 ኢየሱስ ብዙ ዓይነት ተአምራት ፈጽሟል። አጋንንትን በማስወጣት በእነሱ ላይ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 9:37-43) ውኃን ወደ ወይን በመለወጥ ግዑዝ በሆኑ ነገሮችም ላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። (ዮሐንስ 2:1-11) በአንድ ወቅት ኢየሱስ በነፋስ ይናወጥ በነበረው በገሊላ ባሕር ላይ ሲራመድ በማየታቸው ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተገርመዋል። (ዮሐንስ 6:18, 19) በበሽታም ላይ ሥልጣን የነበረው ሲሆን አካላዊ ጉድለቶችን፣ ሥር የሰደዱ ሕመሞችንና ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ በሽታዎችን ፈውሷል። (ማርቆስ 3:1-5፤ ዮሐንስ 4:46-54) እነዚህን ፈውሶች ያከናወነው በተለያዩ መንገዶች ነው። አንዳንዶቹ የተፈወሱት ዳስሷቸው ሲሆን ገና በሩቅ ሳለ የተፈወሱም አሉ። (ማቴዎስ 8:2, 3, 5-13) ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ የተፈወሱት ወዲያውኑ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ቀስ በቀስ ነው።—ማርቆስ 8:22-25፤ ሉቃስ 8:43, 44

14. ኢየሱስ በሞት ላይ እንኳ ሥልጣን እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

14 የሚያስገርመው ኢየሱስ በሞት ላይ እንኳ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል።  በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን እንዳስነሳ የሚገልጹ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። አንዲትን የ12 ዓመት ልጅ፣ የአንዲትን መበለት ብቸኛ ልጅና እኅቶቹ በጣም ይወዱት የነበረን አንድ ሰው ከሞት አስነስቷል። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:38-44) የገጠሙት ሁኔታዎች በሙሉ ከአቅሙ በላይ አልነበሩም። የ12 ዓመቷን ልጅ ያስነሳት ወዲያው እንደሞተች ነበር። የመበለቲቱን ልጅ ያስነሳው በዚያው በሞተበት ዕለት በቃሬዛ ተሸክመው ወደ ቀብር እየወሰዱት ሳለ ነበር። አልዓዛርን ደግሞ ያስነሳው ሞቶ ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ነበር።

ኃይልን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ በማስተዋልና በአሳቢነት መጠቀም

15, 16. ኢየሱስ ኃይሉን የተጠቀመው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እንደሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

15 ፍጽምና የሌለው አንድ ሰብዓዊ ገዢ የኢየሱስን ያህል ኃይል ቢኖረው ምን ያህል አላግባብ ሊጠቀምበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፍጹም ነው። (1 ጴጥሮስ 2:22) ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ኃይላቸውን አላግባብ በመጠቀም ሌሎችን ለመጉዳት የሚነሳሱት እንደ ራስ ወዳድነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ስግብግብነት የመሳሰሉ ባሕርያት ስላሏቸው ሲሆን ኢየሱስ ግን ከእነዚህ ባሕርያት የጸዳ ነው።

16 ኢየሱስ ኃይሉን በራስ ወዳድነት የግል ጥቅሙን ለማሟላት አልተጠቀመበትም። ተርቦ በነበረበት ወቅት ድንጋዮችን ወደ እንጀራ እንዲቀይር የቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለም። (ማቴዎስ 4:1-4) ቁሳዊ ነገር ያልነበረው መሆኑ ኃይሉን ለግል ጥቅሙ እንዳላዋለ የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 8:20) የተለያዩ ተአምራትን የፈጸመው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ እንዳልሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ አለ። እነዚህን ተአምራት ለመፈጸም በተወሰነ ደረጃ መሥዋዕትነት መክፈል ጠይቆበታል። የታመሙትን በሚፈውስበት ጊዜ ኃይል ከእሱ ይወጣ ነበር። አንድ ሰው ብቻ በፈወሰበት ጊዜ እንኳ ከእሱ ኃይል እንደወጣ ታውቆት ነበር። (ማርቆስ 5:25-34) ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰዎች እሱን በመዳሰስ እንዲፈወሱ አድርጓል። (ሉቃስ 6:19) ኢየሱስ ራስ ወዳድ እንዳልሆነ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማስረጃ ነው!

17. ኢየሱስ ኃይሉን ማስተዋል በተሞላበት መንገድ እንደተጠቀመበት ያሳየው እንዴት ነው?

 17 ኢየሱስ ኃይሉን የተጠቀመበት ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ነው። ተአምራት የፈጸመው እንዲሁ ለታይታ ወይም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ብሎ አልነበረም። (ማቴዎስ 4:5-7) የሄሮድስን የተሳሳተ የማወቅ ጉጉት ለማርካት ሲል ብቻ ተአምር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ሉቃስ 23:8, 9) ያለው ኃይል በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲታወቅለት ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ብዙውን ጊዜ የፈወሳቸው ሰዎች ለሌሎች እንዳይናገሩ ያዝዛቸው ነበር። (ማርቆስ 5:43፤ 7:36) ዝናውን በመስማት ብቻ ለእሱ ልዩ ስሜት እንዲያድርባቸው ማድረግ አልፈለገም።—ማቴዎስ 12:15-19

18-20. (ሀ) ኢየሱስ ኃይሉን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ አንድን መስማት የተሳነው ሰው ስለፈወሰበት መንገድ ስታስብ ምን ይሰማሃል?

18 ኃያል የሆነው ኢየሱስ ሥልጣናቸውን ለሰዎች ችግርና ስቃይ ደንታ ቢስ በሆነ መንገድ ከሚጠቀሙ ሰብዓዊ ገዥዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። ኢየሱስ ለሰዎች ያስባል። የተለያየ መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸውን ሰዎች ሲያይ አንጀቱ ስለሚንሰፈሰፍ ችግራቸውን ያስወግድላቸው ነበር። (ማቴዎስ 14:14) ለስሜታቸውና ለፍላጎታቸው ስለሚጨነቅ ኃይሉን በአሳቢነት ይጠቀምበት ነበር። በማርቆስ 7:31-37 ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው ልብ የሚነካ ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው።

19 በዚህ ወቅት ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እሱ ይዘዋቸው የመጡትን በርካታ ሕሙማን ፈውሷል። (ማቴዎስ 15:29, 30) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለአንድ ሰው ልዩ አሳቢነት በማሳየት ለብቻው ነጥሎ ወሰደው። ሰውየው መስማት የተሳነውና አጥርቶ የመናገር ችግር ያለበት ነበር። ኢየሱስ ይህ ሰው ሊያፍር ወይም ሊሸማቀቅ እንደሚችል ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በአሳቢነት ከሕዝቡ ነጥሎ ገለል ወዳለ ቦታ ወሰደው። ከዚያም ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ሰውየው እንዲገነዘብ ለማድረግ ሲል አንዳንድ ምልክቶች ተጠቀመ። “ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ።” * (ማርቆስ 7:33) በመቀጠል ኢየሱስ ወደ ሰማይ አሻቅቦ ተመለከተና  ቃተተ። ይህን ያደረገው ሰውየው የሚፈወሰው በአምላክ ኃይል መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው። በመጨረሻም ኢየሱስ “ተከፈት” አለ። (ማርቆስ 7:34) በዚህ ጊዜ ሰውየው መስማትና አጥርቶ መናገር ቻለ።

20 ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም የታመሙ ሰዎችን በሚፈውስበት ጊዜ እንኳ ለሰዎቹ ስሜት ያስብ የነበረ መሆኑ እንዴት ልብ የሚነካ ነው! ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ርኅሩኅና አሳቢ ንጉሥ በመሲሐዊ መንግሥቱ ላይ ገዢ አድርጎ መሾሙ የሚያስደስት አይደለምን?

ትንቢታዊ ትርጉም ያዘለ

21, 22. (ሀ) ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ምን ያመለክታሉ? (ለ) ኢየሱስ በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን ያለው በመሆኑ በንጉሣዊ ግዛቱ ወቅት ምን ያደርጋል ብለን መጠበቅ እንችላለን?

21 ኢየሱስ ምድር ሳለ የፈጸማቸው ተአምራት ወደፊት በንጉሣዊ ግዛቱ ውስጥ የሚፈሱትን ታላላቅ በረከቶች ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናቸው። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተአምራትን ያከናውናል። ወደፊት ከሚጠብቁን አስደሳች ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

22 ኢየሱስ የተዛባውን የምድርን ሥነ ምሕዳር መልሶ ያስተካክላል። ከዚህ ቀደም ማዕበልን ፀጥ በማድረግ በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን እንዳለው ማሳየቱን አስታውስ። በኢየሱስ ንጉሣዊ የግዛት ዘመን ሰዎች አውሎ ነፋስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሊደርሱብን ይችላሉ የሚል ሥጋት አያድርባቸውም። ይሖዋ ምድርንና በላይዋ የሚኖሩትን ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ በፈጠረበት ጊዜ ኢየሱስ ዋና ሠራተኛ ሆኖ በመሥራቱ የምድር አፈጣጠር ለእሱ እንግዳ አይደለም። የምድርን የተፈጥሮ ሀብት እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል ያውቃል። በእሱ የግዛት ዘመን መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች።—ሉቃስ 23:43

23. ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ኢየሱስ የሰው ልጆች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች የሚያሟላው እንዴት ነው?

23 የሰው ልጆች ስለሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮችስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ በጥቂት እንጀራና ዓሣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገብ መቻሉ በእሱ የግዛት ዘመን ረሃብን እንደሚያስወግድ  ያረጋግጥልናል። ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ስለሚያገኝ ረሃብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አይኖርም። (መዝሙር 72:16) በሕመምና በበሽታ ላይ ሥልጣን ያለው መሆኑ ሕመምተኞችን፣ ማየትና መስማት የተሳናቸውን፣ አንካሶችንና ሽባዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈውስ እንድንተማመን ያደርገናል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ኢየሱስ ሙታንን ለማስነሳት ያለው ችሎታ አባቱ ከሞት እንዲነሱ የሚፈልጋቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማስነሳት የሚያስችል ኃይልም እንደተሰጠው ያረጋግጥልናል።—ዮሐንስ 5:28, 29

24. ኢየሱስ ስላለው ኃይል ስናሰላስል ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል? ለምንስ?

24 ኢየሱስ ስላለው ኃይል ስናሰላስል ይህ የአምላክ ልጅ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን እናስታውስ። (ዮሐንስ 14:9) በመሆኑም ኢየሱስ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይሖዋ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት እንድንገነዘብ ያስችለናል። ለምሳሌ የሥጋ ደዌ ያለበትን አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ ያሳየውን ርኅራኄ አስብ። ኢየሱስ ሰውየው እጅግ ስላሳዘነው ዳሰሰውና “እወድዳለሁ” አለው። (ማርቆስ 1:40-42) ይሖዋ እንዲህ በመሳሰሉ ታሪኮች አማካኝነት ‘ኃይሌን የምጠቀምበት በዚህ መንገድ ነው’ እያለን እንዳለ አድርገን እናስብ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ኃይሉን እንዲህ ባለ ፍቅራዊ መንገድ የሚጠቀምበት መሆኑ እሱን እንድታወድስና እንድታመሰግን አይገፋፋህም?

^ አን.1 በገሊላ ባሕር ላይ ድንገተኛ ማዕበል ብዙ ጊዜ ይነሳል። ይህ ባሕር በጣም ዝቅተኛ ቦታ ላይ (ከባሕር ወለል በታች 200 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ) ስለሚገኝ ባሕሩ ላይ ያለው አየር በአካባቢው ካለው አየር ይበልጥ ሞቃታማ ነው። በዚህም የተነሳ በከባቢ አየር ውስጥ ነውጥ ይፈጠራል። በስተ ሰሜን በኩል ከሚገኘው የሄርሞን ተራራ ተነስተው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ የሚነፍሱ ኃይለኛ ነፋሳት አሉ። ፀጥ ብሎ የነበረው የአየር ጠባይ ድንገት ተለውጦ ኃይለኛ ማዕበል ሊነሳ ይችላል።

^ አን.12 ከዚህም በተጨማሪ በወንጌሎች ውስጥ በርከት ያሉ ተአምራት አንድ ላይ ጠቅለል ተደርገው የተገለጹባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የአንዲት ‘ከተማ ሕዝብ በሙሉ’ ኢየሱስን ለማየት ወጥቶ የነበረ ሲሆን በዚያ የነበሩትን “ብዙ” ሕሙማን ፈውሷል።—ማርቆስ 1:32-34

^ አን.19 እንትፍ ማለት በአይሁዶችም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ የተለመደ የፈውስ ምልክት ነበር። ምራቅን ለፈውስ ይጠቀሙበት እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ በረቢዎች ጽሑፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። ኢየሱስ እንትፍ ያለው ሰውየው ሊፈወስ መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ምራቁን ለመፈወስ እንደሚያገለግል መድኃኒት አድርጎ አልተጠቀመበትም።