በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 34

ስንሞት ምን እንሆናለን?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

እንደምታውቀው በዛሬው ጊዜ ሰዎች ያረጃሉ፣ ይታመማሉ እንዲሁም ይሞታሉ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ልጆችም እንኳን ይሞታሉ። ሞትንና የሞተን ሰው መፍራት ይኖርብሃል?— ስንሞት ምን እንደምንሆን ታውቃለህ?—

በዛሬው ጊዜ በሕይወት ካሉት ሰዎች መካከል ከሞተ በኋላ እንደገና ወደ ሕይወት የተመለሰና ስንሞት ምን እንደምንሆን ሊነግረን የሚችል ሰው የለም። ይሁን እንጂ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከሞት የተነሳ አንድ ሰው ነበር። የእሱን ታሪክ በማንበብ የሞቱ ሰዎች ምን እንደሚሆኑ ልንማር እንችላለን። ይህ ሰው በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በምትገኝ ቢታንያ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ የኢየሱስ ጓደኛ ነው። ስሙ አልዓዛር ሲሆን ማርታና ማርያም የሚባሉ ሁለት እህቶች ነበሩት። የሆነውን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከት።

አንድ ቀን አልዓዛር በጣም ታመመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የነበረው ራቅ ባለ ቦታ ነበር። ስለዚህ ማርታና ማርያም ወንድማቸው አልዓዛር መታመሙን ለኢየሱስ የሚነግር መልእክተኛ ልከው ነበር። ይህን ያደረጉት ኢየሱስ መጥቶ ወንድማቸውን ሊፈውሰው እንደሚችል ያውቁ ስለነበር ነው። ኢየሱስ ሐኪም ባይሆንም ማንኛውንም ዓይነት በሽታ ለመፈወስ የሚያስችል ከአምላክ የተሰጠ ኃይል ነበረው።—ማቴዎስ 15:30, 31

ኢየሱስ አልዓዛር ጋር ከመሄዱ በፊት አልዓዛር በጣም በመታመሙ ሞተ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር እንደተኛና ሊቀሰቅሰው እንደሚሄድ ነገራቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በግልጽ “አልዓዛር ሞቷል” አላቸው። ይህ ስለ ሞት ምን ያስገነዝበናል?— አዎ፣ ሞት ከኃይለኛ እንቅልፍ ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ያስገነዝበናል። ሞት ሕልም እንኳ የማይታይበት በጣም ኃይለኛ እንቅልፍ ነው ሊባል ይችላል።

ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን ለመጠየቅ መጣ። የነማርታ ጓደኞች የሆኑ ብዙ ሰዎች በቦታው ነበሩ። ሰዎቹ የመጡት ወንድማቸው የሞተባቸውን እህትማማቾች ለማጽናናት ነው። ማርታ ኢየሱስ መምጣቱን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች። ማርያምም ወዲያውኑ ኢየሱስን ለማግኘት ወጣች። እሷም በጣም አዝና ስለነበረ እያለቀሰች ኢየሱስ እግር ላይ ተደፋች። ማርያምን የተከተሏት ሌሎች ጓደኞቻቸውም እያለቀሱ ነበር።

ታላቁ አስተማሪ አልዓዛርን የት እንዳደረጉት ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ኢየሱስን አልዓዛር ወደተቀበረበት ዋሻ ወሰዱት። ኢየሱስ ሰዎቹ ሁሉ ሲያለቅሱ ሲመለከት እሱም ማልቀስ ጀመረ። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ያውቀዋል።

ዋሻው በአንድ ትልቅ ድንጋይ ተዘግቶ ስለነበር ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። ድንጋዩን ማንሳታቸው ተገቢ ነው ትላለህ?— ማርታ ድንጋዩን ማንሳት ጥሩ እንዳልሆነ ተሰምቷታል። “ጌታ ሆይ፣ አራት ቀን ስለሆነው አሁን ይሸታል” አለች።

ኢየሱስ ግን “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት። ኢየሱስ፣ ማርታ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነገር ሲፈጸም ልታይ መሆኑን መናገሩ ነበር። ኢየሱስ ምን ሊያደርግ ይሆን? ድንጋዩ ሲነሳ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ ወደ ይሖዋ ጸለየ። ከዚያም በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ። አልዓዛር ከመቃብር ይወጣ ይሆን? መውጣትስ ይችላል?—

አንተ የተኛን ሰው መቀስቀስ ትችላለህ?— አዎ፣ ጮክ ብለህ ከተጣራህ የተኛው ሰው ሊነቃ ይችላል። ይሁን እንጂ በሞት ያንቀላፋን ሰው መቀስቀስ ትችላለህ?— በፍጹም። የቱንም ያህል ጮኸህ ብትጣራ የሞተ ሰው አይሰማም። አንተም ሆንክ እኔ ወይም በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው በምንም ዓይነት መንገድ የሞተን ሰው መቀስቀስ አንችልም።

ኢየሱስ አልዓዛርን ምን አደረገው?

ኢየሱስ ግን የተለየ ነው። እሱ ከአምላክ የተሰጠው ልዩ ኃይል አለው። ስለዚህ ኢየሱስ አልዓዛርን ሲጠራው የሚያስገርም ነገር ተፈጸመ። ለአራት ቀን ሞቶ የቆየው ሰው ከዋሻው ውስጥ ወጣ! ዳግመኛ ሕያው ሆነ! እንደገና መተንፈስና መራመድ እንዲሁም መናገር ቻለ! አዎ፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው።—ዮሐንስ 11:1-44

እስቲ አሁን ሁኔታውን ለማሰብ ሞክር:- አልዓዛር ሲሞት ምን ሆነ? ከሰውነቱ ውስጥ የሆነ ነገር ማለትም ነፍስ ወይም መንፈስ ወጥቶ ሌላ ቦታ ለመኖር ሄዷል? የአልዓዛር ነፍስ ወደ ሰማይ ሄዳ ነበር? በእነዚያ አራት ቀኖች ውስጥ በሰማይ ከአምላክና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲኖር ነበር?—

በፍጹም፣ አልነበረም። ኢየሱስ አልዓዛር ተኝቷል ብሎ እንደነበር አስታውስ። ስትተኛ ምን ይሰማሃል? በጣም ኃይለኛ እንቅልፍ ሲወስድህ በአካባቢህ ምን እየተደረገ እንዳለ አታውቅም፣ አይደል?— ከእንቅልፍህ ስትነቃ ደግሞ ሰዓት ካላየህ በስተቀር ምን ያህል ሰዓት እንደተኛህ አታውቅም።

የሞቱ ሰዎች ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ምንም ነገር አይሰማቸውም። ደግሞም ምንም ነገር መሥራት አይችሉም። አልዓዛር ሞቶ ሳለ የነበረበት ሁኔታም እንደዚሁ ነው። ሞት፣ ኃይለኛ እንቅልፍ ወስዶት ምንም ነገር ማስታወስ የማይችል ሰው ካለበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል።—መክብብ 9:5, 10

አልዓዛር ሞቶ ሳለ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር?

በተጨማሪም እስቲ የሚከተለውን አስብ:- አልዓዛር በእነዚያ አራት ቀናት ውስጥ ሰማይ ላይ ከነበረ ስለዚህ ጉዳይ አይናገርም ነበር?— ደግሞም አልዓዛር ሰማይ ሄዶ ከነበረ ኢየሱስ ከዚያ በጣም ጥሩ ከሆነ ቦታ ወደዚህ ምድር ይመልሰው ነበር?— እንደማይመልሰው የተረጋገጠ ነው!

ሆኖም ብዙ ሰዎች ነፍስ የምትባል ነገር በውስጣችን አለች ብለው ይናገራሉ፤ ደግሞም ሥጋ ከሞተ በኋላ ነፍስ መኖሯን ትቀጥላለች ይላሉ። የአልዓዛር ነፍስ ሕያው ሆና ሌላ ቦታ እየኖረች ነበር ይላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ አይልም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን “ሕያው ነፍስ” እንዳደረገው ይናገራል። አዳም ነፍስ ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ኃጢአት በመሥራቱ እንደሞተ ይናገራል። አዳም ሲሞት የሞተ ነፍስ ሆነና መጀመሪያ ወደተሠራበት አፈር ተመለሰ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም የአዳም ዘሮች ኃጢአትንና ሞትን እንደወረሱ ይናገራል።—ዘፍጥረት 2:7፤ 3:17-19፤ ሮም 5:12

ስለዚህ ከሥጋችን ተለይታ የምትኖር ነፍስ በውስጣችን እንደሌለች በግልጽ ማየት ይቻላል። እያንዳንዳችን ነፍስ ነን። ደግሞም ሰዎች ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ኃጢአትን ስለወረሱ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ ትሞታለች’ በማለት ይናገራል።—ሕዝቅኤል 18:4

ሙታንን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ሙታንን ይፈራሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ሙታን ከሥጋቸው ተለይታ የምትኖርና በሕይወት ያሉትን ሰዎች ልትጎዳ የምትችል ነፍስ አላቸው ብለው ስለሚያምኑ መቃብር አካባቢ አይሄዱም። ይሁን እንጂ የሞተ ሰው በሕይወት ያለን ሰው ሊጎዳ ይችላል?— በፍጹም አይችልም።

አልፎ ተርፎም አንዳንድ ሰዎች ሙታን መንፈስ ሆነው በሕይወት ያሉትን ሰዎች ለማየት ሊመጡ ይችላሉ ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ለሙታን ምግብ ያስቀምጣሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች አምላክ ስለ ሙታን የሚናገረውን ነገር አያምኑም። አምላክ የሚለውን የምናምን ከሆነ ሙታንን አንፈራም። አምላክ ለሰጠን ሕይወት አመስጋኞች ከሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ነገር በማድረግ አመስጋኝነታችንን እናሳያለን።

ይሁን እንጂ ‘አምላክ የሞቱ ልጆችንም ጭምር ያስነሳቸው ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ‘በእርግጥ አምላክ ከሞት ሊያስነሳቸው ይፈልጋል?’ ይህን በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንወያይበታለን።

ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ሰው ራሱ ነፍስ ስለ መሆኑ የሚናገሩትን የሚከተሉትን ተጨማሪ ጥቅሶች እስቲ እናንብብ:- መዝሙር 115:17፤ 146:3, 4ያዕቆብ 5:20