ምዕራፍ ዘጠኝ
አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
1-3. (ሀ) በአቢግያ ቤተሰብ ላይ አደጋ እንዲያንዣብብ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? (ለ) ግሩም ባሕርይ ያላትን ይህችን ሴት በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
አቢግያ ፊቷ የቆመው ወጣት እንደተደናገጠ ከሁኔታው ማስተዋል ችላለች። ወጣቱ በጣም ተረብሿል፤ ደግሞም የተረበሸበት በቂ ምክንያት አለው። በቤተሰቡ ላይ ከባድ አደጋ አንዣቧል። በዚህ ወቅት፣ በአቢግያ ባል በናባል ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙትን ወንዶች በሙሉ ጠራርገው ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ 400 የሚያህሉ ጦረኞች ወደ ናባል ቤት እየገሰገሱ ነበር። ለመሆኑ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?
2 ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው ናባል ነበር። ናባል እንደ ልማዱ ሌሎችን የሚያዋርድና ርኅራኄ የጎደለው ድርጊት ፈጽሟል። በዚህ ወቅት የተሳደበው ግን ፈጽሞ ሊዳፈረው የማይገባውን ሰው ይኸውም የሠለጠኑና ታማኝ የሆኑ ተዋጊዎች ያሉትን ተወዳጅ መሪ ነው። በመሆኑም ከናባል ወጣት ሠራተኞች አንዱ፣ ምናልባትም ከእረኞቹ መካከል ሳይሆን አይቀርም አቢግያ እነሱን ለማዳን አንድ መላ እንደምትፈጥር ተስፋ በማድረግ ወደ እሷ መጣ። ይሁንና አንዲት ሴት አንድን ሠራዊት እንዴት መመከት ትችላለች?
አንዲት ሴት አንድን ሠራዊት እንዴት መመከት ትችላለች?
3 እስቲ በመጀመሪያ ግሩም ባሕርይ ስላላት ስለዚህች ሴት አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት። ለመሆኑ አቢግያ ማን ነች? እንዲህ ያለ ችግር ሊፈጠር የቻለው እንዴት ነው? አቢግያ እምነት በማሳየት ረገድ ከተወችው ምሳሌስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
“አስተዋይና ውብ”
4. ናባል ምን ዓይነት ሰው ነበር?
4 ናባል፣ ለአቢግያ የሚመጥን ባል አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ናባል እግሩ እስኪነቃ ቢዞር ከእሷ የተሻለች ሚስት ሊያገኝ አይችልም፤ አቢግያ የገጠማት ግን በጣም መጥፎ ባል ነው። ይህ ሰው ሀብታም እንደነበር አይካድም። በዚህ የተነሳም ራሱን ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር፤ ይሁን እንጂ ሌሎች ለእሱ ምን አመለካከት ነበራቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ናባል ያለ መጥፎ ስያሜ የተሰጠው ሌላ ሰው የለም ማለት ይቻላል። ስሙ ራሱ “የማይረባ” ወይም “ጅል” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ስም ገና ሲወለድ ወላጆቹ ያወጡለት መጠሪያ ይሆን? ወይስ ከጊዜ በኋላ የተሰጠው ቅጽል ስም? ያም ሆነ ይህ፣ ሰውየው እንደ ስሙ ነበር። ናባል “ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው” ነበር። ጠበኛና ሰካራም የሆነውን 1 ሳሙ. 25:2, 3, 17, 21, 25
ይህን ሰው ብዙዎች ይፈሩት እንዲሁም ይጠሉት ነበር።—5, 6. (ሀ) አቢግያ ከነበሯት ግሩም ባሕርያት መካከል ይበልጥ ማራኪ ሆነው ያገኘሃቸው የትኞቹ ናቸው? (ለ) አቢግያ እንደ ናባል ያለ የማይረባ ሰው ያገባችው ለምን ሊሆን ይችላል?
5 አቢግያ ግን ከናባል ፈጽሞ የተለየች ሴት ነበረች። ስሟ “አባቴ ራሱን ደስተኛ አደረገ” የሚል ትርጉም አለው። ብዙ አባቶች ቆንጆ ልጅ በመውለዳቸው ይኮራሉ፤ አስተዋይ የሆነ አባት ግን ልጁ ውስጣዊ ውበት ያላት መሆኗ ይበልጥ ያስደስተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ውጫዊ ውበት ያለው ሰው እንደ ማስተዋል፣ ጥበብ፣ ድፍረትና እምነት የመሳሰሉትን ባሕርያት ማዳበር አስፈላጊ እንደሆነ አይሰማውም። አቢግያ ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አልነበረችም። መጽሐፍ ቅዱስ አስተዋይና ውብ እንደነበረች በመግለጽ ያወድሳታል።—1 ሳሙኤል 25:3ን አንብብ።
6 በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች፣ አቢግያን የመሰለች ብልህ ሴት እንደ ናባል ያለውን የማይረባ ሰው ማግባቷ ያስገርማቸው ይሆናል። ሆኖም በጥንት ዘመን ብዙውን ጊዜ ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ወላጆች እንደነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ባይሆንም እንኳ ወላጆች ልጆቻቸው ባደረጉት ምርጫ መስማማት አለመስማማታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። የአቢግያ ወላጆች የናባልን ሀብትና ዝና በመመልከት በዚህ ጋብቻ ተስማምተው ወይም ልጃቸው ናባልን እንድታገባ ሁኔታዎችን አመቻችተው ይሆን? ምናልባት ድሃ መሆናቸው እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርጉ ጫና አሳድሮባቸው ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ናባል ሀብታም መሆኑ ጥሩ ባል እንዲሆን አላደረገውም።
7. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸው ለጋብቻ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ማሠልጠን ከፈለጉ ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል? (ለ) አቢግያ ምን ለማድረግ ቆርጣ ነበር?
7 ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ለጋብቻ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው በቁም ነገር ያሠለጥኗቸዋል። ልጆቻቸው ለገንዘብ ብለው ትዳር እንዲመሠርቱ ወይም ኃላፊነት ለመሸከም ሳይደርሱ ገና በልጅነታቸው ለጋብቻ መጠናናት እንዲጀምሩ አይገፋፏቸውም። (1 ቆሮ. 7:36) ይሁንና አቢግያ በዚህ ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቧ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ናባልን አንዴ አግብታዋለች፤ በመሆኑም ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጣ ነበር።
“የስድብ ናዳ አወረደባቸው”
8. ናባል የሰደበው ማንን ነበር? ይህን ማድረጉስ የሞኝነት ተግባር ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
8 ናባል በዚህ ወቅት የወሰደው እርምጃ የአቢግያ ሕይወት ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ ነበር። ናባል የሰደበው ሌላን ሰው ሳይሆን ዳዊትን ነው! ዳዊት ደግሞ ሳኦልን ተክቶ ንጉሥ እንዲሆን አምላክ የመረጠውና ነቢዩ ሳሙኤል የቀባው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ነበር። (1 ሳሙ. 16:1, 2, 11-13) በወቅቱ ዳዊት በቅንዓት ተነሳስቶ ሊገድለው ያሳድደው ከነበረው ከንጉሥ ሳኦል በመሸሽ ከ600 ታማኝ ተዋጊዎቹ ጋር በምድረ በዳ ይኖር ነበር።
9, 10. (ሀ) ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት ምን ትግል ማድረግ ነበረባቸው? (ለ) ናባል ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ላደረጉለት ነገር አመስጋኝ መሆን ይገባው ነበር የምንለው ለምንድን ነው? (አንቀጽ 10 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻም ተመልከት።)
9 ናባል የሚኖረው በማዖን ሲሆን የሚሠራው ግን በአቅራቢያው በሚገኘው * እንዲያውም በዚህ አካባቢ መሬት የነበረው ይመስላል። እነዚህ ከተሞች ለበግ እርባታ አመቺ የሆኑ በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙ የግጦሽ መሬቶች የነበሯቸው ሲሆን ናባል ደግሞ 3,000 በጎች ነበሩት። በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበረው አካባቢ ግን ያልለማ ነበር። በስተ ደቡብ ሰፊ የሆነው የፋራን ምድረ በዳ ይገኛል። በስተ ምሥራቅ በኩል የሚገኘው እስከ ጨው ባሕር ድረስ ያለው አካባቢ ደግሞ ገደላ ገደልና ዋሻ የበዛበት ጠፍ መሬት ነበር። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በዚህ አስቸጋሪ አካባቢ ሕይወታቸውን ለማቆየት ትግል ማድረግ ነበረባቸው፤ ምናልባትም የሚበሉትን ለማግኘት ማደን ብሎም ሌሎች በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም አስፈልጓቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ባለጸጋ የሆነውን የናባልን በጎች ከሚጠብቁት እረኞች ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት አጋጣሚ ነበራቸው።
በቀርሜሎስ ነበር፤10 ታታሪ የነበሩት የዳዊት ወታደሮች ከእረኞቹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? የዳዊት ወታደሮች በፈለጉት ጊዜ ከናባል መንጋ በጎችን መዝረፍ ይችሉ ነበር፤ እነሱ ግን እንዲህ አላደረጉም። እንዲያውም እንደ አጥር በመሆን የናባልን መንጎችና እረኞች ከጥቃት ጠብቀዋቸዋል። (1 ሳሙኤል 25:15, 16ን አንብብ።) በጎችም ሆኑ እረኞች ለአደጋ የተጋለጡ ነበሩ። በአካባቢው አውሬዎች በብዛት ይገኙ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ቦታው ለእስራኤል ደቡባዊ ድንበር ቅርብ በመሆኑ ከባዕድ አገር የሚመጡ ወንበዴዎችና ዘራፊዎች ብዙ ጊዜ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር። *
11, 12. (ሀ) ዳዊት ለናባል መልእክት ሲልክ ዘዴኛ እንደሆነና አክብሮት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ናባል ዳዊት ለላከው መልእክት ምላሽ የሰጠበት መንገድ ትክክል ያልነበረው ከምን አንጻር ነው?
11 ዳዊት በዚያ ምድረ በዳ እነዚያን ሁሉ ሰዎች መመገብ ከባድ ሥራ እንደሚሆንበት ምንም ጥያቄ የለውም። በመሆኑም ዳዊት አንድ ቀን ናባል ምግብ እንዲሰጠው ለመጠየቅ አሥር መልእክተኞችን ላከ። ዳዊት ይህን ጥያቄ ያቀረበው ጥሩ ጊዜ መርጦ ነበር። ወቅቱ በጎች የሚሸለቱበት ሲሆን በዚህ የደስታ ጊዜ ደግሞ ድግስ መደገስና ለሌሎች ልግስና ማሳየት የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ዳዊት ጥያቄውን ያቀረበው በትሕትና እና በአክብሮት ነበር። እንዲያውም ራሱን ያስተዋወቀው ‘ልጅህ ዳዊት’ በማለት ሲሆን ምናልባትም ይህን ያለው በዕድሜ ለሚበልጠው ለናባል አክብሮት እንዳለው ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ናባል፣ ዳዊት ላቀረበለት ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጠ?—1 ሳሙ. 25:5-8
12 ናባል የዳዊትን መልእክት ሲሰማ በጣም ተቆጣ! በመግቢያው ላይ የጠቀስነው ወጣት በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለአቢግያ ሲነግራት፣ ናባል በመልእክተኞቹ ላይ ‘የስድብ ናዳ እንዳወረደባቸው’ ገልጾ ነበር። ስስታም የሆነው ናባል እንጀራውን፣ ውኃውንና ያረደውን ፍሪዳ ለማንም እንደማይሰጥ በቁጣ ገለጸ። ዳዊትን እንደማይረባ ሰው በመቁጠር ያፌዘበት ከመሆኑም ሌላ ከጌታው እንደኮበለለ አገልጋይ አድርጎ ተመልክቶታል። ናባል የነበረው አመለካከት ዳዊትን ይጠላው ከነበረው ከሳኦል የተለየ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሁለቱም ቢሆኑ ይሖዋ ለዳዊት ያለው ዓይነት አመለካከት አልነበራቸውም። አምላክ፣ ዳዊትን 1 ሳሙ. 25:10, 11, 14
ይወደው የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንደ አንድ ዓመፀኛ ባሪያ ሳይሆን የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር።—13. (ሀ) ዳዊት የናባልን ስድብ ሲሰማ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) በያዕቆብ 1:20 ላይ የሰፈረው መሠረታዊ ሥርዓት ዳዊት የወሰደው እርምጃ ትክክል እንዳልነበር እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ዳዊት መልእክተኞቹ ወደ እሱ ተመልሰው የናባልን ምላሽ ሲነግሩት በጣም ተናደደ። “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ከዚያም እሱ ራሱ መሣሪያውን በመታጠቅ 400 ሰዎችን አሰልፎ በናባል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ጉዞ ጀመረ። ዳዊት በናባል ቤተሰብ ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ጠራርጎ ለማጥፋት ምሎ ነበር። (1 ሳሙ. 25:12, 13, 21, 22) ዳዊት ለመቆጣት የሚያበቃ ምክንያት የነበረው ቢሆንም ቁጣውን የገለጸበት መንገድ ግን የተሳሳተ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” ይላል። (ያዕ. 1:20) ታዲያ አቢግያ ቤተሰቧን ማዳን የምትችለው እንዴት ነው?
‘ስለ በጎ ሐሳብሽ የተባረክሽ ሁኚ’
14. (ሀ) አቢግያ ናባል የፈጠረውን ችግር ለማስተካከል የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዳለች ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ናባልና አቢግያ ከነበራቸው የባሕርይ ልዩነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አቢግያ የተፈጠረውን ከባድ ችግር ለማስተካከል የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዳለች ማለት ይቻላል። ከባሏ ከናባል በተለየ መልኩ አቢግያ፣ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነበረች። ወጣቱ አገልጋይ ስለ ናባል ሲናገር “እርሱ እንደ ሆነ . . . ባለጌ [“ምናምንቴ፣” የ1954 ትርጉም] ሰው ስለሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም” ብሎ ነበር። * (1 ሳሙ. 25:17) የሚያሳዝነው፣ ናባል ራሱን ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ሌሎች የሚሉትን አይሰማም ነበር። በዛሬው ጊዜም ብዙዎች እንዲህ ዓይነት የእብሪተኝነት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ወጣቱ አገልጋይ፣ አቢግያ ከዚህ የተለየ አመለካከት ያላት ሴት እንደሆነች ያውቅ ነበር፤ የተፈጠረውን ችግር ለእሷ የነገራትም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።
ከናባል በተለየ መልኩ አቢግያ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነበረች
15, 16. (ሀ) አቢግያ በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰችው ባለሙያ ሚስት መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው? (ለ) አቢግያ የወሰደችው እርምጃ የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደማታከብር የሚያሳይ ነው?
15 አቢግያ የሆነውን ነገር ስትሰማ ወዲያውኑ ምን ማድረግ እንዳለባት በማሰብ ፈጣን እርምጃ ወሰደች። መጽሐፍ ቅዱስ “አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም” በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ መፍጠንን የሚያመለክተው ግስ በዚህ ዘገባ ላይ ብቻ ከአቢግያ ጋር በተያያዘ አራት ጊዜ ተሠርቶበታል። አቢግያ ለዳዊትና አብረውት ላሉት ሰዎች እንጀራ፣ የወይን ጠጅ፣ ታርደው የተሰናዱ በጎች፣ የተጠበሰ እሸት፣ ዘቢብ፣ የበለስ ጥፍጥፍና ሌሎች በርካታ ስጦታዎችን አዘጋጀች። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አቢግያ በቤቷ ያለውን ንብረት በሚገባ ታውቅ እንዲሁም ኃላፊነቷን ጥሩ አድርጋ ትወጣ ነበር፤ በእርግጥም ከጊዜ በኋላ በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰችው ጠባየ ምሳሌ 31:10-31) አቢግያ ያዘጋጀችውን ምግብ አገልጋዮቿ ይዘው ቀድመው እንዲሄዱ ካደረገች በኋላ እሷም ተከተለቻቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም” ይላል።—1 ሳሙ. 25:18, 19
መልካም ወይም ባለሙያ ሚስት ጋር ትመሳሰላለች። (16 አቢግያ እንዲህ ማድረጓ የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደማታከብር የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ናባል፣ ይሖዋ በቀባው ሰው ላይ ክፉ ድርጊት የፈጸመ ሲሆን ይህም ምንም ያላጠፉ በርካታ የናባል ቤተሰብ አባላት እንዲገደሉ ሊያደርግ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። አቢግያ እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር ኖሮ ከባሏ ጋር ተባባሪ እንደሆነች አያስቆጥራትም ነበር? በዚህ ጊዜ ለአምላክ የምታሳየው ተገዢነት ለባሏ ከምታሳየው ተገዢነት መቅደም ነበረበት።
17, 18. (ሀ) አቢግያ ከዳዊት ጋር በተገናኘች ጊዜ ምን አደረገች? ምንስ አለችው? (ለ) ዳዊት ልመናዋን እንዲሰማ ያደረገው ምን ነበር?
17 ብዙም ሳይቆይ አቢግያ፣ ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አገኘቻቸው። በዚህ ጊዜም ወዲያው ከአህያዋ በመውረድ በዳዊት ፊት በግንባሯ ተደፍታ እጅ ነሳች። (1 ሳሙ. 25:20, 23) ከዚያም ለባሏም ሆነ ለቤተሰቧ ምሕረት እንዲያደርግላቸው አጥብቃ በመለመን ለዳዊት የውስጧን ሁሉ ነገረችው። ዳዊት ልመናዋን እንዲሰማ ያደረገው ምን ነበር?
18 አቢግያ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ራሷ በመውሰድ ዳዊት ይቅርታ እንዲያደርግላት ጠየቀችው። አቢግያ ባሏ ልክ እንደ ስሙ የማይረባ ሰው መሆኑን አምና መቀበሏን የገለጸች ሲሆን ምናልባትም ይህን ያደረገችው ዳዊት እንዲህ ያለውን ሰው መቅጣቱ ክብሩን ዝቅ እንደሚያደርገው ለመጠቆም ብላ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ዳዊት የሚዋጋው ‘የይሖዋን ጦርነት’ እንደሆነ በመግለጽ የይሖዋ ወኪል መሆኑን እንደምታምን አሳይታለች። አምላክ፣ ዳዊትን ‘በእስራኤል ላይ እንደሚያነግሠው’ መናገሯም ይሖዋ ዳዊትንም ሆነ ንግሥናውን በተመለከተ የገባውን ቃል እንደምታውቅ የሚጠቁም ነው። በተጨማሪም ዳዊት በደም ዕዳ ሊያስጠይቀው ወይም በኋላ ላይ ‘ለሐዘን’ ሊዳርገው ማለትም የሕሊና ጸጸት ሊያስከትልበት የሚችል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስድ ለምናዋለች። (1 ሳሙኤል 25:24-31ን አንብብ።) በእርግጥም አቢግያ የተናገረችው ሐሳብ ደግነት የተንጸባረቀበትና ልብ የሚነካ ነበር!
19. ዳዊት አቢግያ ለተናገረችው ሐሳብ ምን ምላሽ ሰጠ? ያመሰገናትስ ለምንድን ነው?
19 የዳዊት ምላሽ ምን ነበር? አቢግያ ያመጣችለትን ስጦታ ከተቀበለ በኋላ እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስ . . . ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።” አቢግያ እሱን ለማግኘት ፈጥና በመምጣት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዷ ዳዊት ያመሰገናት ከመሆኑም ሌላ ደም ከማፍሰስ እንዲቆጠብ እንዳደረገችውም ገልጿል። “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ” ካላት በኋላ “ቃልሽን ሰምቻለሁ” በማለት በትሕትና ተናግሯል።—1 ሳሙ. 25:32-35
“እነሆ፤ እኔ ገረድህ”
20, 21. (ሀ) አቢግያ ወደ ባሏ ለመመለስ ፈቃደኛ መሆኗ የሚያስገርመው ለምንድን ነው? (ለ) አቢግያ ናባልን የምታነጋግርበትን ጊዜ በመምረጥ ረገድ ደፋርና አስተዋይ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው?
20 አቢግያ ከዳዊት ጋር ከተለያየች በኋላ ስለዚህ አጋጣሚ ማሰቧ አይቀርም፤ ታማኝና ደግ በሆነው በዳዊት እና ጠበኛ በሆነው ባለቤቷ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነትም 1 ሳሙ. 25:36
እንደምታስተውል የታወቀ ነው። ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ማውጠንጠኗን አልቀጠለችም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አቢግያ ወደ ናባል እንደተመለሰች’ ይናገራል። አዎ፣ የሚስትነት ኃላፊነቷን በሚገባ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ወደ ባሏ ተመልሳለች። ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ስለሰጠችው ስጦታ ለናባል መንገር ነበረባት። ምክንያቱም ይህን የማወቅ መብት አለው። ከዚህም በላይ በቤተሰቡ ላይ አንዣብቦ የነበረውን አደጋ እንዴት እንዳስቀረችው ልትነግረው ይገባል፤ ጉዳዩን ከሌላ ሰው ከሚሰማና የከፋ ውርደት ከሚደርስበት ከእሷ መስማቱ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ናባል ልክ እንደ ነገሥታት ድል ያለ ድግስ ደግሶና በጣም ሰክሮ ስለነበር ጉዳዩን ወዲያውኑ ልትነግረው አልቻለችም።—21 በዚህ ጊዜም አቢግያ፣ ባሏን ለማናገር ስካሩ እስከሚበርድለት እስከ ጠዋት ድረስ በመታገሥ ድፍረትና ማስተዋል አሳይታለች። ናባል በነጋታው ስካሩ የሚበርድለትና የምትነግረውን ነገር መረዳት የሚችል ቢሆንም በቁጣ መገንፈሉ ስለማይቀር አሁንም ሁኔታው ለአቢግያ ይበልጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አቢግያ የተከናወነውን ነገር አንድም ሳታስቀር ነገረችው። በዚህ ጊዜ በንዴት ጦፎ ጉዳት ሊያደርስባት እንደሚችል ጠብቃ ሊሆን ይችላል። እሱ ግን በተቀመጠበት ደርቆ ቀረ።—1 ሳሙ. 25:37
22. ናባል ምን ሆነ? ይህ ሁኔታ በቤተሰብ አባላት ላይ ስለሚፈጸም ማንኛውም ግፍ ወይም በደል ምን ያስተምረናል?
22 ናባል እንዲህ የሆነው ምን ነክቶት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ” ይላል። ምናልባት በአንጎሉ ውስጥ ደም ፈስሶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከአሥር ቀናት ገደማ በኋላ ሕይወቱ አለፈ፤ የሞቱ መንስኤ ከበሽታው ጋር የተያያዘ ብቻ ላይሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ” ይላል። (1 ሳሙ. 25:38) አምላክ በወሰደው ጽድቅ የተንጸባረቀበት የፍርድ እርምጃ ምክንያት አቢግያ በትዳሯ ይገጥማት ከነበረው መከራ ተገላገለች። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የቅጣት እርምጃ ባይወስድም ይህ ዘገባ በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ግፍ ወይም በደል ከእሱ እይታ እንደማይሰወር ያስተምረናል። ይሖዋ፣ መቼም ቢሆን እሱ በወሰነው ጊዜ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረጉ አይቀርም።—ሉቃስ 8:17ን አንብብ።
23. አቢግያ ምን ተጨማሪ በረከት አግኝታለች? የዳዊት ሚስት የመሆን አጋጣሚ በማግኘቷ ባሕርይዋ እንዳልተለወጠ እንዴት እናውቃለን?
23 አቢግያ መጥፎ ከነበረው ትዳሯ ከመገላገሏም ባሻገር ሌላ በረከት አግኝታለች። ዳዊት ናባል መሞቱን ሲሰማ መልእክተኞችን በመላክ የጋብቻ ጥያቄ አቀረበላት። እሷም “እነሆ፤ እኔ ገረድህ አንተን ለማገልገል፣ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” በማለት መለሰች። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው አቢግያ የዳዊት ሚስት ልሆን ነው ብላ አልተኩራራችም፤ እንዲያውም አገልጋዮቹን እንኳ ሳይቀር ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች! በዚህ ጊዜም ወደ ዳዊት ለመሄድ ፈጥና እንደተነሳች ዘገባው ይገልጻል።—1 ሳሙ. 25:39-42
24. አቢግያ በአዲሱ ትዳሯ ውስጥ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋት ሊሆን ይችላል? ይሁንና ባሏም ሆነ የምታመልከው አምላክ ለእሷ ምን አመለካከት ነበራቸው?
1 ሳሙ. 30:1-19) በእርግጥም ዳዊት የይሖዋን ምሳሌ እንደሚከተል አሳይቷል፤ ይሖዋ እንደ አቢግያ ያሉ አስተዋይ፣ ደፋርና ታማኝ የሆኑ ሴቶችን የሚወዳቸው ከመሆኑም በላይ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል።
24 አቢግያ ዳዊትን ካገባች በኋላ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላታል ማለት አይደለም፤ በትዳሯ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች አጋጥመዋት ይሆናል። ዳዊት ቀድሞውንም ቢሆን አኪናሆም የምትባል ሚስት ነበረችው፤ በወቅቱ አምላክ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን ይፈቅድ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ያለው ጋብቻ በዚያ ዘመን በነበሩ ታማኝ ሴቶች ላይ ችግር እንደሚያስከትል አይካድም። ከዚህም ሌላ ዳዊት ገና ንጉሥ አልሆነም፤ በመሆኑም ንጉሥ ሆኖ ይሖዋን ማገልገል እስኪጀምር ድረስ ብዙ እንቅፋቶችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙት የታወቀ ነው። ያም ቢሆን አቢግያ ከዳዊት ጋር ባሳለፈችው ዘመን ሁሉ እሱን በመደገፍ ጥሩ አጋር ሆናለታለች፤ ከጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ የወለደችለት ሲሆን ባሏ ምንጊዜም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታትና ከጥቃት እንደሚጠብቃት መገንዘብ ችላለች። እንዲያውም በአንድ ወቅት ማርከው ከወሰዷት ሰዎች እጅ አስጥሏታል! (^ አን.9 እዚህ ላይ የተጠቀሰው በስተ ሰሜን ጫፍ የሚገኘውና ቆየት ብሎ ነቢዩ ኤልያስ የበኣል ነቢያትን የተገዳደረበት ታዋቂ የሆነው የቀርሜሎስ ተራራ አይደለም። (ምዕራፍ 10ን ተመልከት።) ይኼኛው ቀርሜሎስ በስተ ደቡብ ባለው ምድረ በዳ ጫፍ ላይ የሚገኝ ከተማ ነው።
^ አን.10 ዳዊት በአካባቢው የነበሩትን ባለርስቶችና መንጎቻቸውን ከጥቃት መጠበቅን ይሖዋ አምላክን እንደማገልገል አድርጎ ሳይቆጥረው አልቀረም። በዚያ ዘመን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ዝርያዎች በዚያ አካባቢ እንዲኖሩ የይሖዋ ዓላማ ነበር። በመሆኑም ይህን አካባቢ ከባዕድ አገር ወራሪዎችና ዘራፊዎች ጥቃት መጠበቅ ለይሖዋ የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።
^ አን.14 ወጣቱ አገልጋይ ናባልን ለመግለጽ የተጠቀመበት ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “የቤልሆር (የከንቱነት) ልጅ” የሚል ፍቺ አለው። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ዓረፍተ ነገር ሲተረጉሙ ናባል “ማንንም የማይሰማ” ሰው መሆኑን የሚያሳይ መግለጫ የሚጨምሩ ሲሆን ይህም “ለእሱ መናገር ምንም ዋጋ የለውም” ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል።